ሉቃስ 2:1-40
ሉቃስ 2:1-40 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
በዚያን ዘመን፣ የዓለሙ ሁሉ ሕዝብ እንዲቈጠርና እንዲመዘገብ ከአውግስጦስ ቄሳር ትእዛዝ ወጣ። ይህም ቄሬኔዎስ የሶርያ ገዥ በነበረበት ጊዜ የተደረገ የመጀመሪያው የሕዝብ ቈጠራ ነበር። ስለዚህ እያንዳንዱ ሰው ለመመዝገብ ወደየራሱ ከተማ ሄደ። ዮሴፍም ከዳዊት ቤትና ወገን ስለ ነበረ፣ በገሊላ አውራጃ ከምትገኘው ከናዝሬት ከተማ ተነሥቶ የዳዊት ከተማ ወደ ሆነችው፣ ቤተ ልሔም ወደምትባል ከተማ ወደ ይሁዳ ወጣ። ወደዚያም ለመመዝገብ የተጓዘው፣ የመውለጃ ጊዜዋ ከተቃረበው ከዕጮኛው ከማርያም ጋር ነበር። በዚያም እንዳሉ የምትወልድበት ጊዜ ደረሰ፤ የበኵር ልጇ የሆነውን ወንድ ልጅ ወለደች፤ በጨርቅም ጠቀለለችው፤ በእንግዶችም ማረፊያ ቦታ ስላላገኙ በግርግም አስተኛችው። በዚያው አገር በሌሊት መንጋቸውን ሲጠብቁ በሜዳ የሚያድሩ እረኞች ነበሩ። የጌታም መልአክ ድንገት መጥቶ በአጠገባቸው ቆመ፤ የጌታም ክብር በዙሪያቸው አበራ፤ ታላቅም ፍርሀት ያዛቸው። መልአኩ ግን እንዲህ አላቸው፤ “አትፍሩ፤ ለሕዝቡ ሁሉ የሚሆን ታላቅ ደስታ የምሥራች አምጥቼላችኋለሁና። ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኅን ተወልዶላችኋልና፤ እርሱም ጌታ ክርስቶስ ነው። ይህ ምልክት ይሁናችሁ፤ ሕፃን ልጅ በጨርቅ ተጠቅልሎ በግርግም ተኝቶ ታገኛላችሁ።” ድንገትም ብዙ የሰማይ ሰራዊት ከመልአኩ ጋር ታዩ፤ እግዚአብሔርንም እያመሰገኑ፣ እንዲህ አሉ፤ “ክብር ለእግዚአብሔር በአርያም፣ ሰላምም እርሱ ለሚወድዳቸው ሰዎች በምድር ይሁን!” መላእክቱ ከእነርሱ ተለይተው ወደ ሰማይ ከወጡ በኋላ እረኞቹ፣ “ጌታ የገለጠልንን ይህን የሆነውን ነገር እንድናይ ወደ ቤተ ልሔም እንሂድ” ተባባሉ። እነርሱም ፈጥነው ሄዱ፤ ማርያምንና ዮሴፍን፣ ሕፃኑንም በግርግም ተኝቶ አገኙ። ካዩም በኋላ፣ ስለ ሕፃኑ የተነገራቸውን ገልጠው አወሩ። ይህንም የሰሙ ሁሉ እረኞቹ በነገሯቸው ነገር ተደነቁ፤ ማርያም ግን ይህን ሁሉ በልቧ ይዛ ታሰላስል ነበር። እረኞቹም ሁሉም ነገር እንደ ተነገራቸው ሆኖ በማግኘታቸው፣ ስለ ሰሙትና ስላዩት ሁሉ እግዚአብሔርን እያከበሩና እያመሰገኑ ተመለሱ። ስምንት ቀን ሆኖት የመገረዣ ጊዜው ሲደርስ፣ ከመፀነሱ በፊት መልአኩ ባወጣለት ስም ኢየሱስ ተባለ። በሙሴ ሕግ መሠረት የመንጻታቸው ወቅት በተፈጸመ ጊዜ፣ ዮሴፍና ማርያም ሕፃኑን ለጌታ ለማቅረብ ወደ ኢየሩሳሌም ይዘውት ወጡ፤ ይኸውም በጌታ ሕግ፣ “ተባዕት የሆነ በኵር ሁሉ ለጌታ የተቀደሰ ይሆናል” ተብሎ እንደ ተጻፈ ለመፈጸምና ደግሞም በጌታ ሕግ፣ “ሁለት ዋኖሶች ወይም ሁለት የርግብ ጫጩቶች እንደ ተባለ፣” መሥዋዕት ለማቅረብ ነበር። በዚያን ጊዜ ጻድቅና ትጉህ የሆነ ስምዖን የሚባል አንድ ሰው በኢየሩሳሌም ይኖር ነበር፤ እርሱም የእስራኤልን መጽናናት የሚጠባበቅና መንፈስ ቅዱስ በላዩ ያደረ ሰው ነበር። ደግሞም የጌታን መሲሕ ሳያይ እንደማይሞት በመንፈስ ቅዱስ ተገልጦለት ነበር፤ እርሱም በዚህ ጊዜ በመንፈስ ተመርቶ ወደ ቤተ መቅደስ ገባ፤ የልጁም ወላጆች በሕጉ ልማድ መሠረት ተገቢውን ሊፈጽሙለት ሕፃኑን ኢየሱስን ይዘው በገቡ ጊዜ፣ ስምዖን ተቀብሎ ዐቀፈው፤ እግዚአብሔርን እያመሰገነ እንዲህ አለ፤ “ጌታ ሆይ፤ ቃል በገባኸው መሠረት፣ አሁን ባሪያህን በሰላም አሰናብተው፤ ዐይኖቼ በሰዎች ሁሉ ፊት ያዘጋጀኸውን፣ ማዳንህን አይተዋልና። ይህም ለአሕዛብ መገለጥን የሚሰጥ ብርሃን፣ ለሕዝብህ ለእስራኤልም ክብር ነው።” አባቱና እናቱም ስለ እርሱ በተነገረው ነገር ተገረሙ። ስምዖንም ባረካቸው፤ እናቱን ማርያምንም እንዲህ አላት፤ “ይህ ሕፃን በእስራኤል ለብዙዎች መነሣትና መውደቅ ምክንያት እንዲሆን፣ ደግሞም ክፉ ለሚያስወሩበት ምልክት እንዲሆን ተወስኗል፤ የብዙዎችም የልብ ሐሳብ የተገለጠ እንዲሆን፣ የአንቺም ነፍስ ደግሞ በሰይፍ ይወጋል።” ደግሞም ከአሴር ወገን የሆነች የፋኑኤል ልጅ፣ ሐና የምትባል ነቢይት በዚያ ነበረች፤ እርሷም በጣም አርጅታ ነበር፤ በድንግልናዋ ካገባችው ባሏም ጋር ሰባት ዓመት የኖረች ነበረች፤ ዕድሜዋም ሰማንያ አራት ዓመት እስኪሆናት ድረስ ቀንና ሌሊት ከቤተ መቅደስ ሳትለይ፣ በጾምና በጸሎት የምታገለግል መበለት ሆና ቈየች። በዚያኑም ጊዜ ቀርባ እግዚአብሔርን አመሰገነች፤ የኢየሩሳሌምንም መቤዠት ለሚጠባበቁ ሁሉ ስለ ሕፃኑ ተናገረች። ዮሴፍና ማርያም በጌታ ሕግ የታዘዘውን ሁሉ ከፈጸሙ በኋላ፣ በገሊላ አውራጃ ወዳለችው ከተማቸው ወደ ናዝሬት ተመለሱ። ሕፃኑም እያደገና እየጠነከረ ሄደ፤ በጥበብ ተሞላ፤ የእግዚአብሔርም ጸጋ በእርሱ ላይ ነበረ።
ሉቃስ 2:1-40 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
በዚያም ወራት እንዲህ ሆነ፤ ሰው ሁሉ ይቈጠር ዘንድ ከአውግስጦስ ቄሣር ትእዛዝ ወጣ። ቄሬኔዎስ ለሶርያ መስፍን በነበረ ጊዜ ይህ የመጀመርያ ቈጠራ ሆነ። ሰው ሁሉ ሊቈጠር ወደየከተማው ሄደ። ዮሴፍም ከገሊላ አውራጃ ከናዝሬት ከተማ ወደ ይሁዳ፥ ቤተ ልሔም ወደምትባለው ወደ ዳዊት ከተማ ወጣ፤ እርሱ ከዳዊት ሀገርና ከዘመዶቹም ወገን ነበርና። ፀንሳ ሳለች ከእጮኛው ከማርያም ጋር ይጻፍ ዘንድ ሄደ። በዚያ ሳሉም የምትወልድበት ቀን ደረሰ። የበኵር ልጅዋንም ወለደች፤ አውራ ጣቱንም አሰረችው፤ በጨርቅም ጠቀለለችው፤ በበረትም አስተኛችው፤ በማደርያቸው ቦታ አልነበራቸውምና። በዚያ ሀገር እረኞች ነበሩ፤ ሌሊቱንም ተግተው መንጋቸውን ይጠብቁ ነበር። እነሆም፥ የእግዚአብሔር መልአክ በአጠገባቸው ቆመ፤ የእግዚአብሔርም ብርሃን በዙሪያቸው አበራ፤ ታላቅ ፍርሀትንም ፈሩ። መልአኩም እንዲህ አላቸው፥ “እነሆ፥ ለእናንተና ለሕዝቡ ሁሉ ደስታ የሚሆን ታላቅ የምሥራች እነግራችኋለሁና አትፍሩ። እነሆ፥ ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኅን ተወልዶላችኋል፤ ይኸውም ቡሩክ ጌታ ክርስቶስ ነው። ለእናንተም ምልክቱ እንዲህ ነው፦ ሕፃን አውራ ጣቱን ታስሮ፥ በጨርቅም ተጠቅልሎ በበረት ውስጥ ተኝቶ ታገኛላቸሁ።” ድንገትም ከዚያ መልአክ ጋር ብዙ የሰማይ ሠራዊት እግዚአብሔርን እያመሰገኑ መጡ። “ክብር ለእግዚአብሔር በሰማያት፥ ሰላምም በምድር፥ ለሰው ልጅም በጎ ፈቃድ ሆነ” ይሉ ነበር። ከዚህም በኋላ መላእክት ከእነርሱ ዘንድ ወደ ሰማይ በዐረጉ ጊዜ እነዚያ እረኞች ሰዎች እርስ በርሳቸው፥ “እስከ ቤተ ልሔም እንሂድ፤ እግዚአብሔርም የገለጠልንን ይህን ነገር እንወቅ” አሉ። ፈጥነውም ሄዱ፤ ማርያምንና ዮሴፍን አገኙአቸው፤ ሕፃኑንም በበረት ውስጥ ተኝቶ አገኙት። በአዩም ጊዜ የነገሩአቸው ስለዚህ ሕፃን እንደ ሆነ ዐውቀው አወሩ። የሰሙትም ሁሉ እረኞቹ የነገሩአቸውን አደነቁ። ማርያም ግን ይህን ሁሉ ትጠብቀው፥ በልብዋም ታኖረው ነበር። እረኞችም እንደ ነገሩአቸው ባዩትና በሰሙት ሁሉ እግዚአብሔርን እያከበሩና እያመሰገኑ ተመለሱ። ስምንት ቀን በተፈጸመ ጊዜም ሕፃኑን ሊገዝሩት ወሰዱት፤ በማኅፀንዋ ሳትፀንሰው መልአኩ እንዳወጣለትም ስሙን ኢየሱስ አሉት። የመንጻታቸውም ወራት በተፈጸመ ጊዜ እንደ ሙሴ ሕግ በእግዚአብሔር ፊት ያቆሙት ዘንድ ወደ ኢየሩሳሌም ወሰዱት። “በኵር ሆኖ የሚወለድ ወንድ ልጅ ሁሉ ለእግዚአብሔር የተቀደሰ ይባላል” ተብሎ በእግዚአብሔር ሕግ እንደ ተጻፈ፥ በእግዚአብሔርም ሕግ እንደ ታዘዘ ሁለት ዋኖስ ወይም ሁለት የርግብ ግልገሎች ስለ እርሱ መሥዋዕት አድርገው ያቀርቡለት ዘንድ። በኢየሩሳሌምም ስሙ ስምዖን የሚባል አንድ ሰው ነበር፤ እርሱም ጻድቅና ደግ ሰው ነበር፤ እርሱም የእስራኤልን ደስታቸውን ያይ ዘንድ ተስፋ ያደርግ ነበር፤ መንፈስ ቅዱስም ያደረበት ነበር። የእግዚአብሔርንም መሲሕ ሳያይ እንደማይሞት መንፈስ ቅዱስ ገልጦለት ነበር። መንፈስም ወደ ቤተ መቅደስ ወሰደው፤ ዘመዶቹም በሕግ የተጻፈውን ያደርጉለት ዘንድ ሕፃኑን ጌታችን ኢየሱስን ወደ ቤተ መቅደስ በአገቡት ጊዜ፥ እርሱ ደግሞ ተቀብሎ በክንዱ ታቀፈው፤ እግዚአብሔርንም አመሰገነው። እንዲህም አለ፤ “አቤቱ፥ እንደ አዘዝህ ዛሬ ባርያህን በሰላም ታሰናብተዋለህ። ዐይኖች ትድግናህን አይተዋልና። በወገንህ ሁሉ ፊት ያዘጋጀኸውን፥ ለአሕዛብ ብርሃንን፥ ለወገንህ ለእስራኤልም ክብርን ትገልጥ ዘንድ።” ዮሴፍና እናቱ ግን በእርሱ ላይ ስለሚናገረው ያደንቁ ነበር። ስምዖንም ባረካቸው፤ እናቱን ማርያምንም እንዲህ አላት፤ “እነሆ፥ ይህ ሕፃን ከእስራኤል መካከል ለብዙዎች ለመውደቃቸውና ለመነሣታቸው፥ ለሚቃወሙትም ምልክት ይሆን ዘንድ የተሠየመ ነው፤ ባንቺ ግን በልብሽ ፍላጻ ይገባል፤ የብዙዎቹን ዐሳብ ይገልጥ ዘንድ።” ከአሴር ወገን የምትሆን የፋኑኤል ልጅ ሐና የምትባል ነቢይት ነበረች፤ አርጅታም ነበር፤ ከድንግልናዋም በኋላ ከባል ጋር ሰባት ዓመት ኖረች። ሰማንያ አራት ዓመትም መበለት ሆና ኖረች፤ በጾምና በጸሎትም እያገለገለች፥ ቀንም ሆነ ሌሊት ከቤተ መቅደስ አትወጣም ነበር። ያንጊዜም ተነሥታ እግዚአብሔርን አመሰገነች፤ የኢየሩሳሌምንም ድኅነት ተስፋ ለሚያደርጉ ሁሉ ስለ እርሱ ተናገረች። በእግዚአብሔርም ሕግ የተጻፈውን ሁሉ ከፈጸሙ በኋላ ወደ ገሊላ ወደ ከተማቸው ወደ ናዝሬት ተመለሱ። ሕፃኑም አደገ፤ በመንፈስም ጠነከረ፤ ጥበብንም የተመላ ነበር፤ የእግዚአብሔርም ጸጋ በእርሱ ላይ ነበረች።
ሉቃስ 2:1-40 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
በዚያም ወራት ዓለሙ ሁሉ እንዲጻፍ ከአውግስጦስ ቄሣር ትእዛዝ ወጣች። ቄሬኔዎስ በሶርያ አገር ገዥ በነበረ ጊዜ ይህ የመጀመሪያ ጽሕፈት ሆነ። ሁሉም እያንዳንዱ ይጻፍ ዘንድ ወደ ከተማው ሄደ። ዮሴፍም ደግሞ ከዳዊት ቤትና ወገን ስለ ነበረ ከገሊላ ከናዝሬት ከተማ ተነሥቶ ቤተ ልሔም ወደምትባል ወደ ዳዊት ከተማ ወደ ይሁዳ፥ ፀንሳ ከነበረች ከእጮኛው ከማርያም ጋር ይጻፍ ዘንድ ወጣ። በዚያም ሳሉ የመውለጃዋ ወራት ደረሰ፥ የበኵር ልጅዋንም ወለደች፥ በመጠቅለያም ጠቀለለችው፤ በእንግዶችም ማደሪያ ስፍራ ስላልነበራቸው በግርግም አስተኛችው። በዚያም ምድር መንጋቸውን በሌሊት ሲጠብቁ በሜዳ ያደሩ እረኞች ነበሩ። እነሆም፥ የጌታ መልአክ ወደ እነርሱ ቀረበ የጌታ ክብርም በዙሪያቸው አበራ፥ ታላቅ ፍርሃትም ፈሩ። መልአኩም እንዲህ አላቸው፦ እነሆ፥ ለሕዝቡ ሁሉ የሚሆን ታላቅ ደስታ የምሥራች እነግራችኋለሁና አትፍሩ፤ ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኃኒት እርሱም ክርስቶስ ጌታ የሆነ ተወልዶላችኋልና። ይህም ምልክት ይሆንላችኋል፤ ሕፃን ተጠቅልሎ በግርግምም ተኝቶ ታገኛላችሁ። ድንገትም ብዙ የሰማይ ሠራዊት ከመልአኩ ጋር ነበሩ። እግዚአብሔርንም እያመሰገኑ፦ ክብር ለእግዚአብሔር በአርያም ይሁን ሰላምም በምድር ለሰውም በጎ ፈቃድ አሉ። መላእክትም ከእነርሱ ተለይተው ወደ ሰማይ በወጡ ጊዜ፥ እረኞቹ እርስ በርሳቸው፦ እንግዲህ እስከ ቤተ ልሔም ድረስ እንሂድ እግዚአብሔርም የገለጠልንን ይህን የሆነውን ነገር እንይ ተባባሉ። ፈጥነውም መጡ ማርያምንና ዮሴፍን ሕፃኑንም በግርግም ተኝቶ አገኙ። አይተውም ስለዚህ ሕፃን የተነገረላቸውን ነገር ገለጡ። የሰሙትን ሁሉ እረኞቹ በነገሩአቸው ነገር አደነቁ፤ ማርያም ግን ይህን ነገር ሁሉ በልብዋ እያሰበች ትጠብቀው ነበር። እረኞችም እንደ ተባለላቸው ስለ ሰሙትና ስላዩት ሁሉ እግዚአብሔርን እያመሰገኑና እያከበሩ ተመለሱ። ሊገርዙት ስምንት ቀን በሞላ ጊዜ፥ በማኅፀን ሳይረገዝ በመልአኩ እንደ ተባለ፥ ስሙ ኢየሱስ ተብሎ ተጠራ። እንደ ሙሴም ሕግ የመንጻታቸው ወራት በተፈጸመ ጊዜ፥ በጌታ ሕግ፦ የእናቱን ማኅፀን የሚከፍት ወንድ ሁሉ ለጌታ የተቀደሰ ይባላል ተብሎ እንደ ተጻፈ በጌታ ፊት ሊያቆሙት፥ በጌታም ሕግ፦ ሁለት ዋሊያ ወይም ሁለት የርግብ ጫጩቶች እንደ ተባለ፥ መሥዋዕት ሊያቀርቡ ወደ ኢየሩሳሌም ወሰዱት። እነሆም፥ በኢየሩሳሌም ስምዖን የሚባል ሰው ነበረ፥ ይህም ሰው የእስራኤልን መጽናናት ይጠባበቅ ነበረ፤ ጻድቅና ትጉህም ነበረ፥ መንፈስ ቅዱስም በእርሱ ላይ ነበረ። በጌታም የተቀባውን ሳያይ ሞትን እንዳያይ በመንፈስ ቅዱስ ተረድቶ ነበር። በመንፈስም ወደ መቅደስ ወጣ፤ ወላጆቹም እንደ ሕጉ ልማድ ያደርጉለት ዘንድ ሕፃኑን ኢየሱስን በአስገቡት ጊዜ፥ እርሱ ደግሞ ተቀብሎ አቀፈው እግዚአብሔርንም እየባረከ እንዲህ አለ፦ ጌታ ሆይ፥ አሁን እንደ ቃልህ ባሪያህን በሰላም ታሰናብተዋለህ፤ ዓይኖቼ በሰዎች ሁሉ ፊት ያዘጋጀኸውን ማዳንህን አይተዋልና፤ ይህም ለአሕዛብ ሁሉን የሚገልጥ ብርሃን ለሕዝብህም ለእስራኤል ክብር ነው። ዮሴፍና እናቱም ስለ እርሱ በተባለው ነገር ይደነቁ ነበር። ስምዖንም ባረካቸው እናቱን ማርያምንም፦ እነሆ፥ የብዙዎች ልብ አሳብ ይገለጥ ዘንድ፥ ይህ በእስራኤል ላሉት ለብዙዎቹ ለመውደቃቸውና ለመነሣታቸው ለሚቃወሙትም ምልክት ተሾሞአል፥ በአንቺም ደግሞ በነፍስሽ ሰይፍ ያልፋል አላት። ከአሴር ወገንም የምትሆን የፋኑኤል ልጅ ሐና የምትባል አንዲት ነቢይት ነበረች፤ እርስዋም ከድንግልናዋ ጀምራ ከባልዋ ጋር ሰባት ዓመት ኖረች፤ እርስዋም ሰማኒያ አራት ዓመት ያህል መበለት ሆና በጣም አርጅታ ነበር፤ በጾምና በጸሎትም ሌሊትና ቀን እያገለገለች ከመቅደስ አትለይም ነበር። በዚያችም ሰዓት ቀርባ እግዚአብሔርን አመሰገነች፤ የኢየሩሳሌምንም ቤዛ ለሚጠባበቁ ሁሉ ስለ እርሱ ትናገር ነበር። ሁሉንም እንደ ጌታ ሕግ ከፈጸሙ በኋላ፥ ወደ ገሊላ ወደ ከተማቸው ወደ ናዝሬት ተመለሱ። ሕፃኑም አደገ፥ ጥበብም ሞልቶበት በመንፈስ ጠነከረ፤ የእግዚአብሔርም ጸጋ በእርሱ ላይ ነበረ።
ሉቃስ 2:1-40 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
በዚያን ጊዜ በሮማውያን ግዛት ያሉ ሰዎች ሁሉ እንዲቈጠሩ ከሮማው ንጉሠ ነገሥት አውግስጦስ ታወጀ። ይህም የመጀመሪያው የሕዝብ ቈጠራ በተደረገ ጊዜ ቄሬኔዎስ የሶርያ አገረ ገዥ ነበር። ስለዚህ እያንዳንዱ ሰው ስሙን ለማስመዝገብ ወደ ትውልድ አገሩ ይሄድ ነበር። ዮሴፍም በትውልዱ የዳዊት ዘር ስለ ነበረ በገሊላ ምድር ከምትገኘው ከናዝሬት ከተማ ተነሥቶ በይሁዳ ምድር ወደምትገኘው ወደ ዳዊት ከተማ፥ ወደ ቤተልሔም ሄደ፤ ሊመዘገብ የሄደውም ፀንሳ ከነበረችው ከእጮኛው ከማርያም ጋር ነበር። በቤተልሔም ከተማ ሳሉ ማርያም የመውለጃዋ ጊዜ ደረሰ። በዚያም የበኲር ልጅዋን ወለደች፤ በመታቀፊያ ጨርቅ ጠቀለለችው፤ በእንግዶች ማደሪያ ስፍራ ስላላገኙ በበረት በከብቶች መመገቢያ ግርግም ውስጥ አስተኛችው። በዚያም አካባቢ፥ በሜዳ ላይ ሌሊት መንጋቸውን እየጠበቁ የሚያድሩ እረኞች ነበሩ። እነሆ፥ ለእነርሱ የጌታ መልአክ ታያቸው፤ የጌታም የክብር ብርሃን በዙሪያቸው አበራ፤ እነርሱም በጣም ፈሩ፤ መልአኩ ግን እንዲህ አላቸው፦ “አትፍሩ! ለሕዝቡ ሁሉ ታላቅ ደስታ የሚሆን መልካም ዜና ይዤላችሁ መጥቻለሁ፤ እነሆ! ዛሬ በዳዊት ከተማ አዳኝ ተወልዶላችኋል፤ እርሱም ጌታ ክርስቶስ ነው። ምልክቱም ይህ ነው፤ በመታቀፊያ ጨርቅ የተጠቀለለ ሕፃን በበረት ውስጥ በግርግም ላይ ተኝቶ ታገኛላችሁ።” በድንገት ብዙ የሰማይ መላእክት ከመልአኩ ጋር አብረው ታዩ፤ እግዚአብሔርንም በማመስገን፥ “በሰማይ ለእግዚአብሔር ክብር ይሁን! በምድርም እግዚአብሔር ለሚወዳቸው ሰዎች ሁሉ ሰላም ይሁን!” ይሉ ነበር። መላእክቱ ተለይተዋቸው ወደ ሰማይ በወጡ ጊዜ እረኞቹ እርስ በርሳቸው፦ “እንግዲህ ወደ ቤተልሔም እንሂድ፤ አሁን የተፈጸመውንና ጌታ የገለጠልንን ነገር እንይ” ተባባሉ። በፍጥነት ሄደው ማርያምንና ዮሴፍን አገኙ፤ ሕፃኑንም በከብቶች መመገቢያ ግርግም ውስጥ ተኝቶ አዩት። ሕፃኑንም ካዩ በኋላ መልአኩ ስለ እርሱ የነገራቸውን አወሩ። ይህንንም የሰሙ ሁሉ እረኞቹ ባወሩላቸው ነገር ተደነቁ። ማርያም ግን፥ ይህን ሁሉ ነገር በልብዋ ይዛ ታሰላስለው ነበር። እረኞቹ፥ ሁሉ ነገር መልአኩ እንዳላቸው ሆኖ በማየታቸውና በመስማታቸው፥ እግዚአብሔርን እያከበሩና እያመሰገኑ፥ ወደ ስፍራቸው ተመለሱ። ከስምንት ቀን በኋላ ሕፃኑ በሚገረዝበት ሥነ ሥርዓት ላይ፥ ስሙ “ኢየሱስ” ተብሎ ተጠራ። ይህም ገና ከመፀነሱ በፊት መልአኩ ያወጣለት ስም ነው። በሕግ መሠረት፥ የመንጻት ሥርዓት የሚፈጸምበት ጊዜ ደረሰ፤ ስለዚህ ማርያምና ዮሴፍ ሕፃኑን በጌታ ፊት ለማቅረብ ወደ ኢየሩሳሌም ይዘውት ሄዱ። ይህንንም ያደረጉት በጌታ ሕግ “ወንድ የሆነ በኲር ልጅ ሁሉ ለጌታ ተሰጥቶ የተቀደሰ ይሆናል” የሚል ትእዛዝ ተጽፎ ስለ ነበር ነው። እንዲሁም በጌታ ሕግ “ሁለት ዋኖሶች ወይም ሁለት የርግብ ጫጩቶች ለመሥዋዕት ማቅረብ ይገባል” የሚል ትእዛዝ ነበረ። በዚያን ጊዜ በኢየሩሳሌም ስምዖን የሚባል አንድ ሰው ነበር፤ እርሱም ሕይወቱን ለእግዚአብሔር የሰጠ ጻድቅ ሰው ነበር፤ የእስራኤልን የመዳን ተስፋ ይጠባበቅ ነበር፤ መንፈስ ቅዱስም በእርሱ ላይ ነበር። እርሱ የጌታን መሲሕ ሳያይ እንደማይሞት መንፈስ ቅዱስ ገልጦለት ነበር። በዚያን ቀን መንፈስ ቅዱስ አነሣሥቶት ወደ ቤተ መቅደስ ሄደ፤ ዮሴፍና ማርያምም በሕጉ መሠረት የተለመደውን ሊፈጽሙለት ሕፃኑን ይዘው ወደ ቤተ መቅደስ በገቡ ጊዜ ስምዖን ሕፃኑን ተቀብሎ ዐቅፎ፥ እግዚአብሔርን በማመስገን እንዲህ አለ፤ “ጌታ ሆይ! እነሆ፥ የሰጠኸኝ የተስፋ ቃል ተፈጸመ፤ እንግዲህ አሁን እኔን አገልጋይህን በሰላም አሰናብተኝ፤ ማዳንህን በዐይኔ አይቻለሁ፤ እርሱም በአሕዛብ ሁሉ ፊት ያዘጋጀኸው ነው፤ እርሱ ለአሕዛብ እውነትን የሚገልጥ ብርሃን ይሆናል፤ ለሕዝብህም ለእስራኤል ክብር ነው።” ዮሴፍና ማርያም ስለ ሕፃኑ በተባለው ነገር ሁሉ ይደነቁ ነበር። ስምዖን ከባረካቸው በኋላ በተለይ የሕፃኑን እናት ማርያምን እንዲህ አላት፦ “እነሆ! ይህ ሕፃን በእስራኤል ውስጥ ለብዙዎቹ የመጥፋት፥ ለብዙዎቹ ግን የመዳን ምክንያት ይሆናል፤ እርሱም ብዙዎች የማይቀበሉት ምልክት ይሆናል። በዚህም በብዙዎች ልብ ያለው ስውር ሐሳብ ይገለጣል፤ የአንቺንም ልብ የሐዘን ሰይፍ ሰንጥቆት ያልፋል።” እንዲሁም በዚያን ጊዜ ከአሴር ነገድ የሆነች የፋኑኤል ልጅ ሐና የምትባል አንዲት ነቢይት ነበረች። በዕድሜዋም በጣም የገፋች ሴት ነበረች፤ ከባልዋ ጋር ሰባት ዓመት ከተቀመጠች በኋላ ባልዋ ሞተባት፤ ከዚህም በኋላ ዕድሜዋ ሰማኒያ አራት ዓመት እስኪሆን ድረስ ከቤተ መቅደስ ሳትለይ በጾምና በጸሎት ቀንና ሌሊት እግዚአብሔርን ታገለግል ነበር። በዚያኑ ጊዜ እርስዋም መጥታ ጌታን ታመሰግን ጀመር፤ ስለ ሕፃኑም የኢየሩሳሌምን መዳን በተስፋ ለሚጠባበቁ ሁሉ ትናገር ነበር። በጌታ ሕግ የታዘዘውን ሥርዓት ሁሉ ከፈጸሙ በኋላ በገሊላ ምድር ወደምትገኘው ወደ መኖሪያ ከተማቸው ወደ ናዝሬት ተመለሱ። ሕፃኑም እያደገና እየጠነከረ ሄደ፤ በጥበብም የተሞላ ሆነ፤ የእግዚአብሔርም ጸጋ ከእርሱ ጋር ነበረ።
ሉቃስ 2:1-40 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
በዚያም ወራት የመላው ዓለም ሕዝብ እንዲመዘገቡ ከአውግስጦስ ቄሣር ትእዛዝ ወጣ። ቄሬኔዎስ የሶርያ አገረ ገዥ በነበረ ጊዜ ይህ የመጀመሪያው ምዝገባ ተከናወነ። ስለዚህ ሁሉም ለመመዝገብ፥ እያንዳንዱም ወደ የራሱ ከተማ ሄደ። ዮሴፍም ደግሞ ከዳዊት ቤትና ወገን ስለ ነበረ፥ ከገሊላ ከናዝሬት ከተማ ተነሥቶ ቤተልሔም ወደምትባል ወደ ዳዊት ከተማ ወደ ይሁዳ፥ ፀንሳ ከነበረች ከእጮኛው ከማርያም ጋር ሊመዘገብ ሄደ። በዚያም ሳሉ የመውለጃዋ ወራት ደረሰ፤ የበኩር ልጇንም ወለደች፤ በመጠቅለያም ጠቀለለችው፤ በእንግዶችም ማደሪያ ስፍራ ስላልነበራቸው በግርግም አስተኛችው። በዚያም አካባቢ መንጋቸውን በሌሊት ሲጠብቁ በሜዳ ያደሩ እረኞች ነበሩ። እነሆም፥ የጌታ መልአክ ወደ እነርሱ ቀረበ፤ የጌታ ክብርም በዙሪያቸው አበራ፤ ታላቅ ፍርሃትም ፈሩ። መልአኩ ግን እንዲህ አላቸው፦ “እነሆ፥ ለሕዝቡ ሁሉ ታላቅ ደስታ የሚሆን የምሥራች እነግራችኋለሁና አትፍሩ፤ እነሆ! አዳኝ እርሱም ክርስቶስ ጌታ የሆነ ዛሬ በዳዊት ከተማ ተወልዶላችኋልና። ይህም ምልክት ይሆንላችኋል፤ ሕፃን ተጠቅልሎ በግርግምም ተኝቶ ታገኛላችሁ።” ድንገትም ብዙ የሰማይ ሠራዊት ከመልአኩ ጋር ነበሩ። እግዚአብሔርንም እያመሰገኑ፦ “ክብር ለእግዚአብሔር በአርያም ይሁን! ሰላምም ደስ በሚሰኝባቸው ሰዎች መካከል በምድር ይሁን!” አሉ። መላእክትም ከእነርሱ ተለይተው ወደ ሰማይ በወጡ ጊዜ፥ እረኞቹ እርስ በርሳቸው፦ “እንግዲህ እስከ ቤተልሔም ድረስ እንሂድ፤ ጌታም የገለጠልንን ይህን የሆነውን ነገር እንይ፤” ተባባሉ። ፈጥነውም ሄዱ፤ ማርያምንና ዮሴፍን ሕፃኑንም በግርግም ተኝቶ አገኙ። አይተውም ስለዚህ ሕፃን የተነገራቸውን ቃል ገለጡ። የሰሙትም ሁሉ እረኞቹ በነገሩአቸው ነገር ተደነቁ፤ ማርያም ግን ይህን ነገር ሁሉ በልብዋ እያሰላሰለች ትጠብቀው ነበር። እረኞችም ተነግሯቸው እደነበረው ሁሉን ስለ ሰሙና ስለ አዩ እግዚአብሔርን እያከበሩና እያመሰገኑ ተመለሱ። ስምንት ቀን በሞላውና የመገረዣው ጊዜ ሲደርስ፥ ከመጸነሱ በፊት መልአኩ ባወጣለት ስሙ ኢየሱስ ተባለ። እንደ ሙሴም ሕግ የመንጻታቸው ወራት በተፈጸመ ጊዜ፥ በጌታ ፊት ሊያቀርቡት ወደ ኢየሩሳሌም አመጡት፤ እንዲህም የሆነው በጌታ ሕግ፦ “የእናቱን ማኅፀን የሚከፍት ወንድ ሁሉ ለጌታ የተቀደሰ ይባላል፤” ተብሎ ስለ ተጻፈ ነው፤ እንዲሁም በጌታ ሕግ እንደተባለው፦ “ሁለት ዋኖሶችን ወይም ሁለት የርግብ ጫጩቶችን” መሥዋዕት ለማቅረብ ወደ ኢየሩሳሌም መጡ። እነሆም፥ በኢየሩሳሌም ስምዖን የሚባል አንድ ሰው ነበረ፤ ይህም ሰው የእስራኤልን መጽናናት የሚጠብቅ፥ ጻድቅና ትጉህም ነበረ፤ መንፈስ ቅዱስም በእርሱ ላይ ነበረ። በጌታም የተቀባውን ሳያይ ሞትን እንደማያይ በመንፈስ ቅዱስ ተገልጦለት ነበር። በመንፈስም ተነሣስቶ ወደ መቅደስ መጣ፤ ወላጆቹም እንደ ሕጉ ልማድ ሊያደርጉለት ሕፃኑን ኢየሱስን በአስገቡት ጊዜ፥ እርሱ ደግሞ ተቀብሎ አቀፈው፤ እግዚአብሔርንም እየባረከ እንዲህ አለ፦ “ጌታ ሆይ! አሁን እንደ ቃልህ ባርያህን በሰላም ታሰናብተዋለህ፤ ዐይኖቼ ማዳንህን አይተዋልና፤ እርሱም በሰዎች ሁሉ ፊት ያዘጋጀኸው ነው፤ ይህም ለአሕዛብ ሁሉን የሚገልጥ ብርሃን፥ ለሕዝብህም ለእስራኤል ክብር ነው።” ዮሴፍና እናቱም ስለ እርሱ በተባሉት ነገሮች ይደነቁ ነበር። ስምዖንም ባረካቸው፤ እናቱን ማርያምንም እንዲህ አላት፦ “እነሆ፥ ይህ ሕፃን በእስራኤል ላሉት ለብዙዎች ለመውደቃቸውና ለመነሣታቸው፥ ለሚቃወሙትም ምልክት እንዲሆን ተሾሞአል፤ በዚህም የብዙዎችን የልባቸውን አሳብ የሚገለጥ ይሆናል፤ በአንቺም ደግሞ በነፍስሽ ሰይፍ ያልፋል።” ከአሴር ወገንም የሆነች የፋኑኤል ልጅ ሐና የምትባል አንዲት ነቢይት ነበረች፤ በዕድሜዋም በጣም የገፋች ነበረች፤ እርሷም ከድንግልናዋ ጀምራ ከባልዋ ጋር ሰባት ዓመት ኖረች፤ እርሷም እስከ ሰማኒያ አራት ዓመቷ ድረስ መበለት ነበረች፤ በጾምና በጸሎትም ሌሊትና ቀን እያገለገለች ከመቅደስ አትለይም ነበር። በዚያችም ሰዓት ቀርባ እግዚአብሔርን አመሰገነች፤ የኢየሩሳሌምንም ቤዛ ለሚጠባበቁ ሁሉ ስለ እርሱ ትናገር ነበር። ሁሉንም ነገር እንደ ጌታ ሕግ ከፈጸሙ በኋላ፥ ወደ ገሊላ ወደ ከተማቸው ወደ ናዝሬት ተመለሱ። ሕፃኑም አደገ ጠነከረም፤ ጥበብም ተሞላ፤ የእግዚአብሔርም ጸጋ በእርሱ ላይ ነበረ።