ትንቢተ ዳንኤል 4
4
የናቡከደነፆር ሁለተኛው ሕልም
1ከንጉሡ ከናቡከደነፆር፤ በምድር ሁሉ ወደሚቀመጡ ወገኖችና አሕዛብ፥ በልዩ ልዩ ቋንቋም ወደሚናገሩ ሁሉ፥ “ሰላም ይብዛላችሁ። 2ልዑል አምላክ በፊቴ ያደረገውን ተአምራቱንና ድንቁን እነግራችሁ ዘንድ ወደድሁ። 3ተአምራቱ እንዴት ታላቅ ነው! ድንቁም እንዴት ጽኑ ነው! መንግሥቱም የዘለዓለም መንግሥት ነው፤ ግዛቱም ለልጅ ልጅ ነው።#ምዕ. 4 ከቍ. 1 እስከ 4 ያለው በግሪክ ሰባ. ሊ. የምዕ. 3 መጨረሻዎች ናቸው።
4“እኔ ናቡከደነፆር በቤቴ ደስ ብሎኝ በአዳራሼም ተመችቶኝ ነበር። 5ሕልም አለምሁ፤ እርስዋም አስፈራችኝ፤ በአልጋዬም ላይ ታወክሁ፤ የራሴም ራእይ አስጨነቀኝ። 6ስለዚህ የሕልሜን ፍቺ እንዲያስታውቁኝ የባቢሎን ጠቢባን ሁሉ ወደ እኔ ይገቡ ዘንድ አዘዝሁ። 7የዚያን ጊዜም የሕልም ተርጓሚዎቹና አስማተኞቹ፥ ከለዳውያኑና ቃላተኞቹ ገቡ፤ ሕልሜንም በፊታቸው ተናገርሁ፤ ፍቺውን ግን አላስታወቁኝም። 8በመጨረሻም የእግዚአብሔር ቅዱስ መንፈስ ያለበት እንደ አምላኬ ስም ብልጣሶር የሚባለው ዳንኤል በፊቴ ገባ፤ እኔም እንዲህ አልሁት፦ 9የጠቢባን አለቃ ብልጣሶር ሆይ! የእግዚአብሔር ቅዱስ መንፈስ በአንተ ውስጥ እንደ አለ፥ ከምሥጢርም ሁሉ የሚያስቸግርህ እንደሌለ ዐውቄአለሁና ያየሁትን የሕልሜን ራእይ፥ ፍቺውንም ንገረኝ። 10በአልጋዬ ላይ ራእይ አየሁ፤ እነሆ በምድር መካከል ዛፍ ነበረ፤ ቁመቱም እጅግ ረዥም ነበረ። 11ዛፉም ትልቅ ሆነ፤ በረታም፤ ቁመቱም እስከ ሰማይ ደረሰ፤ ቅርንጫፉም እስከ ምድር ሁሉ ዳርቻ ደረሰ። 12ቅጠሎቹም የተዋቡ ነበሩ፤ ፍሬውም ብዙ ነበረ፤ ሁሉም ከእርሱ ይመገብ ነበረ፤ ከጥላውም በታች የዱር አራዊት ያርፉበት ነበር፥ በቅርንጫፎቹም ውስጥ የሰማይ ወፎች ይቀመጡ ነበር፤ ሥጋ ለባሹም ሁሉ ከእርሱ ይበላ ነበር።
13“በአልጋዬም ላይ በሌሊት ራእይ አየሁ፤ እነሆም አንድ ቅዱስ ጠባቂ ከሰማይ ወረደ። 14በታላቅ ድምፅም እየጮኸ እንዲህ አለ፦ ዛፉን ቍረጡ፤ ቅርንጫፎቹንም ጨፍጭፉ፤ ቅጠሎቹንም አራግፉ፤ ፍሬውንም በትኑ፤ አራዊቱም ከበታቹ፥ ወፎቹም ከቅርንጫፉ ይታወኩ። 15ነገር ግን ሥሩንና ጉቶውን በምድር ውስጥ ተዉት፤ በመስክም ውስጥ በብረትና በናስ ማሰሪያ ታስሮ ይቈይ፤ በሰማይም ጠል ይረስርስ፤ እድል ፋንታውም በምድር ሣር ውስጥ ከአራዊት ጋር ይሁን። 16ልቡም ከሰው ልብ ይለወጥ፤ የአውሬም ልብ ይሰጠው፤ ሰባት ዘመናትም ይለፉበት። 17ልዑል እግዚአብሔር የሰዎችን መንግሥት እንዲገዛ፥ ለወደደውም እንዲሰጠው፥ ሕያዋን ያውቁ ዘንድ ይህ ነገር የጠባቂዎች ትእዛዝ፥ ይህም ፍርድ የቅዱሳን ቃል ነው፤ ሰውንም ትዕቢቱ ያዋርደዋል። 18እኔ ንጉሡ ናቡከደነፆር ያለምሁት ሕልም ይህ ነው፤ አንተም ብልጣሶር! ፍቺውን ንገረኝ፤ የመንግሥቴ ጠቢባን ሁሉ ፍቺውን ይነግሩኝ ዘንድ አልቻሉምና፤ ነገር ግን የእግዚአብሔር ቅዱስ መንፈስ በአንተ ውስጥ አለና አንተ ትችላለህ።”
ዳንኤል የንጉሡን ሕልም እንደ ተረጐመ
19ያን ጊዜም ብልጣሶር የተባለው ዳንኤል አንድ ሰዓት ያህል ዐሰበ፤ ልቡም ታወከ። ንጉሡም መልሶ፥ “ብልጣሶር ሆይ! ሕልሙና ፍቺው አያስቸግርህ” አለው።#“ንጉሡም መልሶ ብልጣሶር ሆይ ሕልሙና ፍቺው አያስቸግርህ አለው” የሚለው በዕብ. ብቻ። ብልጣሶርም መልሶ አለ፥ “ጌታዬ ሆይ! ሕልሙ ለሚጠሉህ፥ ፍቺውም ለጠላቶችህ ይሁን። 20ትልቅ የነበረው፥ የበረታውም፥ ቁመቱም እስከ ሰማይ የደረሰው፥ ቅርንጫፉም እስከ ምድር ሁሉ ድረስ የታየው፥ 21ቅጠሉም አምሮ የነበረው፤ ፍሬውም የበዛው፥ ለሁሉም መብል የነበረበት፥ በበታቹም የምድር አራዊት የተቀመጡ፥ በቅርንጫፎቹም የሰማይ ወፎች ያደሩበት፥ ያየኸው ዛፍ፥ 22ንጉሥ ሆይ! እርሱ ታላቅና ብርቱ የሆንህ አንተ ነህ፤ ታላቅነትህ በዝቶአል፤ እስከ ሰማይም ደርሶአል፤ ግዛትህም እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ ነው። 23ንጉሡም ከሰማይ የወረደውንና፦ ዛፉን ቍረጡ፥ አጥፉትም፤ ነገር ግን ጉቶውን በምድር ውስጥ ተዉት፤ በብረትና በናስ ማሰሪያ ታስሮ በመስክ ውስጥ ይቈይ፤ በሰማይም ጠል ይረስርስ፥ ሰባት ዘመናትም እስኪያልፉበት ድረስ እድል ፋንታው ከምድር አራዊት ጋር ይሁን ያለውን ቅዱስ ጠባቂ ማየቱ፥ 24ንጉሥ ሆይ! ፍቺው ይህ ነው፤ በጌታዬ በንጉሥ ላይ የወረደው የልዑሉ ትእዛዝ ነው፤ 25ልዑሉም የሰዎችን መንግሥት እንዲገዛ፥ ለሚወድደውም እንዲሰጠው እስክታውቅ ድረስ ከሰዎች ተለይተህ ትሰደዳለህ፤ መኖሪያህም ከምድር አራዊት ጋር ይሆናል፤ እንደ በሬም ሣር ትበላለህ፤ በሰማይም ጠል ትረሰርሳለህ፤ ሰባት ዘመናትም ያልፉብሃል። 26የዛፉንም ጉቶ ተዉት ማለቱ፥ ሥልጣን ከሰማያት እንደ ሆነ እስክታውቅ ድረስ መንግሥትህ ይቈይልሃል። 27ንጉሥ ሆይ! ስለዚህ ምናልባት የደኅንነትህ ዘመን ይረዝም እንደ ሆነ ምክሬ ደስ ያሰኝህ፤ በጽድቅና በምጽዋት ትድናለህ፤ በደልህንና ኀጢአትህንም ለድሆች በመራራት እግዚአብሔር ይቅር ይልሃል።”
ሕልሙ እንደ ደረሰ
28ይህ ሁሉ በንጉሡ በናቡከደነፆር ላይ ደረሰ። 29ከዐሥራ ሁለት ወር በኋላም በባቢሎን ቤተ መንግሥት ሰገነት ላይ ሲመላለስ፤ 30ንጉሡ፥ “ይህች እኔ በጕልበቴ ብርታት ለግርማዬ ክብር የመንግሥት መኖሪያ እንድትሆን ያሠራኋት ታላቂቱ ባቢሎን አይደለችምን?” ብሎ ተናገረ። 31ቃሉም ገና በንጉሡ አፍ ሳለ ድምፅ ከሰማይ መጣና፥ “ንጉሥ ናቡከደነፆር ሆይ! መንግሥት ከአንተ ዘንድ ዐለፈች ተብሎ ለአንተ ተነግሮአል፤ 32ልዑሉም የሰዎችን መንግሥት እንዲገዛ፥ ለሚወድደውም እንዲሰጠው እስክታውቅ ድረስ ከሰዎች ተለይተህ ትሰደዳለህ፤ መኖሪያህም ከምድር አራዊት ጋር ይሆናል፤ እንደ በሬም ሣር ትበላለህ፤#ዕብ. “ትበላ ዘንድ ትገደዳለህ” ይላል። ሰባት ዘመናትም ያልፉብሃል” አለው። 33በዚያም ሰዓት ነገሩ በናቡከደነፆር ላይ ደረሰ፤ ጠጕሩም እንደ አንበሳ፥ ጥፍሩም እንደ ንስር እስኪረዝም ድረስ ከሰዎች ተለይቶ ተሰደደ፤ እንደ በሬም ሣር በላ፤ አካሉም በሰማይ ጠል ረሰረሰ።
34ከእነዚያም ዘመናት በኋላ እኔ ናቡከደነፆር ዐይኔን ወደ ሰማይ አነሣሁ፤ አእምሮዬም ተመለሰልኝ፤ ልዑሉንም ባረክሁ፤ ለዘለዓለም የሚኖረውንም አመሰገንሁ፤ አከበርሁትም፤ ግዛቱ የዘለዓለም ግዛት ነውና፥ መንግሥቱም ለልጅ ልጅ ነውና። 35በምድርም የሚኖሩ ሁሉ እንደ ኢምንት ይቈጠራሉ፤ በሰማይም ሠራዊት በምድርም ላይ በሚኖሩ መካከል እንደ ፈቃዱ ያደርጋል፤ እጁንም የሚቃወማት ወይም፥ “ምን ታደርጋለህ?” የሚለው የለም። 36በዚያን ጊዜም አእምሮዬ ተመለሰልኝ፤ ወደ መንግሥቴም ክብር መጣሁ፤ ግርማዬና ውበቴም ወደ እኔ ተመለሰ፤ አማካሪዎችና መኳንንቶችም ፈለጉኝ፤ በመንግሥቴም ውስጥ ጸናሁ፤ ብዙም ክብር ተጨመረልኝ። 37አሁንም እኔ ናቡከደነፆር የሰማይን ንጉሥ አመሰግነዋለሁ፤ ከፍ ከፍም አደርገዋለሁ፥ አከብረውማለሁ። ሥራው ሁሉ እውነት፥ መንገዱም ቀና ነውና፤ በትዕቢትም የሚሄዱትን ያዋርድ ዘንድ ይችላልና።
Currently Selected:
ትንቢተ ዳንኤል 4: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ