የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

መዝሙረ ዳዊት 51

51
1ለመዘምራን አለቃ፥ የዳዊት መዝሙር። 2#2ሳሙ. 12።ወደ ቤርሳቤህ ከገባ በኋላ ነቢዩ ናታን ወደ እርሱ በመጣ ጊዜ፥
3አቤቱ፥ እንደ ቸርነትህ መጠን ማረኝ፥
እንደ ምሕረትህም ብዛት መተላለፌን ደምስስ።
4ከበደሌ ፈጽሞ እጠበኝ፥
ከኃጢአቴም አንጻኝ፥
5 # መዝ. 32፥5፤ 38፥19፤ ኢሳ. 59፥12። እኔ መተላለፌን አውቃለሁና፥
ኃጢአቴም ሁልጊዜ በፊቴ ነውና።
6 # ሮሜ 3፥4። አንተን ብቻ በደልሁ፥
በፊትህም ክፋትን አደረግሁ፥
በነገርህ ትጸድቅ ዘንድ በፍርድህም ንጹሕ ትሆን ዘንድ።
7 # ኢዮብ 14፥4። እነሆ፥ በዓመፃ ተወለድሁ፥
እናቴም በኃጢአት ፀነሰችኝ።
8እነሆ፥ እውነትን ወደድህ፥
የማይታይ ስውር ጥበብን አስታወቅኸኝ።
9 # ኢዮብ 9፥30፤ ኢሳ. 1፥18፤ ሕዝ. 36፥25። በሂሶጵ እርጨኝ፥ እነጻማለሁ፥
እጠበኝ፥ ከበረዶም ይልቅ ነጭ እሆናለሁ።
10ሐሤትንና ደስታን አሰማኝ፥
የሰበርሃቸውም አጥንቶቼ ደስ ይላቸዋል።
11ከኃጢአቴ ፊትህን መልስ፥
በደሌንም ሁሉ ደምስስልኝ።
12 # ሕዝ. 11፥19። አቤቱ፥ ንጹሕ ልብን ፍጠርልኝ፥
የቀናውንም መንፈስ በውስጤ አድስ።
13 # ጥበ. 1፥5፤ 9፥17፤ ኢሳ. 63፥11፤ ሐጌ 2፥5፤ ሮሜ 8፥9። ከፊትህ አትጣለኝ፥
ቅዱስ መንፈስህንም ከእኔ ላይ አትውሰድብኝ።
14የማዳንህን ደስታ መልስልኝ፥
በእሽታ መንፈስም ደግፈኝ።
15ለሕግ ተላላፎች መንገድህን አስተምራለሁ፥
ኃጢአተኞችም ወደ አንተ ይመለሳሉ።
16 # መዝ. 30፥10። የመድኃኒቴ አምላክ እግዚአብሔር ሆይ፥ ከደም አድነኝ፥
አንደበቴም በአንተ ጽድቅ ትደሰታለች።
17አቤቱ፥ ከንፈሮቼን ክፈት፥
አፌም ምስጋናህን ይናገራል።
18 # መዝ. 40፥7፤ 50፥8፤ አሞጽ 5፥21-22፤ ሆሴዕ 6፥6፤ ኢሳ. 1፥11-15፤ ዕብ. 10፥5-7። መሥዋዕትን ብትወድድስ በሰጠሁህ ነበር፥
የሚቃጠለውም መሥዋዕት ደስ አያሰኝህም።
19የእግዚአብሔር መሥዋዕት የተሰበረ መንፈስ ነው፥
የተሰበርውንና የተዋረደውን ልብ እግዚአብሔር አይንቅም።
20 # ኤር. 31፥4፤ ሕዝ. 36፥33። አቤቱ፥ በውዴታህ ጽዮንን አሰማምራት፥
የኢየሩሳሌምንም ቅጽሮች ሥራ።
21የጽድቁን መሥዋዕት
መባውንም የሚቃጠለውንም መሥዋዕት በወደድህ ጊዜ፥
ያንጊዜ በመሠዊያህ ላይ ፍሪዳዎችን ይሠዋሉ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ