ትንቢተ ሕዝቅኤል 40
40
ስለ አዲሱ ቤተ መቅደስ የተገለጠ ራእይ
1በተማረክን በሃያ አምስተኛው ዓመት በዓመቱ መጀመሪያ ከወሩ በዐሥረኛው ቀን፥ ከተማዪቱ ከተመታች በኋላ በዐሥራ አራተኛው ዓመት፥ በዚያው ቀን የእግዚአብሔር እጅ በእኔ ላይ ነበረ፤ እርሱም ወደዚያ ወሰደኝ። 2በእግዚአብሔር ራእይ ወደ እስራኤል ምድር አመጣኝ፤ እጅግም በረዘመ ተራራ ላይ አኖረኝ፤ በዚያም ላይ እንደ ከተማ ሆኖ የተሠራ ነገር በፊቴ ነበረ። 3ወደዚያም አመጣኝ፤ እነሆም መልኩ እንደሚያንፀባርቅ ናስ መልክ የመሰለ አንድ ሰው በዚያ ነበረ፤ በእጁም የተልባ እግር ገመድና የመለኪያ ዘንግ ነበረ፤ እርሱም በበሩ አጠገብ ቆሞ ነበር። 4ያም ሰው፥ “የሰው ልጅ ሆይ! ይህን አሳይህ ዘንድ አንተ ወደዚህ መጥተሃልና በዐይንህ እይ፤ በጆሮህም ስማ፤ የማሳይህንም ሁሉ በልብህ ጠብቅ፤ የምታየውንም ሁሉ ለእስራኤል ቤት ንገር” አለኝ።
5እነሆም በቤቱ ውጭ በዙሪያው ቅጥር ነበረ፤ በሰውየውም እጅ የክንዱ ልክ አንድ ክንድ ከጋት የሆነ ስድስት ክንድ ያለበት የመለኪያ ዘንግ ነበረ፤ የቅጥሩንም ስፋት አንድ ዘንግ ቁመቱንም አንድ ዘንግ አድርጎ ለካ። 6ወደ ምሥራቅ ወደሚመለከተውም በር መጣ፤ በሰባቱም ደረጃዎች ላይ ወጣ፤ በበሩ በኩል ያለውንም የመድረኩን ወለል ወርዱን አንድ ዘንግ አድርጎ ለካ፤ የሁለተኛውም ወለል ወርድ አንድ ዘንግ ነበረ። 7የዕቃ ቤቱ ሁሉ ርዝመት አንድ ዘንግ፤ ወርዱም አንድ ዘንግ ነበረ፤ በዕቃ ቤቶቹም መካከል አምስት ክንድ ነበረ፤ በበሩም ደጀ ሰላም፤ በስተውስጥ በኩል የሚገኝ የበሩ የመድረክ ወለል አንድ ዘንግ ነበረ። 8በስተውስጥም#ግሪክ ሰባ. ሊ. “ሦስተኛው ክፍል” ይላል። ያለውን የበሩን ደጀሰላም አንድ ዘንግ አድርጎ ለካ። 9የበሩንም ደጀ ሰላም ስምንት ክንድ፤ የግንቡንም አዕማድ ወርድ ሁለት ክንድ አድርጎ ለካ፤ የበሩም ደጀ ሰላም በስተውስጥ ነበረ። 10የምሥራቁም ዕቃ ቤቶች በዚህ በኩል ሦስት፥ በዚያም በኩል ሦስት፥ ነበሩ፤ ለሦስቱም አንድ ልክ ነበረ፤ የግንቡም አዕማድ ወርድ በዚህ በኩልና በዚያ በኩል አንድ ልክ ነበረ። 11የበሩንም መግቢያ ወርድ ዐሥር ክንድ፥ የበሩንም ርዝመት ዐሥራ ሦስት ክንድ አድርጎ ለካ። 12በዕቃ ቤቱም ፊት በዚህ በኩል አንድ ክንድ፥ በዚያም በኩል አንድ ክንድ የሆነ ዳርቻ ነበረ፤ የዕቃ ቤቱም በዚህ በኩል ስድስት ክንድ በዚያም በኩል ስድስት ክንድ ነበሩ። 13ከአንዱም የዕቃ ቤት ደርብ ጀምሮ እስከ ሌላው ደርብ ድረስ የበሩን ወርድ ሃያ አምስት ክንድ አድርጎ ለካ፤ በሩና በሩም ትይዩ ነበረ። 14ደጀ ሰላሙንም ሃያ#ዕብ. “ስድሳ” ይላል። ክንድ አድርጎ ለካ፤ በበሩም ደጀ ሰላም ዙሪያ አደባባይ ነበረ። 15ከበሩም መግቢያ ፊት ጀምሮ እስከ ውስጠኛው የበሩ ደጀ ሰላም መጨረሻ ድረስ አምሳ ክንድ ነበረ። 16በዕቃ ቤቶቹም በበሩ ውስጥ በዙሪያው በነበሩትም በግንቡ አዕማድ የዐይነ ርግብ መስኮቶች ነበሩባቸው፤ ደግሞም በደጀ ሰላሙ ውስጥ በዙሪያው መስኮቶች ነበሩ፤ በግንቡም አዕማድ ሁሉ ላይ የዘንባባ ዛፍ ተቀርጾባቸው ነበር።
17ወደ ውስጠኛው አደባባይም አገባኝ፤ እነሆም በአደባባዩ ዙሪያ የተሠሩ ዕቃ ቤቶችና ወለል ነበሩ፤ በወለሉም ላይ ሠላሳ ዕቃ ቤቶች ነበሩ። 18ወለሉም በበሮች አጠገብ ነበረ፤ ይህም ታችኛው ወለል እንደ በሮቹ ርዝመት መጠን ነበረ። 19ከታችኛውም በር ፊት ጀምሮ እስከ ውስጠኛው አደባባይ ፊት ድረስ ወርዱን አንድ መቶ ክንድ አድርጎ ወደ ምሥራቅና ወደ ሰሜን ለካ።
20ወደ ሰሜንም መራኝ፤ እነሆም በውጭው አደባባይ ያለ ወደ ሰሜን የሚመለከት በር ነበረ፤ ርዝመቱንና ወርዱንም ለካ። 21የዕቃ ቤቶቹም በዚህ በኩል ሦስት፥ በዚያም በኩል ሦስት ነበሩ፤ የግንቡ አዕማድና መዛነቢያዎቹም፥ ወደ ምሥራቅ የሚያሳዩ ዘንባባዎቹም አምሳ ክንድ ነበሩ፤ ወርዱም ሃያ አምስት ክንድ ነበረ። 22መስኮቶቹም፥ መዛነቢያዎቹም፥ የዘንባባ ዛፎቹም ወደ ምሥራቅ እንደሚመለከተው በር ልክ ነበሩ፤ ወደ እርሱም የሚያደርሱ ሰባት ደረጃዎች ነበሩ፤ መዛነቢያዎቹም በፊቱ ነበሩ። 23በውስጠኛውም አደባባይ በሰሜኑና በምሥራቁ በኩል በሌላው በር አንጻር በር ነበረ፤ ከበርም እስከ በር አንድ መቶ ክንድ አድርጎ ለካ።
24ወደ ደቡብም መራኝ፤ እነሆም ወደ ደቡብ የሚመለከት በር ነበረ፤ የግንቡን አዕማድና መዛነቢያዎቹንም እንደዚያው መጠን አድርጎ ለካ። 25በእርሱና በመዛነቢያዎቹም ዙሪያ እንደ እነዚያ መስኮቶች የሚመስሉ መስኮቶች ነበሩ፤ ርዝመቱ አምሳ ክንድ፥ ወርዱም ሃያ አምስት ክንድ ነበረ። 26ወደ እርሱም የሚያደርሱ ሰባት ደረጃዎች ነበሩ፤ መዛነቢያዎቹም በፊቱ ነበሩ፤ በግንቡም አዕማድ ላይ አንዱ በዚህ አንዱም በዚያ ወገን ሆኖ የዘንባባ ዛፍ ተቀርጾባቸው ነበር። 27በውስጠኛውም አደባባይ በደቡብ በኩል በር ነበረ፤ ከበር እስከ በር ድረስ በደቡብ በኩል መቶ ክንድ አድርጎ ለካ።
28በደቡብም በር በኩል ወደ ውስጠኛው አደባባይ አገባኝ፤ እንደዚያውም መጠን አድርጎ የደቡብን በር ለካ፤ 29እንደዚያውም መጠን አድርጎ የዕቃ ቤቶቹንና የግንቡን አዕማድ፥ መዛነቢያዎቻቸውንም ለካ፤ በእርሱና በመዛነቢያዎቹም ዙሪያ መስኮቶች ነበሩ፤ ርዝመቱ አምሳ ክንድ፥ ወርዱም ሃያ አምስት ክንድ ነበረ። 30በዙሪያውም ደጀ ሰላሞች ነበሩ፤ ርዝመታቸውም ሃያ አምስት ክንድ፥ ወርዳቸውም አምስት ክንድ ነበረ። 31መዛነቢያዎቹም ወደ ውጭው አደባባይ ይመለከቱ ነበር፤ በግንቡም አዕማድ ላይ የዘንባባ ዛፍ ተቀርጾ ነበር፤ ወደ እርሱም የሚያደርሱ ስምንት ደረጃዎች ነበሩ።
32በውስጠኛውም አደባባይ በምሥራቅ በኩል አገባኝ፤ በሩንም ለካ፤ መጠኑም እንደ እነዚያ ነበረ። 33እንደዚያም መጠን የዕቃ ቤቶቹንና የግንቡን አዕማድ፥ መዛነቢያዎቹንም ለካ፤ በእርሱና በመዛነቢያዎቹም ዙሪያ መስኮቶች ነበሩ፤ ርዝመቱም አምሳ ክንድ፥ ወርዱም ሃያ አምስት ክንድ ነበረ። 34መዛነቢያዎቹም በስተ ውጭ ወደ አለው አደባባይ ይመለከቱ ነበር፤ በግንቡም አዕማድ ላይ በዚህና በዚያ ወገን የዘንባባ ዛፍ ተቀርጾ ነበር፤ ወደ እርሱም የሚያደርሱ ስምንት ደረጃዎች ነበሩት።
35በሰሜንም ወደ አለው በር አመጣኝ፤ እንደዚያውም መጠን ለካው፤ 36የዕቃ ቤቶቹንና የግንቡን አዕማድ፥ መዛነቢያዎቹንም ለካ፤ በዙሪያውም መስኮቶች ነበሩበት፤ ርዝመቱም አምሳ ክንድ፥ ወርዱም ሃያ አምስት ክንድ ነበረ። 37የግንቡም አዕማድ ወደ ውጭው አደባባይ ይመለከቱ ነበር፤ በግንቡም አዕማድ ላይ በዚህና በዚያ ወገን የዘንባባ ዛፍ ተቀርጾ ነበር፤ ወደ እርሱም የሚያወጡ ስምንት ደረጃዎች ነበሩት።
38በበሮቹም በግንቡ አዕማድ አጠገብ ዕቃ ቤቱና መዝጊያው ነበሩ፤ በዚያም የሚቃጠለውን መሥዋዕት ያጥቡ ነበር። 39የሚቃጠለውንም መሥዋዕት፥ የኀጢአቱንና የበደሉንም መሥዋዕት ያርዱባቸው ዘንድ፥ በበሩ ደጀ ሰላም በዚህ ወገን ሁለት ገበታዎች፥ በዚያም ወገን ሁለት ገበታዎች ነበሩ። 40በሰሜን በኩል በአለው በር በስተውጭው፥ በመወጣጫው ደረጃዎች አጠገብ፥ በአንዱ ወገን ሁለት ገበታዎች ነበሩ፤ በሌላውም ወገን በበሩ ደጀ ሰላም በኩል ሁለት ገበታዎች ነበሩ። 41በበሩ አጠገብ በዚህ ወገን አራት ገበታዎች፥ በዚያም ወገን አራት ገበታዎች ነበሩ፤ መሥዋዕት የሚያርዱባቸው ገበታዎች ስምንት ነበሩ። 42ስለሚቃጠለውም መሥዋዕት ርዝመታቸው አንድ ክንድ ተኩል ወርዳቸውም አንድ ክንድ ተኩል ቁመታቸውም አንድ ክንድ የሆኑ፥ የሚቃጠለውን መሥዋዕትና ሌላውን መሥዋዕት የሚያርዱበትን ዕቃ ያኖሩባቸው ዘንድ፥ ከተጠረበ ድንጋይ የተሠሩ አራት ገበታዎች ነበሩ። 43በዙሪያውም በስተውስጥ የነበረው የለዘበ ከንፈራቸው አንድ ጋት ነበረ፤ በገበታውም ላይ#ዕብ. “በገበታዎቹም ላይ የቍርባኑ ሥጋ ነበረባቸው” ይላል። መክደኛ ነበረ፤ ከፀሐይና ከዝናምም የተሰወረ ነበረ።
44ወደ ውስጠኛውም አደባባይ አገባኝ፤ እነሆም ሁለት ቤቶች ነበሩ፤ አንዱ ወደ ሰሜን በሚመለከተው በር አጠገብ ነበረ፤ መግቢያውም ወደ ደቡብ ይመለከት ነበረ፤ ሌላውም ወደ ደቡብ በሚመለከተው በር አጠገብ ነበረ፤ መግቢያውም ወደ ሰሜን ይመለከት ነበር። 45ሰውዬውም፥ “ይህ ወደ ደቡብ የሚመለከት ቤት ለማገልገል ለሚተጉ ካህናት ነው። 46ወደ ሰሜንም የሚመለከተው ቤት መሠዊያዉን ለማገልገል ለሚተጉ ካህናት ነው፤ እነዚህ ከሌዊ ልጆች መካከል ያገለግሉት ዘንድ ወደ እግዚአብሔር የሚቀርቡ የሳዶቅ ልጆች ናቸው” አለኝ። 47አደባባዩንም በአራት ማዕዘኑ ርዝመቱን መቶ ክንድ፥ ወርዱንም መቶ ክንድ አድርጎ ለካ፤ መሠዊያውም በቤቱ ፊት ነበረ።
48ወደ ቤቱም ደጀ ሰላም አመጣኝ፤ የደጀ ሰላሙንም የግንብ አዕማድ ወርድ በዚህ ወገን አምስት ክንድ፤ በዚያም ወገን አምስት ክንድ አድርጎ ለካ፤ የበሩም ወርድ ዐሥራ አራት ክንድ ነበረ፤ በበሩም በዚህ ወገንና በዚያ ወገን የነበሩት ግንቦች ሦስት ሦስት ክንድ ነበሩ። 49የደጀ ሰላሙም ርዝመት ሃያ ክንድ፥ ወርዱም ዐሥራ ሁለት ክንድ ነበረ፥ ወደ እርሱም የሚያደርሱ ዐሥር ደረጃዎች ነበሩ፤ አንድ በዚህ ወገን፥ አንድም በዚያ ወገን ሆነው በመቃኖቹ አጠገብ የግንብ አዕማድ ነበሩ።
Currently Selected:
ትንቢተ ሕዝቅኤል 40: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ