መጽሐፈ ባሮክ 5
5
1ኢየሩሳሌም ሆይ! የኀዘንሽንና የመከራሽን ልብስ ከአንቺ አውልቂው፤ ለዘለዓለም ከእግዚአብሔር ያገኘሽውን የክብር ጌጥሽንም ልበሺ። 2ከእግዚአብሔር ዘንድ የጽድቅ መጐናጸፊያሽን ተጐናጸፊ፤ የዘለዓለማዊውን አምላክ የክብር ዘውድሽንም በራስሽ ላይ ተቀዳጂ። 3እግዚአብሔር ከሰማይ በታች ላሉ ሁሉ ብርሃንሽን ገልጧልና። 4ስምሽም በእግዚአብሔር ዘንድ ለዘለዓለም የጽድቅ ሰላምና እግዚአብሔርን የመፍራት ክብር ተብሎ ይጠራል።
5ኢየሩሳሌም ሆይ! ተነሥተሽ፥ በላይኛውም ቦታ ቁሚ፤ ወደ ምሥራቅም ተመልከቺ፤ ከምዕራብና ከምሥራቅም በቅዱሱ ቃል ልጆችሽ እንደ ተሰበሰቡ እዪ፤ እግዚአብሔርንም በማሰብ ደስ ይላቸዋል። 6ከአንቺም በእግር ወጡ፤ ጠላቶቻቸውም ወሰዷቸው፤ እግዚአብሔር ግን እንደ ንጉሥ ዙፋን በክብር ተሸክመው ወደ አንቺ እንዲያመጧቸው ያደርጋል።
7እግዚአብሔርም ረጃጅሞች ተራሮች ሁሉ ዝቅ ይሉ ዘንድ፥ ጐድጓዳውም ሁሉ ይሞላ ዘንድ፥ ምድርም ይስተካከል ዘንድ፥ እስራኤልም በእግዚአብሔር ክብር በጥርጊያው ጐዳና ይሄድ ዘንድ አዘዘ። 8እስራኤልን በእግዚአብሔር ትእዛዝ ዛፍ ሁሉ፥ በጎ መዓዛ ያለው ዕንጨትም ሁሉ ይጋርዳቸዋልና። 9እግዚአብሔር እስራኤልን በደስታና፥ በክብሩ ብርሃን፥ በምሕረቱና ከእርሱ በሆነች በጽድቁም ያመጣቸዋልና።
Currently Selected:
መጽሐፈ ባሮክ 5: አማ2000
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ