የሐዋርያት ሥራ 11
11
ጴጥሮስን ስለ ተቃወሙት ባልንጀሮች
1ሐዋርያትና በይሁዳ የነበሩ ወንድሞችም አሕዛብ የእግዚአብሔርን ቃል እንደ ተቀበሉ ሰሙ። 2ጴጥሮስም ወደ ኢየሩሳሌም በወጣ ጊዜ ከአይሁድ ወገን የሆኑት ወንድሞች ተቃወሙት። 3“ወደ አልተገረዙት ሰዎች ቤት ገብተህ አብረሃቸው በልተሃል” አሉት። 4ጴጥሮስም ከመጀመሪያ ጀምሮ ይነግራቸው ጀመረ፤ እንዲህም አላቸው። 5“በኢዮጴ ከተማ ሳለሁ ስጸልይ ተመስጦ መጣብኝና ራእይ አየሁ፤ ታላቅ መጋረጃ የመሰለ ዕቃ በአራቱ ማዕዘን ተይዞ ከሰማይ ወረደ፤ ወደ እኔም መጣ። 6በውስጡም አራት እግር ያላቸው እንስሳንና አራዊትን፥ ተንቀሳቃሾችንም፥ የሰማይ ወፎችንም አየሁ። 7‘ጴጥሮስ ሆይ፥ ተነሥና አርደህ ብላ’ የሚለኝንም ቃል ሰማሁ። 8‘አቤቱ፥ ከቶ አይሆንም፤ ንጹሕ ያልሆነ ርኩስ ነገር ወደ አፌ ገብቶ አያውቅም’ አልሁ። 9ደግሞም፦ ‘እግዚአብሔር ንጹሕ ያደረገውን አንተ አታርክሰው’ የሚል ቃል ከሰማይ መለሰልኝ። 10እንዲህም መላልሶ ሦስት ጊዜ ነገረኝ፤ ዳግመኛም ሁሉ ተጠቅልሎ ወደ ሰማይ ተመለሰ። 11በዚያችም ሰዓት ከቂሳርያ ወደ እኔ የተላኩ ሦስት ሰዎች መጡ፤ እኔ ባለሁበት ግቢ በርም ቆሙ። 12መንፈስ ቅዱስም፦ ‘ሳትጠራጠር አብረሃቸው ሂድ’ አለኝ፤ እነዚህ ስድስቱ ወንድሞቻችንም ተከትለውኝ መጡና ወደዚያ ሰው ቤት ገባን። 13እርሱም በቤቱ ቆሞ ሳለ የእግዚአብሔርን መልአክ እንዳየ ‘ወደ ኢዮጴ ከተማ ልከህ ጴጥሮስ የተባለውን ስምዖንን ይጥሩልህ። 14አንተና ቤተ ሰቦችህ ሁሉ የምትድኑበትን ነገር እርሱ ይነግርሃል’ እንደ አለው ነገረን። 15ላስተምራቸው በጀመርሁ ጊዜም ቀድሞ በእኛ ላይ እንደ ወረደ ሁሉ መንፈስ ቅዱስ በእነርሱም ላይ ወረደ። 16#የሐዋ. 1፥5። ‘ዮሐንስ በውኃ አጠመቀ፤ እናንተ ግን፤ በመንፈስ ቅዱስ ትጠመቃላችሁ’ ያለውን የጌታችንን ቃል ዐሰብሁ። 17እንግዲህ እግዚአብሔር በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ለአመንነው ለእኛ እንደ ሰጠን፥ ያን ጸጋውን እንደ እኛ አስተካክሎ ከሰጣቸው እግዚአብሔርን ልከለክል የምችል እኔ ማነኝ?” 18ይህንም በሰሙ ጊዜ ዝም አሉ፥ “እግዚአብሔር ለአሕዛብ ደግሞ ለሕይወት የሚሆን ንስሓን ሰጣቸው እንጃ” እያሉ እግዚአብሔርን አመሰገኑ።
በእስጢፋኖስ ሞት ስለ ተበተኑት ምእመናን
19 #
የሐዋ. 8፥1-4። በእስጢፋኖስ ሞት ምክንያት የተበተኑት ግን፤ ወደ ፊንቄ ወደ ቆጵሮስና ወደ አንጾኪያ ደረሱ፤ ቃሉንም ለአይሁድ ብቻ እንጂ ለአንድስ እንኳ አይናገሩም ነበር። 20ከመካከላቸውም ወደ አንጾኪያ ሄደው ለአረማውያን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ነገር ያስተማሩ የቆጵሮስና የቄሬና ሰዎች ነበሩ። 21የእግዚአብሔርም እጅ ከእነርሱ ጋር ነበረ፤ ወደ ጌታም ተመልሰው ያመኑ ሰዎች ቍጥራቸው በዛ።
22ስለ እነርሱ የተነገረውም ይህ ነገር በኢየሩሳሌም ባለችው ቤተ ክርስቲያን ዘንድ ተሰማ፤ በርናባስንም ወደ አንጾኪያ ላኩት። 23በደረሰ ጊዜም የእግዚአብሔርን ጸጋ አየና ደስ አለው፤ በፍጹም ልባቸውም በእግዚአብሔር ጸንተው ይኖሩ ዘንድ መከራቸው። 24ደግ ሰው፥ መንፈስ ቅዱስ ያደረበት፥ ሃይማኖተኛም ነበርና፤ በጌታችንም አምነው ብዙዎች አሕዛብ ተጨመሩ።
ደቀ መዛሙርት ክርስቲያን ስለ መባላቸው
25ከዚህም በኋላ በርናባስ ሳውልን ሊፈልግ ወደ ጠርሴስ ሄደ፤ በአገኘውም ጊዜ ወደ አንጾኪያ ወሰደው። 26በቤተ ክርስቲያንም አንድ ዓመት አብረው ተቀመጡ፤ ብዙ ሕዝብንም አስተማሩ፤ ደቀ መዛሙርትም መጀመሪያ በአንጾኪያ ክርስቲያን ተብለው ተጠሩ።
27ያንጊዜም ነቢያት ከኢየሩሳሌም ወደ አንጾኪያ ወረዱ። 28#የሐዋ. 21፥10። ከመካከላቸውም አጋቦስ የተባለ አንድ ሰው ተነሥቶ በዓለም ሁሉ ጽኑ ረኃብ እንደሚመጣ በመንፈስ ቅዱስ ተገልጦለት ተናገረ፤ ይህም በቄሣር ቀላውዴዎስ ዘመን ሆነ። 29ከዚህም በኋላ ደቀ መዛሙርት እያንዳንዳቸው የሚችሉትን ያህል አወጣጥተው በይሁዳ ሀገር ለሚኖሩት ወንድሞቻቸው ርዳታን ይልኩ ዘንድ ወሰኑ። 30እንደዚህም አድርገው በበርናባስና በሳውል እጅ ወደ ቀሳውስት ላኩት።
Currently Selected:
የሐዋርያት ሥራ 11: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ