ትንቢተ ሕዝቅኤል 19
19
የኀዘን መዝሙር
1“አንተም ለእስራኤል አለቃ ይህን ሙሾ አሙሽለት፤ 2እንዲህም በል፦ እናትህ ምን ነበረች? እንስት አንበሳ ነበረች፤ በአንበሶች መካከል ተጋደመች፤ በደቦል አንበሶችም መካከል ግልገሎችዋን አሳደገች። 3ከግልገሎችዋም አንዱን አወጣች፤ እርሱም ደቦል አንበሳ ሆነ፤ ንጥቂያንም ተማረ፤ ሰዎችንም ነጥቆ በላ። 4አሕዛብም ስለ እርሱ ሰሙ፤ እርሱም በጕድጓዳቸው ተያዘ፤ በሰንሰለትም አስረው ወደ ግብፅ ምድር ወሰዱት። 5እርስዋም ከእርስዋ እንደ ወሰዱት ባየች ጊዜ ኀይልዋ ጠፋ፤ ከግልገሎችዋም ሌላን ወስዳ ደቦል አንበሳ አደረገችው። 6እርሱም በአንበሶች መካከል አደገ፤ ደቦል አንበሳም ሆነ፤ ንጥቂያም ተማረ፤ ሰዎችንም ነጥቆ በላ። 7ተዘልሎም ይኖራል፤ ከተሞቻቸውንም አጠፋ፤ ሀገራቸውንም አፈረሰ፤ ከግሣቱም ድምፅ የተነሣ ምድርና ሞላዋ ጠፋች። 8አሕዛብም በዙሪያው ከየሀገሩ ሁሉ ተሰበሰቡበት፤ መረባቸውንም በእርሱ ላይ ዘረጉ፤ በወጥመዳቸውም ተያዘ። 9በሰንሰለትም አስረው በቀፎ ውስጥ አኖሩት፤ ወደ ባቢሎንም ንጉሥ አመጡት፤ ድምፁም በእስራኤል ተራሮች ላይ ከዚያ ወዲያ እንዳይሰማ ወደ ግዞት ቤት አገቡት።
10“እናትህ በውኃ አጠገብ እንደ ተተከለች እንደ ወይን ግንድና እንደ ጽጌረዳ ነበረች፤ ከውኃም ብዛት የተነሣ የምታፈራና የምትሰፋ ሆነች። 11ከእርስዋም የጸናች በትር ወጣች፤ ለገዥዎችም በትር ሆነች፤ በዛፎችም መካከል ቁመቷ ረዘመ፤ በቅርንጫፎችዋም ርዝመቷ ታየ። 12ነገር ግን በመዓት ተነቀለች፤ ወደ መሬትም ተጣለች፤ የሚያቃጥልም ነፋስ ፍሬዋን አደረቀ፤ ብርቱዎች በትሮችዋም ተሰበሩና ደረቁ፤ እሳትም በላቻቸው። 13አሁንም በምድረ በዳ፥ በደረቅና በተጠማች መሬት ተተከለች። 14ከተመረጡት ጫፎችዋም በትር እሳት ወጣች፤ ፍሬዋንም በላች፤ የነገሥታትም በትር ይሆን ዘንድ የበረታ በትር የለባትም።” ይህ ሙሾ ነው፤ ለልቅሶም ይሆናል።
Currently Selected:
ትንቢተ ሕዝቅኤል 19: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ