ትንቢተ ሆሴዕ 4
4
እግዚአብሔር እስራኤልን እንደ ወቀሰ
1እናንተ የእስራኤል ልጆች ሆይ! እውነትና ምሕረት፥ እግዚአብሔርንም ማወቅ በምድር ስለሌለ እግዚአብሔር በምድር ላይ የሚኖሩትን ይወቅሳልና የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ። 2ነገር ግን ሐሰት፥ ግዳይና ስርቆት፥ ምንዝርናም ምድርን ሞልተዋል፤ ደምንም ከደም ጋር ይቀላቅላሉ። 3ስለዚህ ምድሪቱ ታለቅሳለች፤ በእርስዋም ከሚቀመጡ ሁሉ ከምድር አራዊትና ከሰማይ ወፎች፤ ከምድርም ተንቀሳቃሾች#“ከምድር ተንቀሳቃሾች” የሚለው በዕብ. የለም። ጋር ትጠፋለች፤ የባሕሩም ዓሦች ያልቃሉ። 4ነገር ግን ሕዝቤ እንደሚከራከር ካህን ነውና እንግዲህ የሚከራከር፥ ማንም አይኑር፥ የሚዘልፍም ማንም አይኑር። 5በቀንም ትደክማለህ፤ ነቢዩም ከአንተ ጋር ይደክማል፤ እናታችሁም ሌሊትን ትመስላለች።#ዕብ. “እናትህንም አጠፋታለሁ” ይላል።
6ሕዝቤ አእምሮ እንደሌላቸው ይመስላሉ፤ አንተም አእምሮህ ተለይቶሃልና እኔ ካህን እንዳትሆነኝ እተውሃለሁ፤ የአምላክህንም ሕግ ረስተሃልና እኔ ደግሞ ልጆችህን እረሳለሁ። 7እንደ ብዛታቸው መጠን ኀጢአት ሠሩብኝ፤ እኔም ክብራቸውን ወደ ውርደት እለውጣለሁ። 8ሕዝቤንም ኀጢአታቸው ትበላቸዋለች፤#ዕብ. እና ግሪክ ሰባ. ሊ. “የሕዝቤ ኀጢአት መብል ሆኖላቸዋል ፤ ልባቸውንም በበደላቸው አድርገዋል” ይላል። ሰውነታቸውንም በበደላቸው ይወስዷታል። 9እንደ ሕዝቡም እንዲሁ ካህኑ ይሆናል፤ በመንገዳቸውም እበቀላቸዋለሁ፤ እንደ ሥራቸውም እከፍላቸዋለሁ። 10እግዚአብሔርንም መጠበቅ ትተዋልና ሲበሉ አይጠግቡም፤ ሲያመነዝሩም አይበዙም።#ግሪክ ሰባ. ሊ. “አይቀናቸውም” ይላል።
11የሕዝቤ ልቡናቸው ዝሙትን፥ መጠጥንና ስካርን ወደደ። 12ሕዝቤ በዝሙት መንፈስ ስተዋልና ከአምላካቸውም ርቀው አመንዝረዋልና በትርን ይጠይቃሉ፤ በትሩም ይመልስላቸዋል። 13በተራሮችም ራስና በኮረብታዎች ላይ ይሠዋሉ፤ ጥላውም መልካም ነውና ከኮምበልና ከልብን፥ ከአሆማም ዛፍ በታች ያርዳሉ፤ ስለዚህ ሴቶች ልጆቻችሁ ይሰስናሉ፤ ሙሽሮቻችሁም ያመነዝራሉ። 14ወንዶችም ደግሞ ከአመንዝሮች ጋር ይጫወታሉና፥ ከጋለሞቶችም ጋር ይሠዋሉና ሴቶች ልጆቻችሁ በሰሰኑ ጊዜ፥ ሙሽሮቻችሁም በአመነዘሩ ጊዜ አልቀጣኋቸውም፤ የማያስተውልም ሕዝብ ከአመንዝራ ጋር ይቀላቀላል።#ዕብ. “የማያስተውል ሕዝብ ይገለበጣል” ይላል።
15እስራኤል ሆይ! አንተ አላዋቂ አትሁን፤ አንተም ይሁዳ! ወደ ጌልጌላ አትሂድ፤ ወደ ቤትአዊንም አትውጡ፤ በሕያው እግዚአብሔርም አትማሉ። 16እስራኤል እንደምትደነብር ጊደር ደንብሮአል፤ እግዚአብሔርም በሰፊው ቦታ እንደ ጠቦት ያሰማራዋል። 17እንዲሁም ኤፍሬም ከጣዖታት ጋር ተጋጠመ፤ ለራሱም ዕንቅፋትን አኖረ። 18ከነዓናውያንንም መረጣቸው፤ ፈጽመውም አመነዘሩ፤ በክፋታቸውም#ዕብ. “ከክብራቸው ይልቅ” ይላል። ውርደትን መረጡ። 19አንተ በክንፎችዋ ውስጥ የነፋስ መናወጥ ነህ፤ ከመሥዋዕታቸውም የተነሣ ያፍራሉ።
Currently Selected:
ትንቢተ ሆሴዕ 4: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ