ትንቢተ ሕዝቅኤል 43
43
የእግዚአብሔር የክብሩ ብርሃን
1ወደ ምሥራቅም ወደሚመለከተው በር አመጣኝ። 2እነሆም የእስራኤል አምላክ ክብር ከምሥራቅ መንገድ መጣ፤ ድምፁም እንደ ብዙ ውኆች ይተምም ነበር፤ ከክብሩም የተነሣ ምድር ታበራ ነበር። 3ያየሁትም ራእይ ከተማዪቱን ለማጥፋት በመጣሁ ጊዜ እንደ አየሁት ራእይ ነበረ፤ ራእዩም በኮቦር ወንዝ እንደአየሁት ራእይ ነበረ፤ እኔም በግምባሬ ተደፋሁ። 4የእግዚአብሔርም ክብር ወደ ምሥራቅ በሚመለከት በር ወደ መቅደሱ ገባ። 5መንፈስም አነሣኝ፤ ወደ ውስጠኛውም አደባባይ አገባኝ፤ እነሆም የእግዚአብሔር ክብር መቅደሱን መልቶት ነበር።
6በመቅደሱም ሆኖ የሚናገረኝን ሰማሁ፤ በአጠገቤም ሰው ቆሞ ነበር።#ግሪክ ሰባ. ሊ. “እኔም ቆሜ ነበር” ይላል። 7እንዲህም አለኝ፥ “የሰው ልጅ ሆይ! በእስራኤል ልጆች መካከል ለዘለዓለም የምቀመጥበት የዙፋኔ ስፍራና የእግሬ ጫማ መረገጫ ይህ ነው። ዳግመኛም የእስራኤል ቤትና ነገሥታቶቻቸው በዝሙታቸውና በከፍታዎቻቸው በአለው በነገሥታቶቻቸው ሬሳ ቅዱስ ስሜን አያረክሱም። 8መድረካቸውን በመድረኬ አጠገብ፥ መቃናቸውንም በመቃኔ አጠገብ አድርገዋልና። በእኔና በእነርሱ መካከል ግንብ ብቻ ነበረ፤ በሠሩትም ርኵሰት ቅዱስ ስሜን አረከሱ፤ ስለዚህ በቍጣዬ አጠፋኋቸው። 9አሁንም ዝሙታቸውንና የነገሥታቶቻቸውን ሬሳ ከእኔ ዘንድ ያርቁ፤ እኔም ለዘለዓለም በመካከላቸው አድራለሁ።
10“አንተም የሰው ልጅ ሆይ፥ ሥራቸውንና ኀጢአታቸውን ይተዉ ዘንድ ለእስራኤል ቤት ይህን ቤት አሳያቸው፤ አምሳያውንም ይለኩ። 11እነርሱም ስለ ሠሩት ሥራ ሁሉ መቅሠፍታቸውን ያገኛሉ፤ አንተም የቤቱን መልክና ምሳሌውን፥ መውጫውንም፥ መግቢያውንም፥ ሥርዐቱንም፥ ሕጉንም ሁሉ አስታውቃቸው፤ ሥርዐቱንና ሕጉን ሁሉ ይጠብቁ ዘንድ፥ ያደርጉትም ዘንድ በፊታቸው ጻፈው። 12በተራራው ራስ ላይ ያለውን ቤቱንና የቤቱን ሥርዐት ሣል፤ የዙሪያውም ዳርቻ ሁሉ ቅዱሰ ቅዱሳን ነው። እነሆ የቤቱ ሕግ ይህ ነው።”
የመሠውያ አሠራር
13የመሠዊያው ልክ በክንድ ይህ ነው፤ ክንዱም ክንድ ተጋት ነው። የመሠረቱም ቁመቱ አንድ ክንድ፥ ወርዱም አንድ ክንድ ነው፤ አንድ ስንዝርም ክፈፍ ዳር ዳሩን በዙሪያው አለ፤ የመሠዊያው ቁመት እንዲሁ ነው። 14በመሬቱም ላይ ከአለው መሠረት ጀምሮ እስከ ታችኛው እርከን ድረስ ሁለት ክንድ፥ ወርዱም አንድ ክንድ ነው፤ ከትንሹም እርከን ጀምሮ እስከ ትልቁ እርከን ድረስ አራት ክንድ፥ ወርዱም አንድ ክንድ ነው። 15ምድጃውም አራት ክንድ ነው፤ በምድጃውም ላይ አንድ ክንድ ወደ ላይ ከፍ የሚሉ አራት ቀንዶች አሉበት። 16የምድጃውም ርዝመት ዐሥራ ሁለት ክንድ፥ ወርዱም ዐሥራ ሁለት ክንድ ነው፥ አራቱም ማዕዘን ትክክል ነው። 17የእርከኑም ርዝመት ዐሥራ አራት ክንድ፥ ወርዱም ዐሥራ አራት ክንድ ነው፤ አራቱም መዐዝን ትክክል ነው፤ በዙሪያውም ያለው ክፈፍ የክንድ እኩሌታ ነው፤ መሠረቱም በዙሪያው አንድ ክንድ ነው፤ ደረጃዎቹም ወደ ምሥራቅ ይመለከታሉ።”
18እንዲህም አለኝ፥ “የሰው ልጅ ሆይ! ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ የሚቃጠለውን መሥዋዕት ያቀርቡበት ዘንድ፥ ደሙንም ይረጩበት ዘንድ በሚሠሩበት ቀን የመሠዊያው ሕግ ይህ ነው። 19ያገለግሉኝ ዘንድ ወደ እኔ ለሚቀርቡ ከሳዶቅ ዘር ለሚሆኑ ለሌዋውያኑ ካህናት ለኀጢአት መሥዋዕት የሚሆነውን ከመንጋው አንድ ወይፈን ትሰጣቸዋለህ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። 20ከደሙም ትወስዳለህ፤ በአራቱ የመሠዊያ ቀንዶቹም፥ በእርከኑም በአራቱ ማዕዘን ላይ፥ በዙሪያውም በአለው ክፈፍ ላይ ትረጨዋለህ፤ እንዲሁ ታነጻዋለህ፤ ታስተሰርይለትማለህ። 21ለኀጢአትም መሥዋዕት የሚሆነውን ወይፈን ትወስዳለህ፤ በመቅደሱም ውጭ በቤቱ በተለየው ስፍራ ይቃጠላል። 22በሁለተኛውም ቀን ለኀጢአት መሥዋዕት የሚሆነውን ነውር የሌለበትን አውራ ፍየል#ግሪክ ሰባ. ሊ. “ሁለት የፍየል ጠቦቶችን” ይላል። ታቀርባለህ፤ በወይፈኑም እንዳነጹት እንዲሁ መሠዊያውን ያነጹበታል። 23ማንጻቱንም ከፈጸምህ በኋላ ነውር የሌለበትን ወይፈን፥ ከበጎችም ነውር የሌለበትን ጠቦት በግ ታቀርባለህ፤ 24በእግዚአብሔርም ፊት ታቀርባቸዋለህ፤ ካህናቱም ጨው ይጨምሩባቸዋል፤ የሚቃጠለውንም መሥዋዕት አድርገው ለእግዚአብሔር ያቀርቡአቸዋል። 25ሰባት ቀንም በየዕለቱ ለኀጢአት መሥዋዕት የሚሆነውን አውራ ፍየል ታቀርባለህ፤ ነውርም የሌለባቸውን አንድ ወይፈንና ከበጎችም አንድ ጠቦት በግ ያቀርባሉ። 26ሰባት ቀን ለመሠዊያው ያስተሠርያሉ፤ ያነጹታል፤ ይቀድሱትማል። 27ቀኖቹንም በፈጸሙ ጊዜ በስምንተኛው ቀን ከዚያም በኋላ ካህናቱ የሚቃጠለውን መሥዋዕታችሁን፥ የደኅንነት መሥዋዕታችሁንም በመሠዊያው ላይ ያደርጋሉ፤ እኔም እቀበላችኋለሁ፥” ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
Currently Selected:
ትንቢተ ሕዝቅኤል 43: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ