ትንቢተ ኢሳይያስ 57

57
1ጻድቅ ይሞታል፥ ማንም ልብ አይለውም፤ ምሕረተኞችም ይወገዳሉ፥ ጻድቃን ከክፉ እንዲድኑ መወሰዳቸውን ማንም አያስተውልም። 2ወደ ሰላም ይገባል፤ በቅንነት የሄደ በአልጋው ላይ ያርፋል። 3እናንተ የአስማተኛይቱ ልጆች፥ የአምንዝራውና የጋለሞታይቱ ዘር፥ ወደዚህ ቅረቡ። 4በማን ታላግጣላችሁ? በማንስ ላይ አፋችሁን ታላቅቃላችሁ? ምላሳችሁንስ በማን ላይ ታስረዝማላችሁ? 5እናንተ በባሉጥ ዛፎች መካከል በለመለመም ዛፍ ሁሉ በታች በፍትወት የምትቃጠሉ፥ እናንተም በሸለቆች ውስጥ በዓለትም ስንጣቂዎች በታች ሕፃናትን የምታርዱ፥ የዓመፅ ልጆችና የሐሰት ዘር አይደላችሁምን? 6በሸለቆው ውስጥ ያሉ የለዘቡ ድንጋዮች እድል ፈንታሽ ናቸው፥ እነርሱም ዕጣዎችሽ ናቸው፤ ለእነርሱም የመጠጥ ቁርባን አፍስሰሻል፥ የእህልንም ቁርባን አቅርበሻል። እንግዲህ በዚህ ነገር አልቈጣም? 7ከፍ ባለውም በረዘመውም ተራራ ላይ መኝታሽን አደረግሽ፥ መሥዋዕትንም ትሠዊ ዘንድ ወደዚያ ወጣሽ። 8ከመዝጊያውና ከመቃኑ በኋላ መታሰቢያሽን አደረግሽ፤ እኔን ትተሽ ለሌላ ተገልጠሻል፥ ወጥተሽ መኝታሽን አስፍተሻል፤ ቃል ኪዳንም ተጋባሻቸው፥ ባየሽበትም ስፍራ ሁሉ መኝታቸውን ወደድሽ። 9ዘይትም ይዘሽ ወደ ንጉሡ ሄድሽ፥ ሽቱሽንም አበዛሽ፥ መልእክተኞችሽንም ወደ ሩቅ ላክሽ፥ እስከ ሲኦልም ድረስ ተዋረድሽ። 10በመንገድሽም ብዛት ደከምሽ፥ ነገር ግን፦ ተስፋ የለም አላልሽም፤ የጉልበትን መታደስ አገኘሽ፥ ስለዚህም አልዛልሽም። 11ሐሰትን የተናገርሺው እኔንም ያላሰብሽው፥ በልብሽም ነገሩን ያላኖርሺው፥ ማንን ሰግተሽ ነው? ማንንስ ፈርተሽ ነው? እኔ ብዙ ጊዜ ዝም አልሁ፥ አንቺም አልፈራሽም። 12እኔ ጽድቅሽን እናገራለሁ፥ ሥራሽም አይረዳሽም። 13ወደ አንቺ የሰበሰብሻቸው በጮኽሽ ጊዜ ይታደጉሽ፤ ንፋስ ግን ይወስዳቸዋል፤ ሽውሽውታም ሁሉን ያስወግዳቸዋል። በእኔ የታመነ ግን ምድሪቱን ይገዛል፥ የተቀደሰውንም ተራራዬን ይወርሳል። 14እርሱም፦ “ጥረጉ፥ መንገድን አዘጋጁ፥ ከሕዝቤም መንገድ ዕንቅፋትን አስወግዱ” ይላል። 15ለዘለዓለም የሚኖር ስሙም ቅዱስ የሆነ፥ ከፍ ያለው ልዑል እንዲህ ይላል፦ የተዋረዱትን ሰዎች መንፈስ ሕያው አደርግ ዘንድ፥ የተቀጠቀጠውንም ልብ ሕያው አደርግ ዘንድ፥ የተቀጠቀጠና የተዋረደ መንፈስ ካለው ጋር በከፍታና በተቀደሰ ስፍራ እቀመጣለሁ። 16መንፈስም የፈጠርሁትም ነፍስ ከፊቴ እንዳይዝል ለዘለዓለም አልጣላም፥ ሁልጊዜም አልቈጣም። 17ኃጢአት ስለ ሞላበት ስግብግብነቱ ተቈጣሁት፤ ቀጣሁት፤ ፊቴንም በቁጣ ከእርሱ ሰወርኩ፤ እርሱ ግን በመንገዱ ገፋበት። 18መንገዶቹን አይቻለሁ፤ ቢሆንም እፈውሰዋለሁ፤ እመራዋለሁ፤ ለእርሱና ስለ እርሱ ለሚያለቅሱትም መጽናናትን እሰጣለሁ። 19#ኤፌ. 2፥17።የከንፈሮችን ፍሬ እፈጥራለሁ፤ በሩቅም በቅርብም ላለው ሰላም ሰላም ይሁን፥ እፈውሰውማለሁ፥ ይላል ጌታ። 20ክፉዎች ግን እንደሚንቀሳቀስ ባሕር ናቸው፤ ጸጥ ሊል አይችልምና፥ ውኆቹም ጭቃና ጉድፍ ያወጣሉ። 21#ኢሳ. 48፥22።ለክፉዎች ሰላም የላቸውም ይላል አምላኬ።

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ