መጽሐፈ ሳሙኤል ካልእ 1
1
ዳዊት የሳኦልንና የዮናታንን ሞት እንደ ሰማ
1እንዲህም ሆነ፤ ሳኦል ከሞተ በኋላ ዳዊት አማሌቃውያንን ከመግደል ተመለሰ፤ ዳዊትም በሴቄላቅ ሁለት ቀን ተቀመጠ። 2በሦስተኛውም ቀን፥ እነሆ፥ ከሰፈር ከሳኦል ወገን አንድ ሰው ልብሱን ቀድዶ፥ በራሱም ላይ ትቢያ ነስንሶ መጣ፤ ወደ ዳዊትም በመጣ ጊዜ በምድር ላይ ወድቆ ሰገደለት። 3ዳዊትም፥ “ከወዴት መጣህ?” አለው፤ እርሱም፥ “ከእስራኤል ሰፈር አምልጬ መጣሁ” አለው። 4ዳዊትም፥ “ነገሩ ምንድን ነው? እስኪ ንገረኝ” አለው። እርሱም መልሶ፥ “ሕዝቡ ከሰልፉ ሸሽቶአል፤ ከሕዝቡም ብዙው ወደቁ፤ ሞቱም፤ ሳኦልና ልጁ ዮናታንም ደግሞ ሞተዋል” አለው። 5ዳዊትም ወሬውን ያመጣለትን ጐልማሳ፥ “ሳኦልና ልጁ ዮናታን እንደ ሞቱ እንዴት ዐወቅህ?” አለው። 6ወሬውን ያመጣለት ጎልማሳም አለ፥ “በጌላቡሄ ተራራ ተዋግተው ወደቁ፤#ዕብ. “በድንገት ወደ ጌላቡሄ ተራራ መጣሁ” ይላል። እነሆም፥ ሳኦል በጦሩ ላይ ተኝቶ ነበር፤ ሰረገሎችና ፈረሰኞችም ተከትለው ደረሱበት። 7ወደ ኋላውም ዘወር አለና እኔን አይቶ ጠራኝ፤ እኔም፦ እነሆኝ አልሁ። 8እርሱም፦ አንተ ማን ነህ? አለኝ፤ እኔም አማሌቃዊ ነኝ ብዬ መለስሁለት። 9እርሱም፦ ክፉ ጨለማ ይዞኛልና#ዕብ. “ጨንቆኛልና” ይላል። ደግሞ እስካሁን ድረስ ነፍሴ ገና ፈጽማ ሕያውት ናትና በላዬ ቆመህ ግደለኝ አለኝ። 10እኔም ከወደቀ በኋላ አለመዳኑን አይቼ በላዩ ቆሜ ገደልሁት፤ በራሱም ላይ የነበረውን ዘውድ፥ በክንዱም የነበረውን ቢተዋ ወሰድሁ፤ ወደዚህም ወደ ጌታዬ አመጣሁት።”
11ዳዊትም ልብሱን ቀደደ፤ ከእርሱም ጋር የነበሩ ሰዎች ሁሉ ልብሳቸውን ቀደዱ። 12በጦር ወድቀዋልና ለሳኦልና ለልጁ ለዮናታን፥ ለይሁዳም ሕዝብ ለእስራኤልም ወገን እንባ እያፈሰሱ አለቀሱ፤ እስከ ማታም ድረስ ጾሙ። 13ዳዊትም ወሬውን ያመጣለትን ጐልማሳ፥ “አንተ ከወዴት ነህ?” አለው፤ እርሱም፥ “እኔ የመጻተኛው የአማሌቃዊው ልጅ ነኝ” ብሎ መለሰለት። 14ዳዊትም፥ “ትገድለው ዘንድ እግዚአብሔር በቀባው ላይ እጅህን ስትዘረጋ እንዴት አልፈራህም?” አለው። 15ዳዊትም ከብላቴኖቹ አንዱን ጠርቶ፥ “ሂድና ግደለው” አለው፤ ገደለውም። 16ዳዊትም፥ “እግዚአብሔር የቀባውን እኔ ገድያለሁ ብሎ አፍህ በላይህ መስክሮአልና ደምህ በራስህ ላይ ይሁን” አለው።
ዳዊት ስለ ሳኦልና ስለ ልጁ ዮናታን ሞት የተቀኘው ቅኔ
17ዳዊትም ስለ ሳኦልና ስለ ልጁ ዮናታን ይህን የኀዘን ቅኔ ተቀኘ፤ 18የይሁዳንም ልጆች ያስተምሩ ዘንድ አዘዘ። እነሆ ይህ በጻድቃን መጽሐፍ ተጽፎአል።
19“እስራኤል ሆይ፥ ለሞቱትና ለተገደሉት ሐውልት ትከል፤#ዕብ. “የእስራኤል ክብር በኮረብቶች ላይ ተወግቶ ሞተ” ይላል።
ኀያላን እንዴት ወደቁ!
20የፍልስጥኤማውያን ሴቶች ልጆች ደስ እንዳይላቸው፥
የቈላፋንም ሴቶች ልጆች እልል እንዳይሉ፥
በጌት ውስጥ አታውሩ፤
በአስቀሎናም አደባባይ የምስራች አትበሉ።
21እናንተ የጌላቡሄ ተራሮች ሆይ፥
ዝናብና ጠል አይውረድባችሁ፤
ቍርባንንም የሚያበቅል እርሻ አይሁንባችሁ።
የኀያላን ጋሻ በዚያ ወድቆአልና፤
የሳኦልም ጋሻ ዘይት አልተቀባምና።
22ከሞቱት ደምና ከኀያላን ስብ፥
የዮናታን ቀስት ባዶዋን አልተመለሰችም፤
የሳኦልም ሰይፍ ባዶዋን አልተመለሰችም።
23ሳኦልና ዮናታን የተወደዱና ያማሩ ነበሩ፤
በሕይወታቸውና በሞታቸው አልተለያዩም፤
ከንስር ይልቅ ፈጣኖች ነበሩ፤
ከአንበሳም ይልቅ ብርቱዎች ነበሩ።
24የእስራኤል ሴቶች ልጆች ሆይ፥
ቀይ ሐርና ጥሩ ግምጃ ያለብሳችሁ ለነበረ፥
በወርቀዘቦም ያስጌጣችሁ ለነበረ ለሳኦል አልቅሱለት።
25ኀያላን በሰልፍ ውስጥ እንዴት ወደቁ!
ዮናታን ሆይ፥ ሌሎችም የተመቱት በኮረብቶችህ ላይ ወደቁ።
26ወንድሜ ዮናታን ሆይ፥ እኔ ስለ አንተ እጨነቃለሁ፤
አንተ በእኔ ዘንድ እጅግ የተወደድህ ነበርህ፤
ከሴት ፍቅር ይልቅ ፍቅርህ ለእኔ ድንቅ ነበረ።
27ኀያላን እንዴት ወደቁ!
የሰልፍም ዕቃዎች እንዴት ጠፉ!”
Currently Selected:
መጽሐፈ ሳሙኤል ካልእ 1: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ