መጽሐፈ ሳሙኤል ቀዳማዊ 18
18
ሳኦል በዳዊት እንደቀና
1እንዲህም ሆነ፤ ዳዊት ለሳኦል መንገሩን በፈጸመ ጊዜ የዮናታን ነፍስ በዳዊት ነፍስ ታሰረች፤ ዮናታንም እንደ ነፍሱ ወደደው። 2በዚያም ቀን ሳኦል ወሰደው፤ ወደ አባቱም ቤት ይመልሰው ዘንድ አልፈቀደለትም። 3ዮናታንም እንደ ነፍሱ ስለ ወደደው ዮናታንና ዳዊት ቃል ኪዳን አደረጉ። 4ዮናታንም የለበሰውን ካባ አውልቆ እርሱንና ልብሱን፥ ሰይፉንም፥ ቀስቱንም፥ ዝናሩንም ለዳዊት ሸለመው። 5ዳዊትም ሳኦል ወደ ላከው ሁሉ ይሄድ ነበር፤ አስተውሎም ያደርግ ነበር፤ ሳኦልም በጦረኞች ላይ ሾመው፤ ይህም በሕዝብ ሁሉ ዐይንና በሳኦል ባሪያዎች ዐይን መልካም ነበረ።
6እንዲህም ሆነ፤ ዳዊት ፍልስጥኤማዊውን ገድሎ በተመለሰ ጊዜ፥ እየዘመሩና እየዘፈኑ፥ እልልም እያሉ ከበሮና አታሞ ይዘው ዳዊትን#ዕብ. “ንጉሡን ሳኦልን ሊቀበሉ” ይላል። ሊቀበሉ ሴቶች ከእስራኤል ከተሞች ሁሉ ወጡ። 7ሴቶችም፥ “ሳኦል ሺህ ገደለ፤ ዳዊትም ዐሥር ሺህ ገደለ” እያሉ እየተቀባበሉ ይዘፍኑ ነበር። 8ሳኦልም እጅግ ተቈጣ፤ ይህም ነገር ሳኦልን አስከፋው፤ እርሱም፥ “ለዳዊት ዐሥር ሺህ ሰጡት፤ ለእኔ ግን ሺህ ብቻ ሰጡኝ፤ ከመንግሥት በቀር ምን ቀረበት?”#“ከመንግሥት በስተቀር ምን ቀረበት” የሚለው በግሪክ ሰባ. ሊ. የለም። አለ። 9ከዚያም ቀን ጀምሮ ሳኦል ዳዊትን ሁልጊዜ ይጠባበቀው ነበር።
10 # ምዕ. 18 ቍ. 10-11 በግሪክ ሰባ. ሊ. የለም። እንዲህም ሆነ፤ በነጋው ሳኦልን ክፉ መንፈስ ከእግዚአብሔር ዘንድ ያዘው፤ በቤቱም ውስጥ ትንቢት ተናገረ። ዳዊትም በየቀኑ ያደርግ እንደ ነበረ በእጁ በገና ይመታ ነበር። ሳኦልም ጦሩን በእጁ ይዞ ነበር። 11ሳኦልም፥ “ዳዊትን ከግንቡ ጋር አጣብቄ እመታዋለሁ” ብሎ ጦሩን ወረወረ። ዳዊትም ሁለት ጊዜ ከፊቱ ዘወር አለ። 12እግዚአብሔርም ከእርሱ ጋር ስለ ነበረ፥ ከሳኦልም ስለ ተለየ ሳኦል ከዳዊት ፊት የተነሣ ፈራ። 13ስለዚህም ሳኦል ከእርሱ አራቀው፤ የሺህ አለቃም አድርጎ ሾመው፤ በሕዝቡም ፊት ይወጣና ይገባ ነበር። 14ዳዊትም በአካሄዱ ሁሉ ብልህና ዐዋቂ ነበር፤ እግዚአብሔርም ከእርሱ ጋር ነበረ። 15ሳኦልም እጅግ ብልህ እንደ ሆነ አይቶ እጅግ ፈራው። 16ነገር ግን በፊታቸው ይወጣና ይገባ ስለነበረ እስራኤልና ይሁዳ ሁሉ ዳዊትን ወደዱ።
ዳዊት የሳኦልን ልጅ እንደ አገባ
17ሳኦልም ዳዊትን፥ “ታላቂቱ ልጄ ሜሮብ እነኋት፤ እርስዋን እድርልሃለሁ፤ ብቻ ጀግና ልጅ ሁንልኝ፤ ስለ እግዚአብሔርም ጦርነት ተጋደል” አለው። ሳኦልም፥ “የፍልስጥኤማውያን እጅ በእርሱ ላይ ትሁን እንጂ የእኔ እጅ በእርሱ ላይ አትሁን” ይል ነበር። 18ዳዊትም ሳኦልን፥ “ለንጉሥ አማች እሆን ዘንድ እኔ ማን ነኝ? ሰውነቴስ ምንድን ናት? የአባቴስ ወገን በእስራኤል ዘንድ ምንድን ነው?” አለው። 19ነገር ግን የሳኦል ልጅ ሜሮብ ዳዊትን የምታገባበት ጊዜ ሲደርስ ለሚሆላዊው ለአድርኤል ተዳረች። 20የሳኦልም ልጅ ሜልኮል ዳዊትን ወደደች፤ ይህም ወሬ ለሳኦል ደረሰለት፤ ነገሩም ደስ አሰኘው። 21ሳኦልም፥ “እርስዋን እሰጠዋለሁ፤ እርስዋም እንቅፋት ትሆንበታለች” አለ። እነሆም፥ የፍልስጥኤማውያን እጅ በሳኦል ላይ ነበረች።#ዕብ. “በእርሱ ላይ ትሆን ዘንድ እርስዋን እድርለታለሁ አለ ሳኦልም ዳዊትን ዛሬ ሁለተኛ አማች ትሆነኛለህ አለው” የሚል ይጨምራል።
22ሳኦልም ብላቴኖቹን፥ “እነሆ፥ ንጉሥ እጅግ ወድዶሃል፤ ቤተ ሰቡም ሁሉ ወድደውሃል፤ አሁንም ለንጉሥ አማች ሁን ብላችሁ በስውር ለዳዊት ንገሩት” ብሎ አዘዛቸው። 23የሳኦልም ብላቴኖች ይህን ቃል በዳዊት ጆሮ ተናገሩ፤ ዳዊትም፥ “እኔ የተዋረድሁና ክብር የሌለኝ ሰው ስሆን ለንጉሥ አማች እሆን ዘንድ ለእናንተ ትንሽ ነገር ይመስላችኋልን?” አለ። 24የሳኦልም ብላቴኖች፦ ዳዊት እንዲህ ብሎ ተናገረ ብለው ነገሩት። 25ሳኦልም አላቸው፥ “የንጉሥን ጠላቶች ይበቀል ዘንድ ከመቶ ፍልስጥኤማውያን ሸለፈት በቀር ንጉሥ ማጫ አይሻም ብላችሁ ለዳዊት ንገሩት” አላቸው። ሳኦል ግን ይህን ማለቱ በፍልስጥኤማውያን እጅ ይጥለው ዘንድ አስቦ ነው። 26የሳኦልም ብላቴኖች ይህን ቃል ለዳዊት ነገሩት፤ ለንጉሥም አማች ይሆን ዘንድ ዳዊትን ደስ አሰኘው። 27ዳዊትና ሰዎቹም ተነሥተው ሄዱ፤ ከፍልስጥኤማውያንም ሁለት መቶ#ግሪክ ሰባ. ሊ. “አንድ መቶ” ይላል። ሰዎችን ገደሉ፤ ዳዊትም ለንጉሥ አማች ይሆን ዘንድ ሰለባቸውን አምጥቶ በቍጥራቸው ልክ ለንጉሡ ሰጠ። ሳኦልም ልጁን ሜልኮልን ዳረለት። 28ሳኦልም እግዚአብሔር ከዳዊት ጋር እንደ ሆነ አየ፤ እስራኤልም ሁሉ ወደዱት። 29ሳኦልም ዳዊትን አጥብቆ ፈራው፤ ሳኦልም ዕድሜውን ሁሉ ለዳዊት ጠላት ሆነ። 30የፍልስጥኤማውያንም አለቆች ይወጡ ነበር፤ በወጡም ጊዜ ሁሉ ከሳኦል አገልጋዮች ሁሉ ይልቅ ዳዊት አስተውሎ ያደርግ ነበርና ስሙ እጅግ ተጠርቶ ነበር።
Currently Selected:
መጽሐፈ ሳሙኤል ቀዳማዊ 18: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ