መጽሐፈ ሳሙኤል ቀዳማዊ 17
17
ዳዊት ጎልያድን እንደ ገደለ
1ፍልስጥኤማውያንም ጭፍሮቻቸውን ለጦርነት ሰበሰቡ፤ ራሳቸውም በይሁዳ በሰኮት ተሰበሰቡ፤ በሰኮትና በዓዜቃ መካከል በኤፌርሜም#ዕብ. “በኤፌስደሜም” ይላል። ሰፈሩ። 2ሳኦልና የእስራኤል ሰዎችም ተሰበሰቡ፤ በኤላ ሸለቆም ሰፈሩ፤ ከፍልስጥኤማውያንም ጋር ሊዋጉ ተሰለፉ። 3ፍልስጥኤማውያንም በአንድ ወገን በተራራ ላይ ቆመው ነበር፥ እስራኤልም በሌላው ወገን በተራራ ላይ ቆመው ነበር፤ በመካከላቸውም ሸለቆ ነበረ። 4ከፍልስጥኤማውያንም ሰፈር የጌት ሰው ጎልያድ፥ ቁመቱም ስድስት ክንድ#ግሪክ ሰባ. ሊ. “አራት ክንድ” ይላል። ከስንዝር የሆነ፥ ኀይለኛ ሰው መጣ። 5በራሱም የናስ ቍር ደፍቶ ነበር፤ ጥሩርም ለብሶ ነበር፤ የጥሩሩም ሚዛን አምስት ሺህ ሰቅል ናስና ብረት ነበረ። 6በእግሮቹም ላይ የናስ ገምባሌ ነበረ፤ የናስም ጭሬ በትከሻው ላይ ነበረ። 7የጦሩም የቦ እንደ ሸማኔ መጠቅለያ ነበረ፤ የጦሩም ሚዛን ስድስት መቶ ሰቅል ብረት ነበረ፤ ጋሻ ጃግሬውም በፊቱ ይሄድ ነበር። 8እርሱም ቆሞ ወደ እስራኤል ጭፍሮች ጮኸ፥ “ከእኛ ጋር ትዋጉ ዘንድ ለምን ወጣችሁ? እኔ ፍልስጥኤማዊ አይደለሁምን? እናንተስ የሳኦል አገልጋዮች ዕብራውያን አይደላችሁምን? ከእናንተ አንድ ሰው ምረጡ፤ ወደ እኔም ይውረድ፤ 9ከእኔም ጋር ሊዋጋ ቢችል ቢገድለኝም፥ ባሪያዎች እንሆናችኋለን፤ እኔ ግን ባሸንፈው፥ ብገድለውም፥ እናንተ ባሪያዎች ትሆኑናላችሁ፤ ለእኛም ትገዛላችሁ” አለ። 10ፍልስጥኤማዊውም፥ “ዛሬ የእስራኤልን ጭፍሮች ተገዳደርኋቸው፤ አንድ ሰው ስጡኝ ሁለታችንም ለብቻችን እንዋጋ አልኋቸው” አለ። 11ሳኦልና እስራኤልም ሁሉ ይህን የፍልስጥኤማዊውን ቃል በሰሙ ጊዜ እጅግ ፈሩ፤ ደነገጡም።#ምዕ. 17 ቍ. 12-31 በግሪክ ሰባ. ሊ. የለም።
12ዳዊትም የዚያ የኤፍራታዊው ሰው ልጅ ነበረ፤ ያም ሰው ከቤተ ልሔም ይሁዳ ስሙም እሴይ ነበረ፤ ስምንት ልጆችም ነበሩት፤ እሴይም በሳኦል ዘመን በዕድሜ አርጅቶ ሸምግሎም ነበር። 13የእሴይም ሦስቱ ታላላቆች ልጆቹ ሳኦልን ተከትለው ወደ ሰልፉ ሄደው ነበር፤ ወደ ሰልፉም የሄዱት የሦስቱ ልጆች ስም ይህ ነበረ፤ ታላቁ ኤልያብ፥ ሁለተኛውም አሚናዳብ፥ ሦስተኛውም ሣማዕ ነበረ። 14ዳዊትም የሁሉ ታናሽ ነበረ፤ ሦስቱም ታላላቆቹ ሳኦልን ተከትለው ነበር። 15ዳዊትም የአባቱን በጎች ለመጠበቅ ከሳኦል ዘንድ ወደ ቤተ ልሔም ይመላለስ ነበር። 16ፍልስጥኤማዊውም ጥዋትና ማታ እየመጣ አርባ ቀን ይቆም ነበር።
17እሴይም ልጁን ዳዊትን እንዲህ አለው፥ “ከዚህ በሶ አንድ የኢፍ መስፈሪያ እነዚህንም ዐሥር እንጀራዎች ለወንድሞችህ ውሰድ፤ ወደ ሰፈሩም ፈጥነህ ሂድና ለወንድሞችህ ስጣቸው፤ 18ይህንም ዐሥሩን አይብ ወደ ሻለቃው ውሰደው፤ የወንድሞችህንም ደኅንነት ጠይቅ፤ ወሬአቸውንም አምጣልኝ።” 19ሳኦልና የእስራኤልም ሰዎች ሁሉ ከፍልስጥኤማውያን ጋር እየተዋጉ በኤላ ሸለቆ ነበሩ። 20ዳዊትም ማልዶ ተነሣ፤ በጎቹንም ለጠባቂ ተወ፤ እሴይም ያዘዘውን ይዞ ሄደ፤ ጭፍራውም ተሰልፎ ሲወጣ፥ ለሰልፍም ሲጮኽ በሰረገሎች ወደ ተከበበው ሰፈር መጣ። 21የእስራኤልና የፍልስጥኤማውያን ሠራዊትም ፊት ለፊት ተሰላልፈው ነበር። 22ዳዊትም ዕቃውን በዕቃ ጠባቂው እጅ አኖረው፤ ወደሚዋጉበትም ሮጦ ሄደ፤ የወንድሞቹንም ደኅንነት ጠየቀ። 23እርሱም ሲነጋገራቸው፥ እነሆ፥ ጎልያድ የተባለ ያ አርበኛ ፍልስጥኤማዊ የጌት ሰው ከፍልስጥኤማውያን ጭፍራ መካከል ወጣ፤ ቀድሞ የተናገረውንም ቃል ተናገረ፤ ዳዊትም ሰማ። 24የእስራኤልም ሰዎች ሁሉ ሰውዬውን ባዩ ጊዜ እጅግ ፈርተው ከፊቱ ሸሹ። 25የእስራኤልም ሰዎች፥ “ይህን የወጣውን ሰው አያችሁትን? በእውነት እስራኤልን ሊገዳደር ወጣ፤ የሚገድለውንም ሰው ንጉሡ እጅግ ባለጠጋ ያደርገዋል፤ ልጁንም ይድርለታል፤ ያባቱንም ቤተ ሰብ በእስራኤል ዘንድ ከግብር ነጻ ያወጣቸዋል” አሉ። 26ዳዊትም በአጠገቡ ለቆሙት ሰዎች፦ ይህን ፍልስጥኤማዊ ለሚገድል፥ ከእስራኤልም ተግዳሮትን ለሚያርቅ ሰው በውኑ ይህ ይደረግለታል? የሕያው አምላክን ጭፍሮች የሚገዳደር ይህ ያልተገረዘ ፍልስጥኤማዊ ማን ነው?” ብሎ ተናገራቸው። 27ሕዝቡም፥ “ለሚገድለው ሰው እንዲህ ይደረግለታል” ብለው እንደ ቀድሞው መለሱለት።
28ታላቅ ወንድሙም ኤልያብ ከሰዎች ጋር ሲነጋገር ሰማ፤ ኤልያብም በዳዊት ላይ እጅግ ተቈጣ፥ “ለምን ወደዚህ ወረድህ? እነዚያንስ ጥቂቶች በጎች በምድረ በዳ ለማን ተውሃቸው? እኔ ኵራትህንና የልብህን ክፋት አውቃለሁና ሰልፉን ለማየት መጥተሃል” አለው። 29ዳዊትም፥ “እኔ ምን አደረግሁ? ይህ ታላቅ ነገር አይደለምን?” አለ። 30ዳዊትም ከእርሱ ወደ ሌላ ሰው ዘወር አለ፤ እንደዚህም ያለ ነገር ተናገረ፤ ሕዝቡም እንደ ቀድሞው ያለ ነገር መለሱለት።
31ዳዊትም የተናገረው ቃል ተሰማ፤ ለሳኦልም ነገሩት፤ ወደ እርሱም ወሰደው። 32ዳዊትም ሳኦልን፥ “ስለ እርሱ የማንም ልብ አይውደቅ፤#ግሪክ ሰባ. ሊ. “የጌታዬ ንጉሥ ልቡ አይሸበር” ይላል። እኔ ባሪያህ ሄጄ ያን ፍልስጥኤማዊ እወጋዋለሁ” አለው። 33ሳኦልም ዳዊትን፥ “አንተ ገና ብላቴና ነህና፥ እርሱም ከብላቴንነቱ ጀምሮ ጦረኛ ነውና ይህን ፍልስጥኤማዊ ለመውጋት ትሄድ ዘንድ አትችልም” አለው። 34ዳዊትም ሳኦልን አለው፥ “እኔ ባሪያህ የአባቴን በጎች ስጠብቅ አንበሳ ወይም ድብ ይመጣ ነበር፤ ከመንጋውም ጠቦት ይወስድ ነበር። 35በኋላውም እከተለውና እመታው ነበር። ከአፉም አስጥለው ነበር፤ በተነሣብኝም ጊዜ ጕሮሮውን አንቄ እመታውና እገድለው ነበር። 36እኔ ባሪያህ አንበሳና ድብ ገደልሁ፤ ይህም ያልተገረዘው ፍልስጥኤማዊ ከእነርሱ እንደ አንዱ ይሆናል። እንግዲህ እገድለው ዘንድ፥ ከእስራኤልም ተግዳሮትን አስወግድ ዘንድ ዛሬ አልሄድምን? የሕያው አምላክ ጭፍሮችን ይገዳደር ዘንድ ይህ ቈላፍ ምንድን ነው?” 37ዳዊትም፥ “ከአንበሳና ከድብ እጅ ያስጣለኝ እግዚአብሔር ከዚህ ያልተገረዘ ፍልስጥኤማዊ እጅ ያስጥለኛል” አለ። ሳኦልም ዳዊትን፥ “ሂድ፤ እግዚአብሔርም ከአንተ ጋር ይሁን” አለው። 38ሳኦልም ለዳዊት ጥሩር አለበሰው፤ በራሱም ላይ የናስ ቍር ደፋለት። 39ዳዊትንም ሰይፉን በልብሱ ላይ አስታጠቀው፤ ዳዊትም አንድና ሁለት ጊዜ ሲራመድ ደከመ። ዳዊትም ሳኦልን፥ “አለመድሁምና በዚህ መሄድ አልችልም” አለው። ከላዩም አወለቁለት። 40ዳዊትም በትሩን በእጁ ያዘ፤ ከወንዝም አምስት ድብልብል ድንጋዮችን መረጠ፤ በእረኛ ኮሮጆውም በኪሱ ከተታቸው፤ ወንጭፍም በእጁ ነበረ፤ ወደ ፍልስጥኤማዊውም ቀረበ።
41ፍልስጥኤማዊውም መጥቶ ወደ ዳዊት ቀረበ፤ ጋሻ ጃግሬውም በፊቱ ይሄድ ነበር።#ምዕ. 17 ቍ. 41 በግሪክ ሰባ. ሊ. የለም። 42ጎልያድም ዳዊትን ትኩር ብሎ አየው፤ ቀይ ብላቴና፥ መልኩም ያማረ ነበረና ናቀው። 43ፍልስጥኤማዊውም ዳዊትን፥ “በትርና ድንጋይ ይዘህ የምትመጣብኝ እኔ ውሻ ነኝን?” አለው። ዳዊትም፥ “የለም ከውሻ ትከፋለህ”#“የለም ከውሻ ትከፋለህ” የሚለው በዕብ. የለም። አለው። ፍልስጥኤማዊውም ዳዊትን በአምላኮቹ ረገመው። 44ፍልስጥኤማዊውም ዳዊትን፥ “ወደ እኔ ና፤ ሥጋህንም ለሰማይ ወፎችና ለምድር አራዊት እሰጣቸዋለሁ” አለው። 45ዳዊትም ፍልስጥኤማዊዉን አለው፥ “አንተ ሰይፍና ጦር፥ ጋሻም ይዘህ ትመጣብኛለህ፤ እኔ ግን ዛሬ በተገዳደርኸው በእስራኤል ጭፍሮች አምላክ ስም በሰራዊት ጌታ በእግዚአብሔር ስም እመጣብሃለሁ። 46እግዚአብሔር ዛሬ አንተን በእጄ አሳልፎ ይሰጣል፤ እመታህማለሁ፤ ራስህንም ከአንተ እቈርጠዋለሁ፤ ሬሳህንና የፍልስጥኤማውያንንም ሠራዊት ሬሶች ለሰማይ ወፎችና ለምድር አራዊት ዛሬ እሰጣለሁ። ምድር ሁሉ እግዚአብሔር ከእስራኤል ጋር እንዳለ ያውቃሉ፤ 47ይህም ጉባኤ ሁሉ እግዚአብሔር በሰይፍና በጦር የሚያድን እንዳይደለ ያውቃል። ሰልፉ ለእግዚአብሔር ነውና፤ እግዚአብሔርም እናንተን በእጃችን አሳልፎ ይሰጣል።” 48ፍልስጥኤማዊውም ተነሥቶ ዳዊትን ሊገናኘው በቀረበ ጊዜ ዳዊት ፍልስጥኤማዊዉን ሊገናኘው ወደ ሰልፉ ሮጠ። 49ዳዊትም እጁን ወደ ኮሮጆው አግብቶ አንድ ድንጋይ ወሰደ፤ ወነጨፈውም፤ ፍልስጥኤማዊውንም ግንባሩን መታው፤ ድንጋዩም ጥሩሩን ዘልቆ በግንባሩ ተቀረቀረ፤ እርሱም በምድር ላይ በፊቱ ተደፋ።
50ዳዊትም ፍልስጥኤማዊውን በወንጭፍና በድንጋይ አሸነፈው፤ ፍልስጥኤማዊውንም መትቶ ገደለ ፤ በዳዊትም እጅ ሰይፍ አልነበረም።#ምዕ. 17 ቍ. 50 በግሪክ ሰባ. ሊ. የለም። 51ዳዊትም ሮጦ በፍልስጥኤማዊው ላይ ቆመ፤ ሰይፉንም ይዞ ከሰገባው መዘዘው፤ ገደለውም፤ ራሱንም ቈረጠው። ፍልስጥኤማውያንም ዋናቸው እንደ ሞተ ባዩ ጊዜ ሸሹ። 52የእስራኤልና የይሁዳ ሰዎችም ተነሥተው እልል አሉ፤ ፍልስጥኤማውያንንም እስከ ጌትና እስከ አስቀሎና በር ድረስ አሳደዱአቸው። የፍልስጥኤማውያንም በድኖቻቸው እስከ ጌትና እስከ አቃሮን በሮች ድረስ በመንገድ ላይ ወደቁ። 53የእስራኤልም ሰዎች ፍልስጥኤማውያንን ከማሳደድ ተመልሰው ሰፈራቸውን በዘበዙ። 54ዳዊትም የፍልስጥኤማዊውን ራስ ይዞ ወደ ኢየሩሳሌም አመጣው፤ ጋሻና ጦሩን ግን በድንኳኑ ውስጥ አኖረው።
55ሳኦልም ዳዊትን ፍልስጥኤማዊውን ሊዋጋ ሲወጣ ባየ ጊዜ ለሠራዊቱ አለቃ ለአቤኔር፥ “አቤኔር ሆይ፥ ይህ ብላቴና የማን ልጅ ነው?” አለው። አቤኔርም፥ “ንጉሥ ሆይ፥ በሕያው ነፍስህ እምላለሁ አላውቅም” አለ። 56ንጉሡም፥ “ይህ ብላቴና የማን ልጅ እንደ ሆነ አንተ ጠይቅና ዕወቅ” አለው። 57ዳዊትም ፍልስጥኤማዊውን ገድሎ በተመለሰ ጊዜ አቤኔር ወሰደው፤ ወደ ሳኦልም ፊት አመጣው፤ የፍልስጥኤማዊውንም ራስ በእጁ ይዞ ነበር። 58ሳኦልም፥ “አንተ ብላቴና የማን ልጅ ነህ?” አለው ዳዊትም፥ “እኔ የቤተ ልሔሙ የባሪያህ የእሴይ ልጅ ነኝ” ብሎ መለሰ።#ምዕ. 17 ቍ. 55-58 በግሪክ ሰባ. ሊ. የለም።
Currently Selected:
መጽሐፈ ሳሙኤል ቀዳማዊ 17: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ