ትንቢተ ዳንኤል 13
13
ሶስና
1በባቢሎን የሚኖር ስሙ ኢዮአቄም የሚባል አንድ ሰው ነበረ። 2የኬልቅዩ ልጅ ስሟ ሶስና የምትባል ሚስት አግብቶ ነበር። እጅግም መልከ መልካምና እግዚአብሔርን የምትፈራ ነበረች። 3ወላጆችዋም ደጋግ ሰዎች ነበሩ። ለልጃቸውም የሙሴን ሕግ አስተምረዋት ነበር። 4ባሏ ኢዮአቄምም እጅግ ባለጸጋ ነበር፤ በቤቱም አጠገብ የተክል ቦታ ነበረው፤ ከሁሉ እርሱ ይከብር ነበርና አይሁድም ወደ እርሱ ይመጡ ነበር።
5ኀጢአት ከባቢሎን፥ ሕዝቡን እንጠብቃቸዋለን ከሚሉ ግብዞች መምህራንም እንደ ወጣች እግዚአብሔር ስለ እነርሱ የተናገረባቸው ሁለት ግብዞች መምህራን በዚያ ወራት በሕዝቡ መካከል ታዩ። 6እነርሱም በኢዮአቄም ቤት ያገለግሉ ነበር፥ የሚፈራረዱ ሰዎችም ሁሉ ወደ እርሱ#ግሪኩ “ወደ እነርሱ” ይላል። ይመጡ ነበር።
7ሕዝቡ ሁሉ ወደ ቤታቸው ከገቡ በኋላ ቀትር በሆነ ጊዜ ሶስና ወደ ባሏ ተክል ቦታ እየገባች በዚያ ትመላለስ ነበር። 8እነዚያም ሁለት መምህራንበዚያ እየገባች ስትመላለስ ሁልጊዜ ያይዋት ነበር። እርሷንም ተመኙአት። 9ልቡናቸውንም ለወጡ፤ ሰማይንም እንዳያዩ ዐይናቸውን ከደኑ፤ እውነተኛ ሕግንም አላሰቡም። 10ሁለቱም ሁሉ በፍቅሯ ተነደፉ፤ እርስ በርሳቸውም በልቡናቸው ያለውን ነገር አልተነጋገሩም። 11ምኞታቸውን መናገር አፍረዋልና። ከእርስዋም ጋር ይተኙ ዘንድ ይፈልጉ ነበር። 12ያገኝዋትም ዘንድ ሁልጊዜ ይጠብቋት ነበር።
13አንዱ ሁለተኛውን፥ “የምሣ ጊዜ ነውና ወደ ቤታችን እንግባ አለው፤” 14እየራሳቸውም ተለያይተው ሄዱ። ተመልሰውም በዚያ በአንድነት ተገናኙ፤ ሁለቱም ሁሉ ተያዩ፤ ያንጊዜም ምኞታቸውን ተነጋገሩ። እርስዋንም ብቻዋን የሚያገኙበትን ጊዜ ተቃጠሩ።
15ከዚህ በኋላ ቀን ሲጠብቋት ሶስና ሁልጊዜም ትገባ እንደ ነበር ከሁለቱ ደንገጥሮችዋ ጋር ገባች፤ አልቧትም ነበርና በተክል ቦታ ውስጥ ትታጠብ ዘንድ ወደደች። 16ተሰውረውም ከሚጠብቋት ከሁለቱ መምህራን በቀር በዚያ ማንም አልነበረም። 17ትታጠብም ዘንድ ደንገጥሮችዋን ሽቱና ዘይት እንዲያመጡና የተክሉን ቦታ በር እንዲዘጉ አዘዘቻቸው። 18እነርሱም እንዳዘዘቻቸው አደረጉ፤ የተክሉንም ቦታ በር ዘግተው ያዘዘቻቸውን ያመጡ ዘንድ በስርጥ ጎዳና ወጡ፤ የተሰወሩ እነዚያን መምህራን ግን አላዩአቸውም ነበር።
19እነዚያም ደንገጥሮች ከወጡ በኋላ ሁለቱ መምህራን ተነሥተው ወደ እርስዋ ሮጡ። 20“እነሆ የተክሉ ቦታ በር ተዘግትዋል፤ የሚያየንም የለም፤ ከአንቺ ጋር እንተኛ ዘንድ እንወዳለንና እሺ በዪን። 21ይህ ከአልሆነ ግን ከአንቺ ጋር ወንድ እንደ አገኘን ተናግረን እናጣላሻለን፤ ስለዚህም ነገር ደንገጥሮችሽን ከአንቺ አስወጥተሽ ሰደድሽ” አሏት።
22ሶስናም አለቀሰች፤ ”በሁሉም ፈጽሜ ተቸነፍሁ፤ ባደርገውም እሞታለሁ፤ ባላደርገውም አልድንም፤ ከእጃቸው ማምለጥንም አልችልም። 23በእግዚአብሔር ፊት ከምበድል ኀጢአት ሳልሠራ በእጃችሁ መውደቅ ይሻለኛል” አለች። 24ሶስናም ቃሏን አሰምታ ጮኸች፤ እነዚያም መምህራን ከእርሷ ጋር ጮኹ።
25አንዱም ሮጦ የተክሉን ቦታ በር ከፈተ። 26በቤትዋም ያሉ ሰዎች በተክል ቦታW መካከል ጩኸትን ሰምተው ወጡ፤ ምንም እንደ ሆነ ያዩ ዘንድ በሥርጥ ጎዳና ሮጡ። 27እነዚህም ሁለቱ መምህራን ይህን ነገር በተናገሩ ጊዜ በሶስና እንደዚህ ያለ ነገር ፈጽሞ ተሰምቶ አያውቅም ነበርና ዘመዶችዋና አገልጋዮችዋ እጅግ አፈሩ።
28በማግሥቱም ሕዝቡ በባሏ በኢዮአቄም ዘንድ በተሰበሰቡ ጊዜ እነዚያ ሁለት መምህራን ሶስናን ያስገድሏት ዘንድ ከአመፀኛ ልቡናቸው ጋር መጡ። 29“በሕዝቡ ሁሉ ፊት ያመጧት ዘንድ ወደ ኢዮአቄም ሚስት ወደ ሶስና ላኩ” አሉ ወደሷም ላኩባት። 30እርሷም ከእናትና ከአባትዋ፥ ከልጆችዋና ከዘመዶችዋም ሁሉ ጋር መጣች።
31ሶስናም እጅግ ደመ ግቡና መልከ መልካም ነበረች። 32እነዚያም ዐመፀኞች መምህራን መልኳን ለመጥገብ ክንብንቧን ይገልጧት ዘንድ አዘዙ፤ ክንብንቧንም ገለጧት። 33አባትዋና እናትዋ፥ ቤተ ሰቦችዋም፥ የሚያውቋትም ሰዎች ሁሉ አለቀሱላት።
34እነዚያም ሁለቱ መምህራን በሕዝቡ መካከል ተነሥተው እጆቻቸውን በራሷ ላይ አኖሩ። 35እሷ ግን ልቡናዋ በእግዚአብሔር አምኗልና እያለቀሰች ወደ ሰማይ ተመለከተች። 36እነዚያም መምህራን፥ “ብቻችንን በተክል ቦታ ውስጥ ስንመላለስ ይህች ሴት ከሁለቱ ደንገጥሮችዋ ጋር ገባች፤ ደንገጥሮችዋም ልካቸዋለችና የተክሉን ቦታ በር ዘግተው ሄዱ። 37ደንገጥሮችዋንም ከላከቻቸው በኋላ አንድ ጎልማሳ ከተሰወረበት መጥቶ ከእርስዋ ጋር ተኛ። 38እኛም በዚያ ተክል ቦታ ዳርቻ ሆነን ኀጢአታቸውን አየን፤ ወደ እነርሱም ሮጠን ሄድን፤ በአንድነትም ተኝተው አገኘናቸው። 39እኛም እርሱን መያዝ ተሳነን፤ እሱ በርትቶብናልና አመለጠን፤ የተክል ቦታውንም በር ከፍቶ ወጣ። 40እርስዋን ግን ያዝናት፤ ሰውየውም ማን እንደ ሆነ ጠየቅናት፤ ነገር ግን አልነገረችንም፤ ለዚህም ነገር እኛ ምስክሮች ነን” አሉ። 41የሕዝብ መምህራን ነበሩና ፈራጆችም ነበሩና በአደባባይ የተሰበሰቡ ሰዎች ነገራቸውን አመኗቸው፤ ትሞትም ዘንድ ፈረዱባት።
42ሶስናም ቃሏን አሰምታ ጮኸች፥ “ዘለዓለማዊ የሆንህ፥ የተሰወረውን የምታውቅ፥ ከመሆኑ በፊት ሁሉን የምታውቅ አምላክ ሆይ! 43በሐሰት እንደ መሰከሩብኝ አንተ ታውቃለህ፤ እነዚህ መምህራን ክፉ ነገርን ስለአደረጉብኝ የሠራሁት ነገር ሳይኖር እነሆ እሞታለሁ” አለች። 44እግዚአብሔርም ቃሏን ሰማት። 45ይገድሏትም ዘንድ ሲወስዷት እግዚአብሔር ስሙ ዳንኤል የሚባል የአንድ ወጣት ልጅ ልቡናን አነሣሣ።#ግሪክ ሰባ. ሊ. “ቅዱስ መንፈስን አነሣሣ” ይላል። 46እርሱም፥ “እኔ ከዚች ሴት ደም ንጹሕ ነኝ” ብሎ ቃሉን አሰምቶ ተናገረ።
47ሕዝቡም ሁሉ ወደ እርሱ ተመልሰው፥ “አንተ የምትናገረው ይህ ነገር ምንድን ነው?” አሉ። 48ዳንኤልም በመካከላቸው ቆሞ፥ “አላዋቂዎች የምትሆኑ እናንት የእስራኤል ልጆች! ሳትመረምሩ፥ ነገሩንም ሳትረዱ በእስራኤል ሴት ልጅ ላይ እንደዚህ ትፈርዳላችሁን? 49እነዚህ መምህራን በሐሰት መስክረውባታልና ወደ አደባባይ ተመለሱ” አላቸው። 50ሕዝቡም ሁሉ እየሮጡ ወደ አደባባይ ተመለሱ፤ አለቆችም ዳንኤልን፥ “እግዚአብሔር አንተን አልቆሃልና በመካከላችን ተቀምጠህ ንገረን” አሉት። 51ዳንኤልም፥ “እየራሳቸው አራርቃችሁ አቁሟቸው፤ እኔም ልመርምራቸው” አላቸው። 52እያንዳንዳቸውንም አራርቀው አቆሟቸው፤ እርሱም አንዱን ጠርቶ፥ “አንተ በክፋት ያረጀህ፥ ቀድሞ የሠራሃቸው ኀጢአቶችህ ደረሱብህ። 53የሐሰት ፍርድን ፈርደሃልና ጻድቁንና ንጹሑን አትግደል ብሎ እግዚአብሔር ቢከለክል በደለኛውን አዳንህ፤ ንጹሑንም ገደልህ። 54አሁንም ይህቺን ሴት ከአየሃት ሁለቱን ሁሉ በምን ዐይነት ዛፍ ሥር ሲጫወቱ አየህ? ንገረኝ” አለው “በኮክ ዛፍ ሥር ሲጫወቱ አየኋቸው” አለ።
55ዳንኤልም፥ “በእውነት ሐሰትን ተናገርህ፤ ደምህ በራስህ ላይ ነው፤ ከመካከልህ ይሰነጥቅህ ዘንድ የእግዚአብሔር መልአክ እነሆ፥ ከእግዚአብሔር ዘንድ ታዘዘ” አለው። 56እርሱንም እልፍ አደረገው፤ ሁለተኛውንም ያመጡት ዘንድ አዘዘ፤ አመጡትም፤ “አንተ የይሁዳ ዘር ያይደለህ የከነዓን ዘር ነህ፤ ውበት አሳተህ፤ ክፉ ፈቃድም ልቡናህን ገለበጠው። 57እርስዋ እናንተን መከራከር አልቻለችምና፥ የይሁዳ ሴት ልጅ እናንተን ፈርታለችና፥ ዐመፃችሁንም ታግሣለችና የእስራኤልን ሴት ልጅ እንዲህ ታደርጓታላችሁን። 58አሁንም ሁለቱ ሲጫወቱ ያየህበት ዛፍ ምንድን ነው? ንገረኝ” አለው። እርሱም፥ “ሮማን በሚባል ዛፍ ሥር አየኋት” አለው።
59ዳንኤልም፥ “አንተም በእውነት ሐሰትን ተናገርህ፤ ደምህም በራስህ ላይ ነው፤ በሰይፍ ከሁለት ይሰነጥቅህ ዘንድ፥ ፈጽሞም ያጠፋህ ዘንድ እነሆ የእግዚአብሔር መልአክ ይጠብቅሃል” አለው።
60ሕዝቡም ሁሉ ቃላቸውን አሰምተው ጮኹ፤ ያመነችበት፥ ሶስናን#ግሪክ ሰባ. ሊ. “የሚያምኑበትን ሁሉ የሚያድን እግዚአብሔርን ...” ይላል። ያዳናት እግዚአብሔርንም አመሰገኑ። 61ከቃላቸው የተነሣ ዳንኤል ነቅፏቸዋልና፥ ምስክርነታቸውንም ሐሰት አድርጎባቸዋልና በእነዚያ በሁለቱ መምህራን ላይ በጠላትነት ተነሡባቸው። 62እንደ ሙሴም ሕግ በባልንጀራቸው ላይ ክፉ እንደ አደረጉ በእነርሱም ላይ አደረጉባቸው። ገደሉአቸውም፤ በዚያችም ቀን ንጹሕ ደምን አዳኑ።
63በእርሷ ላይ ክፉ ሥራ አልተገኘምና ስለ ልጃቸው ስለ ሶስና ኬልቅዩና ሚስቱ ከባልዋ ከኢዮአቄምና ከዘመዶችዋ ሁሉ ጋር እግዚአብሔርን አመሰገኑት። 64ዳንኤልም ከዚያች ቀን ጀምሮ ሁልጊዜ በእግዚአብሔርና በሕዝቡ ፊት ገናና ሆነ።
Currently Selected:
ትንቢተ ዳንኤል 13: አማ2000
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ