የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ትንቢተ ኢሳይያስ 23

23
ጢሮስና ሲዶና
1 # ሕዝ. 26፥1—28፥19፤ ኢዮብ 3፥4-8፤ አሞጽ 1፥9-10፤ ዘካ. 9፥1-4፤ ማቴ. 11፥21፤22፤ ሉቃ. 10፥13፤14። ስለ ጢሮስ የተነገረ ትንቢት። እናንተ የተርሴስ መርከቦች ሆይ፥ ወደባቹህ ፈርሷልና አልቅሱ፤ ዜናው ከኪትም ምድር ደርሷችኋል። 2እናንተ በባሕር ዳርቻ የምትኖሩ፥ በባሕርም የሚሻገሩ የሲዶና ነጋዴዎች የሞሉባችሁ፥ ጸጥ በሉ። 3በጥልቅ ውኆቿ ላይ የሺሖር እህልና የዓባይ ወንዝ መከር ገቢዋ ነበር፤ እርሷም የአሕዛብ የንግድ መናኸሪያ ነበረች። 4ባሕሩ “አላማጥሁም፤ አልወለድሁም፤ ወንዶችና ሴቶች ልጆችን አላሳደግሁም” ብሏልና፥ አንቺ ሲዶና ሆይ፥ አንቺ የባሕር ምሽግ ሆይ፥ እፈሪ። 5ከጢሮስ የሚመጣው ዜና፤ በግብጽ በሚሰማበት ጊዜ ጭንቅ ይይዛቸዋል። 6ወደ ተርሴስም ተሻገሩ፤ እናንተ በደሴት የምትኖሩ አልቅሱ። 7በጥንት ዘመን ተቆርቁራ የነበረችው፥ እሩቅ ምድር ድረስ እድትሰፍር እግሮችዋ ያጓጓዟት፥ የደስታችሁ ከተማ ይህች ናት? 8አክሊል በተቀዳጀች፥ ነጋዴዎችዋ መሳፍንት በሆኑ፥ በምድር የከበሩ ሻጮችና ለዋጮች በነበሯት፥ በጢሮስ ላይ ይህን ያሰበ ማን ነበር? 9የክብርን ሁሉ ትዕቢት ሊሽር፥ የምድርንም ክብር ሁሉ ሊያስንቅ የሠራዊት ጌታ ይህን ወስኗል። 10የተርሴስ ልጅ ሆይ፥ የሚከለክልሽ የለምና እንደ ዓባይ ወንዝ በምድርሽ ላይ ፍሰሺ። 11እጁን በባሕር ላይ ዘረግቶ መንግሥታትንም አናውጧል፤ የከነዓንም ምሽጎች እንዲፈርሱ ጌታ አዟል። 12አንቺ የተሰባበርሽ የሲዶና ድንግል ልጅ ሆይ፥ ከእንግዲህ ወዲህ ደስ አይበልሽ፤ ተነሽ ወደ ኪቲም ተሻገሪ፥ በዚያም ደግሞ አታርፊም አለ። 13እነሆ፥ የከለዳውያን አገር! ይህ ሕዝብ ሆኖ አይገኝም፤ አሦራውያን ለምድረ በዳ አራዊት ሰጥተውታል፤ ግንቦቻቸውን ሠሩ፥ አዳራሾችዋንም አፈረሱ፥ ባድማም አደረጓት። 14እናንተ የተርሴስ መርከቦች ሆይ፥ ምሽጋችሁ ፈርሶአልና ዋይ በሉ። 15በዚያም ቀን እንዲህ ይሆናል፤ ጢሮስ እንደ አንድ ንጉሥ ዘመን ሰባ ዓመት ያህል የተረሳች ትሆናለች፤ ከሰባ ዓመት በኋላ ግን ለጢሮስ በጋለሞታ ዘፈን እንደሚሆን እንዲሁ ይሆናል። 16አንቺ የተረሳሽ ጋለሞታ ሆይ፥ መሰንቆ ያዢ በከተማ ላይም ዙሪ፤ መታሰቢያም ይሆንልሽ ዘንድ ዜማን አሳምሪ ዘፈንሽንም አብዢ። 17ከሰባ ዓመትም በኋላ ጌታ ጢሮስን ይጎበኛታል፥ ወደ ዋጋዋም ትመለሳለች፥ ደግሞም በምድር ፊት ላይ ከሆኑ ከዓለም መንግሥታት ሁሉ ጋር ትገለሙታለች። 18ንግድዋና ዋጋው ለጌታ የተቀደሰ ይሆናል፤ ንግድዋንም በልተው ይጠግቡ ዘንድ ማለፊያም ልብስ ይለብሱ ዘንድ በጌታ ፊት ለሚኖሩ ይሆናል እንጂ በዕቃ ቤትና በግምጃ ቤት ውስጥ አይከተትም።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ