ኦሪት ዘኍልቊ 15
15
ልዩ ልዩ ቁርባን
1ጌታም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ 2“ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ለእነርሱ ተናገር፦ ወደምሰጣችሁ ወደምትኖሩባት ምድር በገባችሁ ጊዜ፥ 3ስእለታችሁን ለመፈጸም፥ ወይም በፈቃዳችሁ፥ ወይም በበዓላችሁ፥ ለጌታ መዓዛው ያማረ ሽታ እንዲሆን ከበሬ ወይም ከበግ መንጋ የሚቃጠል መሥዋዕት ወይም መሥዋዕት የሚሆን በእሳት የሚቀርብ ቁርባን አድርጋችሁ ለጌታ ብታቀርቡ፥ 4ቁርባኑን ለማቅረብ የሚያመጣ ሰው የኢን መስፈሪያ አራተኛ እጅ በሆነ ዘይት የተለወሰ ከመስፈሪያው ከዐሥር እጅ አንድ እጅ የሆነ መልካም ዱቄትን የእህል ቁርባን አድርጎ ለጌታ ያቅርብ፤ 5የኢንም መስፈሪያ አራተኛ እጅ የወይን ጠጅ ለመጠጥ ቁርባን ከሚቃጠል መሥዋዕት ወይም ከሌላ መሥዋዕት ጋር ለእያንዳንዱ ጠቦት ታዘጋጃለህ። 6ለአንዱም አውራ በግ የኢን መስፈሪያ ሢሶ በሆነ ዘይት የተለወሰ ከመስፈሪያው ከዐሥር እጅ ሁለት እጅ የሆነ መልካም ዱቄት ለእህል ቁርባን እንዲሆን ታዘጋጃለህ፤ 7ለጌታም መዓዛው ያማረ ሽታ እንዲሆን የኢን መስፈሪያ ሢሶ የወይን ጠጅ ለመጠጥ ቁርባን ታቀርባለህ። 8ለሚቃጠልም መሥዋዕት ወይም ለሌላ መሥዋዕት ወይም ስእለትን ለመፈጸም ወይም ለአንድነት መሥዋዕት ወይፈንን ለጌታ ብታዘጋጅ፥ 9ከወይፈኑ ጋር የኢን መስፈሪያ ግማሽ በሆነ ዘይት የተለወሰ ከመስፈሪያው ከዐሥር እጅ ሦስት እጅ መልካም ዱቄት ለእህል ቁርባን ታቀርባለህ። 10ለጌታም መዓዛው ያማረ ሽታ እንዲሆን በእሳት የሚቀርብ ቁርባን አድርገህ፥ የኢን መስፈሪያ ግማሽ የወይን ጠጅ ለመጠጥ ቁርባን ታቀርባለህ።
11“ለእያንዳንዱም ወይፈን ወይም ለእያንዳንዱ አውራ በግ ወይም ለእያንዳንዱ ተባት የበግ ወይም የፍየል ጠቦት እንዲሁ ይደረጋል። 12እንዳዘጋጃችሁት ቍጥር መጠን፥ እንዲሁ እንደ ቁጥራቸው ለእያንዳንዱ ታደርጋላችሁ። 13የአገሩ ተወላጅ የሆነ ሁሉ ለጌታ መዓዛው ያማረ ሽታ እንዲሆን በእሳት የሚቀርበውን ቁርባን ባቀረበ ጊዜ እነዚህን ነገሮች እንዲሁ ያደርጋል። 14መጻተኛም ከእናንተ ጋር ቢቀመጥ፥ ወይም በትውልዳችሁ መካከል ማንም ሰው ቢኖር፥ ለጌታ መዓዛው ያማረ ሽታ እንዲሆን በእሳት የሚቀርበውን ቁርባን ቢያቀርብ፥ እናንተ እንደምታደርጉት እርሱ እንዲሁ ያደርጋል። 15ለእናንተና በእናንተ መካከል ለሚቀመጥ መጻተኛ ለጉባኤው ሁሉ አንድ ዓይነት ሥርዓት ይኑር፥ ለልጅ ልጃችሁም የዘለዓለም ሥርዓት ይሆናል፤ እናንተ እንደ ሆናችሁት መጻተኛውም በጌታ ፊት እንዲሁ ይሆናል። 16#ዘሌ. 24፥22።ለእናንተና ከእናንተ ጋር ለሚቀመጥ መጻተኛ አንድ ዓይነት ሕግና አንድ ዓይነት ፍርድ ይኑራችሁ።”
17ጌታም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ 18“ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ለእነርሱ ተናገር፦ ወደማመጣችሁ ምድር በገባችሁ ጊዜ፥ 19እናንተ የምድሪቱን እንጀራ በበላችሁ ጊዜ ለጌታ እንደ ልዩ ስጦታ የሚቀርበውን ቁርባን ታቀርባላችሁ። 20መጀመሪያ ከምታዘጋጁት ሊጥ አንድ እንጐቻ ልዩ ስጦታ የሆነ ቁርባን አድርጋችሁ ታቀርባላችሁ፤ ከአውድማውም እንደ ልዩ ስጦታ አድርጋችሁ እንደምታቀርቡት ቁርባን እንዲሁ ታቀርቡታላችሁ። 21መጀመሪያ ከምታዘጋጁት ሊጥ እንደ ስጦታ አድርጋችሁ የምታቀርቡትን ቁርባን እስከ ልጅ ልጃችሁ ለጌታ ትሰጣላችሁ።
22“ነገር ግን ስሕተት ባለማወቅ ብትፈጽሙ፥ ጌታም ለሙሴ ያዘዛቸውን እነዚህን ትእዛዛት ሁሉ ባታደርጉ፥ 23ጌታ ትዕዛዝን ከሰጠበት ቀን ጀምሮ ወደፊትም እስከ ልጅ ልጃችሁ ጌታ በሙሴ አንደበት ያዘዛችሁን ሁሉ ባታደርጉ፥ 24ይህንንም ነገር ማኅበሩ ሳያውቀው በስሕተት የተደረገ ቢሆን፥ ማኅበሩ ሁሉ ለሚቃጠል መሥዋዕት ከእህሉ ቁርባንና ከመጠጡ ቁርባን ጋር እንደ ሕጉ ለጌታ መዓዛው ያማረ ሽታ እንዲሆን አንድ ወይፈን፥ ለኃጢአትም መሥዋዕት አንድ አውራ ፍየል ያቅርብ። 25ካህኑም ለእስራኤል ልጆች ማኅበር ሁሉ ያስተሰርይላቸዋል፥ ባለማወቅ ስሕተት ፈጽመው ነበርና፥ ባለማወቅም ስለ ፈጸሙት ስሕተታቸው ለጌታ በእሳት የሚቀርበውን ቁርባናቸውን አምጥተዋልና፥ ማለማወቅም ስለ ፈጸሙት ስሕተታቸው የኃጢአታቸውን መሥዋዕት በጌታ ፊት አቅርበዋልና እነርሱ ይቅር ይባላሉ። 26ለእስራኤልም ልጆች ማኅበር ሁሉ፥ ሕዝቡም ሁሉ ባለማወቅ ይህ ስሕተት ፈጽመዋልና በመካከላቸውም ለሚኖሩት መጻተኞች ስርየት ይደረግላቸዋል።
27 #
ዘሌ. 4፥27-31። “አንድ ሰው ባለማወቅ ኃጢአት ቢሠራ፥ ለኃጢአት መሥዋዕት አንዲት የአንድ ዓመት እንስት ፍየል ያቀርባል። 28ባለማወቅም ኃጢአት ሠርቶ ስሕተትን ለፈጸመው ለዚያ ሰው እንዲያስተሰርይለት፥ ካህኑ በጌታ ፊት ማስተስሪያ ያደርጋል፤ እርሱም ይቅር ይባላል። 29ትውልዱ በእስራኤል ልጆች መካከል ቢሆን፥ ወይም በመካከላቸው የሚቀመጥ መጻተኛ ቢሆን፥ ባለማወቅ ኃጢአትን ለሚሠራ ሁሉ አንድ ዓይነት ሕግ ይኑራችሁ። 30ነገር ግን የአገሩ ተወላጅ ቢሆን ወይም መጻተኛ ቢሆን፥ በትዕቢት ማናቸውንም ነገሮች የሚያደርግ ሰው ጌታን ሰድቦአል፤ ያም ሰው ከሕዝቡ መካከል ተለይቶ ይጠፋል። 31የጌታን ቃል ስለ ናቀ፥ ትእዛዙንም ስላፈረሰ፥ ያ ሰው ፈጽሞ ይጥፋ፤ በደሉ በራሱ ላይ ነው።”
ሰንበትን በመተላለፍ የሚጣል ቅጣት
32የእስራኤልም ልጆች በምድረ በዳ ሳሉ አንድ ሰው በሰንበት ቀን እንጨት ሲለቅም አገኙ። 33እንጨትም ሲለቅም ያገኙት ሰዎች ወደ ሙሴና ወደ አሮን ወደ ማኅበሩም ሁሉ አመጡት። 34በእርሱም ላይ ምን ሊደረግበት እንደሚገባ ገና ግልጽ አልነበረምና በእስር ቤት አኖሩት። 35ጌታም ሙሴን እንዲህ አለው፦ “ሰውየው ፈጽሞ ይገደል፤ ከሰፈሩ ውጭ ማኅበሩ ሁሉ በድንጋይ ይውገሩት።” 36ማኅበሩም ሁሉ ከሰፈሩ ወደ ውጭ አውጡት፥ ጌታም ሙሴን እንዳዘዘው በድንጋይ ወግረው ገደሉት።
በለልብስ ጫፍ ላይ የሚደረግ ዘርፍ
37ጌታም ሙሴን እንዲህ አለው፦ 38#ዘዳ. 22፥12።“ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ተናገር፦ እነርሱም ትውልዶቻቸውም በልብሳቸው ጫፍ ዘርፍ እንዲያደርጉ፥ በዘርፉም ጫፍ ሁሉ ላይ ሰማያዊ ፈትል እንዲያኖሩበት እዘዛቸው። 39ዘርፉንም በልብሳችሁ ላይ አኑሩት እርሱንም በተመለከታችሁ ጊዜ የጌታን ትእዛዝ ሁሉ ታስታውሳላችሁ ታደርጉታላችሁም፥ ምኞታችሁንም በመከተል ያመነዘራችሁባትን የልባችሁንና የዐይኖቻችሁን ፈቃድ የማትከተሉ ትሆናላችሁ። 40ስለዚህ ትእዛዜን ሁሉ አስታውሱት አድርጉትም፥ ለአምላካችሁም ቅዱሳን ሁኑ። 41እኔ ጌታ አምላካችሁ ነኝ፤ አምላክ እንድሆናችሁ ከግብጽ ምድር ያወጣኋችሁ እኔ ጌታ አምላካችሁ ነኝ።”
Currently Selected:
ኦሪት ዘኍልቊ 15: መቅካእኤ
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ