ትንቢተ ሕዝቅኤል 22
22
የኢየሩሳሌም ሕዝብ ኀጢአት
1የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ 2“አንተም የሰው ልጅ ሆይ! ደም በምታፈስስ ከተማ ላይ ትፈርዳለህን? ርኵሰቷን ሁሉ አስታውቃት። 3እንዲህም በላት፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ጊዜሽ እንዲደርስ በመካከልሽ ደምን የምታፈስሺ፥ እንድትረክሺም በራስሽ ላይ ጣዖታትን የምታደርጊ ከተማ ሆይ! 4ባፈሰስሽው ደም በድለሻል፤ ባደረግሻቸውም ጣዖታት ረክሰሻል፤ ቀንሽንም አቀረብሽ፤ ዘመንሽንም አሳጠርሽ፤ ስለዚህ ለአሕዛብ መሰደቢያ፥ ለሀገሮችም ሁሉ መሳለቂያ አደረግሁሽ። 5አንቺ ስምሽ የረከሰ፥ ኀጢአትም የሞላብሽ ሆይ! ወደ አንቺ የቀረቡና ከአንቺ የራቁ ይሳለቁብሻል።
6“እነሆ የእስራኤል ቤት አለቆች እያንዳንዳቸው ከዘመዶቻቸው ጋር#ዕብ. “እያንዳንዱ እንደ ችሎቱ” ይላል። ደም ያፈስሱ ዘንድ በአንቺ ውስጥ ተባበሩ። 7በአንቺ ውስጥ አባትንና እናትን አቃለሉ፤ በመካከልሽ በመጻተኛው ላይ በደልን አደረጉ፤ በአንቺ ውስጥ ድሀ አደጉንና መበለቲቱን አስጨነቁ። 8ቅድሳቴንም ናቁ፤ ሰንበታቴንም አረከሱ። 9በውስጥሽ ደምን ያፈስሱ ዘንድ ሌቦች ሰዎች በአንቺ ውስጥ ነበሩ፤ በአንቺ ውስጥ በተራሮች ላይ በሉ፤ በመካከልሽም የማይገባ ነገርን አደረጉ። 10በአንቺ ውስጥ የአባቶቻቸውን ኀፍረተ ሥጋ ገለጡ፤ በአንቺም ውስጥ አደፍ ያለባትን አዋረዱ። 11ሰውም ከባልንጀራው ሚስት ጋር ሰሰነ፤ አባትም የልጁን ሚስት በኀጢአት አረከሰ፤ በአንቺም ዘንድ ወንድም የአባቱን ልጅ እኅቱን አስነወረ። 12በአንቺ ውስጥ ደምን ያፈስሱ ዘንድ መማለጃን ተቀበሉ፤ በአንቺም አራጣና ትርፍ ወስደዋል፤ ቀማኛነትሽንና ኀጢአትሽን ፈጸምሽ፤ እኔንም ረሳሽኝ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
13“ስለዚህ እነሆ አንቺ ባደረግሽው ሥራ፥ በመካከልሽም በነበረው ደም ላይ በእጄ አጨበጨብሁ። 14እኔ በማደርግብሽ ወራት ልብሽ ይታገሣልን? ወይስ እጆችሽ ይጸናሉን? እኔ እግዚአብሔር ተናግሬአለሁ፤ አደርገውማለሁ። 15ወደ አሕዛብም እበትንሻለሁ፤ በሀገሮችም እዘራሻለሁ፤ ከአንቺም ርኵሰትሽ ይጠፋል። 16በአሕዛብም ፊት ከአንቺ እወርሳለሁ፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።”
17የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ 18“የሰው ልጅ ሆይ! የእስራኤል ቤት ሁሉ የተቀላቀሉ ናስና ቆርቆሮ፥ ብረትና እርሳስ ሆኑብኝ፤ በማጣሪያም መካከል የተቀላቀለ ብር ሆኑ። 19ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ሁላችሁ አተላ ሆናችኋልና ስለዚህ እነሆ በኢየሩሳሌም ውስጥ እሰበስባችኋለሁ። 20እንዲያቀልጡት እሳት ያናፉበት ዘንድ ብርንና መዳብን፥ ብረትንና እርሳስን፥ ቆርቆሮንም በከውር እንደሚሰበስቡ፥ እንዲሁ በቍጣዬና በመዓቴ እሰበስባችኋለሁ፤ በዚያም ውስጥ እጨምራችኋለሁ፤ አቀልጣችሁማለሁ። 21በላያችሁ የመዓቴን እሳት አነድድባችኋለሁ፤ በመካከሉም ትቀልጣላችሁ። 22ብርም በከውር ውስጥ እንደሚቀልጥ፥ እንዲሁ በውስጥዋ ትቀልጣላችሁ፤ እኔም እግዚአብሔር መዓቴን እንዳፈሰስሁባችሁ ታውቃላችሁ።”
የእስራኤል መሪዎች በደል
23የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ 24“የሰው ልጅ ሆይ! አንቺ ዝናም የማይዘንብብሽ፥ በቍጣ ቀን ጠል የማይወርድብሽ ምድር ነሽ በላት። 25በመካከሏ ያሉ ነቢያት እንደ አንበሳ ያገሳሉ፤ ይነጥቃሉ፤ ፈጽመውም ይቀማሉ፤ ሰውነትንም ያጠፋሉ፤ መማለጃንም ይቀበላሉ፤ በመካከልዋም መበለቶችዋ ይበዛሉ። 26ካህናቷም ሕጌን ጣሱ፤ በመቅደሴም መካከል ቅድሳቴን አረከሱ፤ ከርኵሰትም አልራቁም፤ በንጹሕና በርኩስ መካከል ያለውንም ልዩነት አላወቁም፤ ዐይናቸውንም ከሰንበታቴ ሸፈኑ፤ እኔም በመካከላቸው ረከስሁ። 27በውስጥዋ ያሉ አለቆችዋ የስስትን ትርፍ ለማግኘት ሲሉ ደምን ያፈስሱ ዘንድ፥ ነፍሶችንም ያጠፉ ዘንድ እንደሚናጠቁ ተኵላዎች ናቸው። 28ነቢያቶቻቸውም ይቀቡአቸዋል፤ ከንቱ ነገርንም ያዩላቸዋል፤ እግዚአብሔር እንዲህ አለ እያሉም በሐሰት ያምዋርቱላቸዋል፤ እግዚአብሔር ግን አልነገራቸውም። 29የምድር ሕዝብ ግፍን አደረጉ፤ ቅሚያንም ሠሩ፤ ድሆችንና ችግረኞችን አስጨነቁ፤ ለመጻተኛውም አልፈረዱለትም። 30ቅጥርን የሚጠግንን፥ ምድሪቱንም እንዳላጠፋት በፈረሰበት በኩል በፊቴ የሚቆምላትን ሰው ከእነርሱ መካከል ፈለግሁ፤ ነገር ግን አላገኘሁም። 31ስለዚህ ቍጣዬን አፈሰስሁባቸው፤ በመዓቴም እሳት አጠፋኋቸው፤ መንገዳቸውንም በራሳቸው ላይ መለስሁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።”
Currently Selected:
ትንቢተ ሕዝቅኤል 22: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ