ትንቢተ ዳንኤል 9
9
የዳንኤል ጸሎት
1በከለዳውያን መንግሥት ላይ በነገሠ፥ ከሜዶን ዘር በነበረ በአሕሻዊሮስ ልጅ በዳርዮስ በመጀመሪያው ዓመት፥ 2በነገሠ በመጀመሪያው ዓመት እኔ ዳንኤል በሰባ ዓመት የኢየሩሳሌም ጥፋት እንደሚፈጸም እግዚአብሔር በነቢዩ ኤርምያስ የተናገረው ቃል በተጻፈበት መጽሐፍ ያለውን የዘመኑን ቍጥር ዐወቅሁ።
3ማቅ ለብሼ፥ በአመድም ላይ ሆኜ ስጾም እጸልይና እለምን ዘንድ ፊቴን ወደ ጌታ ወደ አምላክ አቀናሁ። 4ወደ አምላኬም ወደ እግዚአብሔር ጸለይሁ፤ ተናዝዤም እንዲህ አልሁ፥ “ጌታ ሆይ! ከሚወድዱህና ትእዛዝህን ከሚፈጽሙ ጋር ቃል ኪዳንንና ምሕረትን የምትጠብቅ ታላቅና የምታስፈራ አምላክ ሆይ! 5ኀጢአትን ሠርተናል፥ በድለንማል፤ ክፋትንም አድርገናል፤ ዐምፀንማል፤ ከትእዛዝህና ከፍርድህም ፈቀቅ ብለናል፤ 6በስምህም ለነገሥታቶቻችንና ለአለቆቻችን፥ ለአባቶቻችንም፥ ለሀገሩም ሕዝብ ሁሉ የተናገሩትን ባሪያዎችህን ነቢያትን አልሰማንም። 7ጌታ ሆይ! ጽድቅ ለአንተ ነው፤ እንደ ዛሬም ለእኛ ለይሁዳ ሰዎችና በኢየሩሳሌም ለሚቀመጡ፥ ለእስራኤልም ሁሉ በቅርብና በሩቅም ላሉት አንተን በበደሉበት በበደላቸው ምክንያት በበተንህበት ሀገር ሁሉ የፊት እፍረት ነው። 8ጌታ ሆይ!#ግሪክ ሰባ. ሊ. “ጽድቃችን በአንተ ላይ ነው” የሚል ይጨምራል። በአንተ ላይ ኀጢአት ስለ ሠራን ለእኛና ለነገሥታቶቻችን፥ ለአለቆቻችንና ለአባቶቻችንም የፊት እፍረት ነው። 9ለጌታ ለአምላካችን ምሕረትና ይቅርታ ነው፤ በእርሱ ላይ ዐምፀናልና። 10በባሪያዎቹም በነቢያት እጅ በፊታችን በአኖረው በሕጉ እንሄድ ዘንድ የአምላካችንን የግዚአብሔርን ቃል አልሰማንምና። 11እስራኤልም ሁሉ ሕግህን ተላልፈዋል፤ ቃልህንም መስማትን እንቢ ብለዋል፤ በእርሱ ላይ ኀጢአት ሠርተናልና መርገምና በእግዚአብሔር ባሪያ በሙሴ ሕግ የተጻፈው መሐላ መጣብን። 12እጅግ ክፉ ነገርንም በእኛ ላይ በማምጣቱ በላያችንና በእኛ ዘንድ በተሾሙት ፈራጆቻችን ላይ የተናገረውን ቃል አጸና፤ በኢየሩሳሌምም ላይ እንደ ተደረገው ያለ ነገር ከቶ ከሰማይ ሁሉ በታች አልተደረገም። 13በሙሴም ሕግ እንደ ተጻፈ ይህ ክፉ ነገር ሁሉ መጣብን፤ ከኀጢአታችን እንመለስ፤ እውነትህንም እናስብ ዘንድ ወደ አምላካችን ወደ እግዚአብሔር ፊት አልለመንንም። 14ስለዚህም እግዚአብሔር ክፉ ነገርን በእኛ ላይ ፈጥኖ አመጣ፤ አምላካችን እግዚአብሔር በሚሠራው ሥራ ሁሉ ጻድቅ ነውና፤ እኛም ቃሉን አልሰማንምና። 15አሁንም ሕዝብህን ከግብፅ ምድር በበረታች እጅ ያወጣህ፥ እንደ ዛሬም ቀን ስምን ለአንተ ያደረግህ ጌታ አምላካችን ሆይ! ኀጢአትን ሠርተናል፤ ክፋትንም አድርገናል። 16ጌታ ሆይ! በፍጹም ቸርነትህ ቍጣህንና መቅሠፍትህን ከከተማህ ከኢየሩሳሌምና ከተቀደሰው ተራራህ መልስ፤ ስለ ኀጢአታችንና ስለ አባቶቻችን በደል ኢየሩሳሌምና ሕዝብህ በዙሪያችን ላሉት ሁሉ መሰደቢያ ሆነዋልና። 17አሁንም አምላካችን ሆይ! የባሪያህን ጸሎትና ልመናውን ስማ፤ ጌታ ሆይ! በፈረሰው በመቅደስህ ላይ ስለ አንተ ስትል ፊትህን አብራ። 18አምላኬ ሆይ! በፊትህ የምንለምን ስለ ብዙ ምሕረትህ ነው እንጂ ስለ ጽድቃችን አይደለምና ጆሮህን አዘንብለህ ስማ፤ ዐይንህንም ገልጠህ ጥፋታችንንና ስምህ የተጠራባትን ከተማ ተመልከት። 19አቤቱ! ስማ፤ አቤቱ፥ ይቅር በል፤ አቤቱ! አድምጥና አድርግ፤ አምላኬ ሆይ! ስምህ በከተማህና በሕዝብህ ላይ ተጠርቶአልና ስለ ራስህ አትዘግይ።”
20እኔም ገና ስናገርና ስጸልይ፥ በኀጢአቴና በሕዝቤም በእስራኤል ኀጢአት ስናዘዝ፥ በአምላኬም በእግዚአብሔር ፊት ስለ ተቀደሰው ስለ አምላኬ ተራራ ይቅርታን ስጠይቅ፥ 21ገናም በጸሎት ስናገር አስቀድሜ በራእይ አይችው የነበረው ሰው ገብርኤል እነሆ እየበረረ መጣ፤ በማታም መሥዋዕት ጊዜ ዳሰሰኝ። 22አስተማረኝም፤ ተናገረኝም፤ እንዲህም አለ፥ “ዳንኤል ሆይ! ጥበብንና ማስተዋልን እሰጥህ ዘንድ አሁን መጥቻለሁ። 23አንተ እጅግ የተወደድህ ሰው ነህና በልመናህ መጀመሪያ ላይ ቃል ወጥቶአል፤ እኔም እነግርህ ዘንድ መጥቻለሁ፤ አሁንም ነገሩን መርምር፤ ራእዩንም አስተውል።
24“ዐመፃን ይጨርስ፥ ኀጢአትንም ይፈጽም፥ በደልንም ያስተሰርይ፥ የዘለዓለምንም ጽድቅ ያገባ፥ ራእይንና ትንቢትን ያትም፥ ቅዱሰ ቅዱሳኑንም ይቀባ ዘንድ በሕዝብህና በቅድስት ከተማህ ላይ ሰባ ሱባዔ ተቀጥሮአል። 25ስለዚህ ዕወቅ፤ አስተውልም፤ ኢየሩሳሌምን መጠገንና መሥራት ትእዛዙ ከሚወጣበት ጀምሮ እስከ ንጉሥ ክርስቶስ ድረስ ሰባት ሱባዔና ስድሳ ሁለት ሱባዔ ይሆናል፤ ጎዳናዋና ቅጥርዋ ተመልሶ ይሠራል፤ ጊዜውም ይፈጸማል።#ዕብ. “እርስዋም በጭንቅ ዘመን ከጎዳናና ከቅጥር ጋር ትሠራለች” ይላል። 26ከስድሳ ሁለት ሱባዔ በኋላም መሢሕ ይገደላል፤ በእርሱም ዘንድ ፍትሕ የለም፤ ከሚመጣውም አለቃ ጋር ከተማዪቱንና መቅደሱን ያጠፋል፤ ፍጻሜውም በጎርፍ ይሆናል፤ እስከ መጨረሻም ድረስ ጦርነት ይሆናል፤ ጥፋትም ተቀጥሮአል። 27እርሱም ከብዙ ሰዎች ጋር ቃል ኪዳን ለአንድ ሱባዔ ያጸናል፤ በሱባዔውም እኩሌታ መሥዋዕቱንና ቍርባኑን ያስቀራል፤ በቤተ መቅደስም የጥፋት ርኵሰት ይሆናል፤ እስከ ዘመኑም ፍጻሜ የጥፋት መጨረሻ ይሆናል።”
Currently Selected:
ትንቢተ ዳንኤል 9: አማ2000
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ