የሉቃስ ወንጌል 2:1-40

የሉቃስ ወንጌል 2:1-40 መቅካእኤ

በዚያም ወራት የመላው ዓለም ሕዝብ እንዲመዘገቡ ከአውግስጦስ ቄሣር ትእዛዝ ወጣ። ቄሬኔዎስ የሶርያ አገረ ገዥ በነበረ ጊዜ ይህ የመጀመሪያው ምዝገባ ተከናወነ። ስለዚህ ሁሉም ለመመዝገብ፥ እያንዳንዱም ወደ የራሱ ከተማ ሄደ። ዮሴፍም ደግሞ ከዳዊት ቤትና ወገን ስለ ነበረ፥ ከገሊላ ከናዝሬት ከተማ ተነሥቶ ቤተልሔም ወደምትባል ወደ ዳዊት ከተማ ወደ ይሁዳ፥ ፀንሳ ከነበረች ከእጮኛው ከማርያም ጋር ሊመዘገብ ሄደ። በዚያም ሳሉ የመውለጃዋ ወራት ደረሰ፤ የበኩር ልጇንም ወለደች፤ በመጠቅለያም ጠቀለለችው፤ በእንግዶችም ማደሪያ ስፍራ ስላልነበራቸው በግርግም አስተኛችው። በዚያም አካባቢ መንጋቸውን በሌሊት ሲጠብቁ በሜዳ ያደሩ እረኞች ነበሩ። እነሆም፥ የጌታ መልአክ ወደ እነርሱ ቀረበ፤ የጌታ ክብርም በዙሪያቸው አበራ፤ ታላቅ ፍርሃትም ፈሩ። መልአኩ ግን እንዲህ አላቸው፦ “እነሆ፥ ለሕዝቡ ሁሉ ታላቅ ደስታ የሚሆን የምሥራች እነግራችኋለሁና አትፍሩ፤ እነሆ! አዳኝ እርሱም ክርስቶስ ጌታ የሆነ ዛሬ በዳዊት ከተማ ተወልዶላችኋልና። ይህም ምልክት ይሆንላችኋል፤ ሕፃን ተጠቅልሎ በግርግምም ተኝቶ ታገኛላችሁ።” ድንገትም ብዙ የሰማይ ሠራዊት ከመልአኩ ጋር ነበሩ። እግዚአብሔርንም እያመሰገኑ፦ “ክብር ለእግዚአብሔር በአርያም ይሁን! ሰላምም ደስ በሚሰኝባቸው ሰዎች መካከል በምድር ይሁን!” አሉ። መላእክትም ከእነርሱ ተለይተው ወደ ሰማይ በወጡ ጊዜ፥ እረኞቹ እርስ በርሳቸው፦ “እንግዲህ እስከ ቤተልሔም ድረስ እንሂድ፤ ጌታም የገለጠልንን ይህን የሆነውን ነገር እንይ፤” ተባባሉ። ፈጥነውም ሄዱ፤ ማርያምንና ዮሴፍን ሕፃኑንም በግርግም ተኝቶ አገኙ። አይተውም ስለዚህ ሕፃን የተነገራቸውን ቃል ገለጡ። የሰሙትም ሁሉ እረኞቹ በነገሩአቸው ነገር ተደነቁ፤ ማርያም ግን ይህን ነገር ሁሉ በልብዋ እያሰላሰለች ትጠብቀው ነበር። እረኞችም ተነግሯቸው እደነበረው ሁሉን ስለ ሰሙና ስለ አዩ እግዚአብሔርን እያከበሩና እያመሰገኑ ተመለሱ። ስምንት ቀን በሞላውና የመገረዣው ጊዜ ሲደርስ፥ ከመጸነሱ በፊት መልአኩ ባወጣለት ስሙ ኢየሱስ ተባለ። እንደ ሙሴም ሕግ የመንጻታቸው ወራት በተፈጸመ ጊዜ፥ በጌታ ፊት ሊያቀርቡት ወደ ኢየሩሳሌም አመጡት፤ እንዲህም የሆነው በጌታ ሕግ፦ “የእናቱን ማኅፀን የሚከፍት ወንድ ሁሉ ለጌታ የተቀደሰ ይባላል፤” ተብሎ ስለ ተጻፈ ነው፤ እንዲሁም በጌታ ሕግ እንደተባለው፦ “ሁለት ዋኖሶችን ወይም ሁለት የርግብ ጫጩቶችን” መሥዋዕት ለማቅረብ ወደ ኢየሩሳሌም መጡ። እነሆም፥ በኢየሩሳሌም ስምዖን የሚባል አንድ ሰው ነበረ፤ ይህም ሰው የእስራኤልን መጽናናት የሚጠብቅ፥ ጻድቅና ትጉህም ነበረ፤ መንፈስ ቅዱስም በእርሱ ላይ ነበረ። በጌታም የተቀባውን ሳያይ ሞትን እንደማያይ በመንፈስ ቅዱስ ተገልጦለት ነበር። በመንፈስም ተነሣስቶ ወደ መቅደስ መጣ፤ ወላጆቹም እንደ ሕጉ ልማድ ሊያደርጉለት ሕፃኑን ኢየሱስን በአስገቡት ጊዜ፥ እርሱ ደግሞ ተቀብሎ አቀፈው፤ እግዚአብሔርንም እየባረከ እንዲህ አለ፦ “ጌታ ሆይ! አሁን እንደ ቃልህ ባርያህን በሰላም ታሰናብተዋለህ፤ ዐይኖቼ ማዳንህን አይተዋልና፤ እርሱም በሰዎች ሁሉ ፊት ያዘጋጀኸው ነው፤ ይህም ለአሕዛብ ሁሉን የሚገልጥ ብርሃን፥ ለሕዝብህም ለእስራኤል ክብር ነው።” ዮሴፍና እናቱም ስለ እርሱ በተባሉት ነገሮች ይደነቁ ነበር። ስምዖንም ባረካቸው፤ እናቱን ማርያምንም እንዲህ አላት፦ “እነሆ፥ ይህ ሕፃን በእስራኤል ላሉት ለብዙዎች ለመውደቃቸውና ለመነሣታቸው፥ ለሚቃወሙትም ምልክት እንዲሆን ተሾሞአል፤ በዚህም የብዙዎችን የልባቸውን አሳብ የሚገለጥ ይሆናል፤ በአንቺም ደግሞ በነፍስሽ ሰይፍ ያልፋል።” ከአሴር ወገንም የሆነች የፋኑኤል ልጅ ሐና የምትባል አንዲት ነቢይት ነበረች፤ በዕድሜዋም በጣም የገፋች ነበረች፤ እርሷም ከድንግልናዋ ጀምራ ከባልዋ ጋር ሰባት ዓመት ኖረች፤ እርሷም እስከ ሰማኒያ አራት ዓመቷ ድረስ መበለት ነበረች፤ በጾምና በጸሎትም ሌሊትና ቀን እያገለገለች ከመቅደስ አትለይም ነበር። በዚያችም ሰዓት ቀርባ እግዚአብሔርን አመሰገነች፤ የኢየሩሳሌምንም ቤዛ ለሚጠባበቁ ሁሉ ስለ እርሱ ትናገር ነበር። ሁሉንም ነገር እንደ ጌታ ሕግ ከፈጸሙ በኋላ፥ ወደ ገሊላ ወደ ከተማቸው ወደ ናዝሬት ተመለሱ። ሕፃኑም አደገ ጠነከረም፤ ጥበብም ተሞላ፤ የእግዚአብሔርም ጸጋ በእርሱ ላይ ነበረ።