ትንቢተ ሕዝቅኤል 29
29
በግብፅ ላይ የተነገረ ትንቢት
1በዐሥረኛው ዓመት በዐሥረኛው ወር ከወሩም በዐሥራ ሁለተኛው ቀን#ግሪክ ሰባ. ሊ. “በዐሥራ ሁለተኛው ዓመት በዐሥረኛው ወር በመጀመሪያው ቀን” ይላል። የእግዚአብሔር ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ 2“የሰው ልጅ ሆይ! ፊትህን በግብጽ ንጉሥ በፈርዖን ላይ አድርግ፤ በእርሱና በግብፅ ሁሉ ላይም ትንቢት ተናገር፤ 3እንዲህም በል፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ በወንዞች መካከል የሚተኛ፥ ወንዙ የእኔ ነው፤ ለራሴም ሠርቼዋለሁ የሚል ታላቅ ዘንዶ የግብፅ ንጉሥ ፈርዖን ሆይ! እነሆ በአንተ ላይ ነኝ። 4በመንጋጋዎችህ መቃጥን አገባብሃለሁ፤ የወንዞችህንም ዓሦች ሁሉ ወደ ቅርፊትህ አጣብቃለሁ፤ ከወንዞችህም መካከል አወጣሃለሁ፤ የወንዞችህም ዓሦች ሁሉ ወደ ቅርፊትህ ይጣበቃሉ። 5አንተንና የወንዞችህን ዓሦች ሁሉ ወደ ምድረ በዳ እጥላለሁ፤ በምድርም ፊት ላይ ትወድቃለህ እንጂ አትከማችም፤ አትሰበሰብምም፤ መብልም አድርጌ ለምድር አራዊትና ለሰማይ ወፎች ሰጥቼሃለሁ። 6ለእስራኤል ቤት የሸንበቆ በትር ሁነሃቸዋልና በግብፅ የሚኖሩ ሁሉ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ። 7በእጅ በያዙህ ጊዜ ተሰበርህ፤ ጫንቃቸውንም ሁሉ አቈሰልህ፤ በተደገፉብህም ጊዜ ተሰበርህ፤ ወገባቸውንም ሁሉ አንቀጠቀጥህ።
8“ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ ሰይፍን አመጣብሃለሁ፦ ሰውንና እንስሳንም ከአንተ ዘንድ አጠፋለሁ። 9የግብፅም ምድር ባድማና ውድማ ትሆናለች፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ፤ አንተ፦ ወንዙ የእኔ ነው፤ የሠራሁትም እኔ ነኝ ብለሃልና። 10ስለዚህ፥ እነሆ በአንተና በወንዞችህ ላይ ነኝ፤ የግብፅንም ምድር ከሚግዶል ጀምሮ እስከ ሰዌኔና እስከ ኢትዮጵያ ዳርቻ ድረስ በጦርና በቸነፈር ውድማና ባድማ አደርጋታለሁ። 11የሰው እግር አያልፍባትም፤ የእንስሳም ኮቴ አይረግጣትም፥ እስከ አርባ ዓመትም ድረስ ማንም አይኖርባትም። 12ባድማም በሆኑ ምድሮች መካከል የግብፅን ምድር ባድማ አደርጋታለሁ፤ በፈረሱትም ከተሞች መካከል ከተሞችዋ አርባ ዓመት ፈርሰው ይቀመጣሉ፤ ግብፃውያንንም ወደ አሕዛብ እበትናቸዋለሁ፤ በሀገሮችም እዘራቸዋለሁ።”
13ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ “ከአርባ ዓመት በኋላ ግብፃውያንን ከተበተኑባቸው አሕዛብ ዘንድ እሰበስባለሁ፤ 14የግብፅንም ምርኮ እመልሳለሁ፤ ወደ ተወለዱባትም ምድር ወደ ጳትሮስ እመልሳቸዋለሁ፤ በዚያም የተዋረደች መንግሥት ይሆናሉ። 15እንደ ገና በአሕዛብ ላይ ከፍ ከፍ እንዳይሉ ትንሽ መንግሥት ይሆናሉ፤ በአሕዛብም ላይ እንዳይበዙ አሳንሳቸዋለሁ። 16የእስራኤል ቤት እነርሱን በተከተሉ ጊዜ እርስዋ በደልን ታሳስባለች፤ ከእንግዲህም ወዲያ መታመኛ አትሆንላቸውም፤ እኔም ጌታ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።”
ንጉሥ ናቡከደነፆር ግብፅን ድል እንደ አደረገ
17እንዲህም ሆነ፤ በሃያ ሰባተኛው ዓመት በመጀመሪያው ወር ከወሩም በመጀመሪያው ቀን የእግዚአብሔር ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ 18“የሰው ልጅ ሆይ! የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር ሠራዊቱን በጢሮስ ላይ ጽኑ ሥራን አሠራቸው፤ ራስ ሁሉ የተላጨ፥ ጫንቃም ሁሉ የተላጠ ሆኖአል፤ ነገር ግን በላይዋ ስለ አሠራው ሥራ እርሱና ሠራዊቱ ከጢሮስ ደመወዝ አልተቀበሉም። 19ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ የግብፅን ምድር ለባቢሎን ንጉሥ ለናቡከደነፆር እሰጠዋለሁ፤ ብዛቷንም ይወስዳል፤ ምርኮዋንም ይማርካል፤ ብዝበዛዋንም ይበዘብዛል፤ ይህም ለሠራዊቱ ደመወዝ ይሆናል። 20ስለ እኔ ሠርተዋልና በጢሮስ ላይ ስለ አገለገለው አገልግሎት የግብፅን ምድር ደመወዝ አድርጌ ሰጥቼዋለሁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
21“በዚያ ቀን ለእስራኤል ቤት ቀንድን አበቅላለሁ፤ በመካከላቸውም ለአንተ የተከፈተ አፍን እሰጥሀለሁ፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።”
Currently Selected:
ትንቢተ ሕዝቅኤል 29: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ