ኦሪት ዘዳግም 27
27
በድንጋዮች ላይ የተጻፈ ሕግ
1ሙሴም የእስራኤልን ሽማግሌዎች እንዲህ ብሎ አዘዛቸው፥ “ዛሬ ያዘዝኋችሁን ትእዛዝ ታደርጉ ዘንድ ዕወቁ፤ 2አምላካችሁ እግዚአብሔር ወደሚሰጣችሁ ምድር ዮርዳኖስን በተሻገራችሁ ጊዜ ታላላቅ ድንጋዮችን ለእናንተ አቁሙ፤ በኖራም ምረጓቸው። 3የአባቶቻችሁ አምላክ እግዚአብሔር እንደ ተናገራችሁ፥#ዕብ. “ተስፋ እንደ ሰጠህ” ይላል። ወተትና ማር ወደምታፈስስ ምድር፥ አምላካችሁ እግዚአብሔር ወደሚሰጣችሁ ምድር ትገቡ ዘንድ በተሻገራችሁ ጊዜ፥ የዚህን ሕግ ቃሎች ሁሉ በድንጋዮች ላይ ጻፉ። 4ዮርዳኖስንም በተሻገራችሁ ጊዜ፥ ዛሬ እንዳዘዝኋችሁ፥ እነዚህን ድንጋዮች በጌባል ተራራ አቁሙ፤ በኖራም ምረጓቸው። 5በዚያም ለአምላክህ ለእግዚአብሔር መሠዊያ ሥራ፤ መሠዊያውም ብረት ካልነካው ድንጋይ ይሁን። 6ካልተጠረበም ድንጋይ ለአምላክህ ለእግዚአብሔር መሠዊያ ሥራ፤ ለአምላክህም ለእግዚአብሔር የሚቃጠለውን መሥዋዕትህን አቅርብበት፤ 7ለአምላክህ ለእግዚአብሔርም የደኅንነት መሥዋዕት ሠዋበት፤ በዚያም ብላ፤ ጥገብም፤ በአምላክህም በእግዚአብሔር ፊት ደስ ይበልህ። 8የዚህንም ሕግ ቃሎች ሁሉ የተገለጠ አድርገህ በድንጋዮቹ ላይ ጻፍ።”
9ሙሴና ሌዋውያን ካህናት ለእስራኤል ሁሉ እንዲህ ብለው ተናገሩ፥ “እስራኤል ሆይ፥ ዝም ብለህ አድምጥ፤ ዛሬ የአምላክህ የእግዚአብሔር ሕዝብ ሆነሃል። 10የአምላክህንም የእግዚአብሔርን ቃል ስማ፤ ዛሬም የማዝዝህን ትእዛዙንና ሥርዐቱን አድርግ።”
ዐሥራ ሁለት ርግማኖች
11ሙሴም በዚያ ቀን እንዲህ ብሎ ሕዝቡን አዘዘ፦ 12“ዮርዳኖስን በተሻገራችሁ ጊዜ ሕዝቡን ይባርኩ ዘንድ በገሪዛን ተራራ ላይ የሚቆሙ እነዚህ ናቸው፤ ስምዖንና ሌዊ፥ ይሁዳና ይሳኮር፥ ዮሴፍና ብንያም። 13ይረግሙም ዘንድ በጌባል ተራራ ላይ የሚቆሙ እነዚህ ናቸው፤ ሮቤልና ጋድ፥ አሴርና ዛብሎን፥ ዳንና ንፍታሌም። 14ሌዋውያንም ከፍ ባለች ድምፅ ለእስራኤል ሰዎች ሁሉ እንዲህ ብለው ይናገሩ።
15“በእግዚአብሔር ዘንድ የተጠላ የሠራተኛ እጅ ሥራን፥ የተቀረፀ ወይም ቀልጦ የተሠራ ምስልን የሚያደርግ፥ በስውርም የሚያቆመው ሰው ርጉም ይሁን፤ ሕዝቡም ሁሉ መልሰው አሜን ይላሉ።
16“አባቱን ወይም እናቱን የሚያቃልል ርጉም ይሁን፤ ሕዝቡም ሁሉ አሜን ይላሉ።
17“የባልንጀራውን የድንበር ምልክት የሚገፋ ርጉም ይሁን፤ ሕዝቡም ሁሉ አሜን ይላሉ።
18“ዕውሩን ከመንገድ ፈቀቅ የሚያደርግ ርጉም ይሁን፤ ሕዝቡም ሁሉ አሜን ይላሉ።
19“በመጻተኛ፥ በድሃ-አደጉም፥ በመበለቲቱም ላይ ፍርድን የሚያጣምም ርጉም ይሁን፤ ሕዝቡም ሁሉ አሜን ይላሉ።
20“ከእንጀራ እናቱ ጋር የሚተኛ የአባቱን ኀፍረት ገልጦአልና ርጉም ይሁን፤ ሕዝቡም ሁሉ አሜን ይላሉ።
21“ከእንስሳ ሁሉ የሚደርስ ርጉም ይሁን፤ ሕዝቡም ሁሉ አሜን ይላሉ።
22“ከአባቱ ወይም ከእናቱ ልጅ ከእኅቱ ጋር የሚተኛ ርጉም ይሁን፤ ሕዝቡም ሁሉ አሜን ይላሉ።
23“ከአማቱ ጋር የሚተኛ ርጉም ይሁን፤ ሕዝቡም ሁሉ አሜን ይላሉ። ከዋርሳው ጋር የሚተኛ#“ከዋርሳው ጋር የሚተኛ” የሚለው በግእዝ የለም። ርጉም ይሁን፤ ሕዝቡም ሁሉ አሜን ይሁን ይላሉ።
24“ባልንጀራውን በተንኰል የሚመታ ርጉም ይሁን፤ ሕዝቡም ሁሉ አሜን ይላሉ።
25“የንጹሑን ሰው ነፍስ ለመግደል ጉቦ የሚቀበል ርጉም ይሁን፤ ሕዝቡም ሁሉ አሜን ይላሉ።
26“የዚህን ሕግ ቃሎች ያደርግ ዘንድ የማያጸና ርጉም ይሁን፤ ሕዝቡም ሁሉ አሜን ይላሉ።
Currently Selected:
ኦሪት ዘዳግም 27: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ