ትንቢተ ሕዝቅኤል 34
34
የእስራኤል እረኞች
1የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ 2“የሰው ልጅ ሆይ! ትንቢት ተናገር፤ በእስራኤል እረኞች ላይ ትንቢት ተናገር፤ እረኞችንም እንዲህ በላቸው፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ራሳቸውን ለሚያሰማሩ ለእስራኤል እረኞች ወዮላቸው!#“ራሳቸውን ለሚያሰማሩ ለእስራኤል እረኞች ወዮላቸው” የሚለው በግሪክ ሰባ. ሊ. የለም። እረኞች ራሳቸውን ያሰማራሉን? እረኞች በጎችን ያሰማሩ ዘንድ አይገባቸውምን? 3ወተቱን ትጠጣላችሁ፤#ዕብ. “ጮማውን ትበላላችሁ” ይላል። ጠጕሩንም ትለብሳላችሁ፤ የወፈሩትን ታርዳላችሁ፤ በጎቹን ግን አታሰማሩም። 4የደከመውን አላጸናችሁትም፤ የታመመውንም አልፈወሳችሁትም፤ የተሰበረውንም አልጠገናችሁትም፤ የባዘነውንም አልመለሳችሁትም፤ የጠፋውንም አልፈለጋችሁትም፤ በኀይልና በጭቈናም ገዛችኋቸው። 5በጎችም እረኛን በማጣት ተበተኑ፤ ለዱርም አራዊት ሁሉ መብል ሆኑ። 6በጎች በተራሮች ሁሉና በረዘሙ ኮረብቶች ሁሉ ላይ ተበትነዋል፤ በጎችም በምድር ፊት ሁሉ ላይ ተበትነዋል፤ የሚፈልግም አልነበረም፤ የሚመልስም አልነበረም።
7“ስለዚህ እረኞች ሆይ! የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ፤ 8ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እኔ ሕያው ነኝና እረኞች ስለሌሉ፥ እረኞችም በጎችን ስላልፈለጉ፥ እረኞችም ራሳቸውን እንጂ በጎችን ስላላሰማሩ፥ በጎች ንጥቂያ ሆነዋልና፥ በጎችም ለዱር አራዊት ሁሉ መብል ሆነዋልና፤ 9ስለዚህ እረኞች ሆይ! የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ። 10ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ በእረኞች ላይ ነኝ፤ በጎችንም ከእጃቸው እፈልጋለሁ፤ በጎችንም ከማሰማራት አስተዋቸዋለሁ፤ ከዚያም ወዲያ እረኞች በጎችን አያሰማሩም፤ በጎችንም ከአፋቸው አድናለሁ፤ መብልም አይሆኑላቸውም።
11“ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ እኔ ራሴ በጎችን እሻለሁ፤ እጐበኛቸዋለሁም። 12በደመናና በጭጋግ ቀን እረኛ ከበጎቹ መካከል የተለየውን እንደሚፈልግ፥ እንደዚሁ በጎችን እፈልጋለሁ፤ በደመናና በጭጋግ ቀን ከተበተኑባቸው ሀገሮች ሁሉ እሰበስባቸዋለሁ። 13ከአሕዛብም ዘንድ አወጣቸዋለሁ፤ ከሀገሮችም ሁሉ እሰበስባቸዋለሁ፤ ወደ ገዛ ሀገራቸውም አመጣቸዋለሁ፤ በእስራኤልም ተራሮች ላይ፥ በፈሳሾችም አጠገብ፥ በምድርም ላይ ሰዎች በሚኖሩባት ስፍራ ሁሉ አሰማራቸዋለሁ። 14በመልካም ማሰማርያ አስማራቸዋለሁ፤ ጕረኖአቸውም በረዥሞቹ በእስራኤል ተራሮች ላይ ይሆናል፤ በዚያ በመልካም ጕረኖ ውስጥ ይመሰጋሉ፤ በእስራኤልም ተራሮች ላይ በለመለመ ማሰማርያ ይሰማራሉ። 15እኔ ራሴ በጎችን አሰማራለሁ፤ አስመስጋቸውማለሁ፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። 16የጠፋውንም እፈልጋለሁ፤ የባዘነውንም እመልሳለሁ፤ የተሰበረውንም እጠግናለሁ፤ የደከመውንም አጸናለሁ፤ የወፈረውንና#“የወፈረውንና” የሚለው በዕብ. ብቻ። የበረታውንም እጠብቃለሁ፤#ዕብ. “አጠፋለሁ” ይላል። በፍርድም እጠብቃቸዋለሁ።”
17ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ “እናንተም መንጋዬ ሆይ! እነሆ በበግና በበግ መካከል፥ በአውራ በግና በአውራ ፍየልም መካከል እፈርዳለሁ። 18የቀረውን ማሰማርያችሁን በእግራችሁ የረገጣችሁት፥ የተሰማራችሁበት መልካሙ መሰማርያ ባይበቃችሁ ነውን? የቀረውንስ ውኃ በእግራችሁ ያደፈረሳችሁት፥ ጥሩውን ውኃ መጠጣታችሁ ባይበቃችሁ ነውን? 19በጎችም በእግራችሁ በረገጣችሁት ይሰማራሉ፤ በእግራችሁም ያደፈረሳችሁትን ይጠጣሉ።
20“ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላቸዋል፦ እነሆ እኔ በወፈሩት በጎችና በከሱት በጎች መካከል እፈርዳለሁ። 21እስክትበትኑአቸው ድረስ በእንቢያና በትከሻ ስለምትገፉአቸው፥ የደከሙትንም ሁሉ በቀንዳችሁ ስለምትወጉአቸው፥ 22ስለዚህ መንጋዬን አድናለሁ፤ ከእንግዲህ ወዲህም ንጥቂያ አይሆኑም፤ በበግና በበግ መካከልም እፈርዳለሁ። 23በላያቸውም አንድ እረኛ አቆማለሁ፤ እርሱም ያሰማራቸዋል፤ እርሱም ባሪያዬ ዳዊት ነው፤ እረኛም ይሆናቸዋል። 24እኔም እግዚአብሔር አምላክ እሆናቸዋለሁ፤ ባሪያዬ ዳዊትም በመካከላቸው አለቃ ይሆናል፤ እኔ እግዚአብሔር ተናግሬአለሁ።
25“የሰላምንም ቃል ኪዳን ከዳዊት ቤት ጋር አደርጋለሁ፤ ክፉዎችንም አራዊት ከምድር አጠፋለሁ፤ ተዘልለውም በምድረ በዳ ይኖራሉ፤ በዱርም ውስጥ ይተኛሉ። 26እነርሱንና በኮረብታዬ ዙሪያ ያሉትን ስፍራዎች#“ያሉትን ስፍራዎች” የሚለው በዕብ. ብቻ። እባርካቸዋለሁ፤ ዝናቡንም በጊዜው#“በጊዜው” የሚለው በዕብ. ብቻ። አወርዳለሁ፤ የበረከትም ዝናብ ይሆናል። 27የምድረ በዳ ዛፍም ፍሬውን ይሰጣል፤ ምድርም ቡቃያዋን ትሰጣለች፤ በምድራቸውም በሰላም ታምነው ይኖራሉ፤ የቀንበራቸውንም ማነቆ በሰበርሁ ጊዜ፥ ከሚገዙአቸውም እጅ ባዳንኋቸው ጊዜ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ። 28እንግዲህ ለአሕዛብ ንጥቂያ አይሆኑም፤ የምድርም አራዊት አይበሉአቸዋም፤ ተዘልለውም ይቀመጣሉ፤ የሚያስፈራቸውም የለም። 29የሰላምን ተክል አቆምላቸዋለሁ፤ እንግዲህም ከራብ የተነሣ በምድር አያልቁም፤ የአሕዛብንም ስድብ ከእንግዲህ ወዲህ አይሸከሙም። 30እኔ እግዚአብሔር አምላካቸው ከእነርሱ ጋር እንዳለሁ፥ እነርሱም የእስራኤል ቤት ሕዝቤ እንደ ሆኑ ያውቃሉ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። 31እናንተም በጎች፥ የማሰማሪያዬ በጎች፥ ሰዎች#“ሰዎች” የሚለው በዕብ. ብቻ። ናችሁ፤ እኔም አምላካችሁ ነኝ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።”
Currently Selected:
ትንቢተ ሕዝቅኤል 34: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ