ትንቢተ ኤርምያስ 15
15
በይሁዳ ሕዝብ ላይ ስለሚደርሰው ፍርድ
1እግዚአብሔርም እንዲህ አለኝ፥ “ሙሴና ሳሙኤል በፊቴ ቢቆሙም፥ ልቤ ወደዚህ ሕዝብ አያዘነብልም፤ እነዚህን ሕዝቦች ከፊቴ አባርራቸው፤ ይውጡ። 2እነርሱም፦ ወዴት እንሂድ ቢሉህ፥ አንተ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ለሞት የሆነ ወደ ሞት፥ ለሰይፍም የሆነ ወደ ሰይፍ፥ ለራብም የሆነ ወደ ራብ፥ ለምርኮም የሆነ ወደ ምርኮ ትላቸዋለህ። 3ሰይፍን ለመግደል፥ ውሾችንም ለመጐተት፥ የሰማያትንም ወፎች፥ የምድርንም አራዊት ለመብላትና ለማጥፋት፥ አራቱን ዓይነት ጥፋት አዝዝባቸዋለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር። 4የይሁዳ ንጉሥ የሕዝቅያስ ልጅ ምናሴ በኢየሩሳሌም ስለ አደረገው ሁሉ በምድር መንግሥታት ሁሉ መካከል ለመከራ አሳልፌ እሰጣቸዋለሁ።
5“ኢየሩሳሌም ሆይ! የሚራራልሽ ማን ነው? የሚያዝንልሽስ ማን ነው? ወይስ ስለ ደኅንነትሽ ይጠይቅ ዘንድ ፈቀቅ የሚል ማን ነው? 6አንቺ እኔን ከድተሽኛል፤ እኔንም መከተል ትተሻል፤ ይላል እግዚአብሔር፤ ወደ ኋላሽም ተመልሰሻል፤ ስለዚህ እጄን በአንቺ ላይ ዘርግቼ አጠፋሻለሁ፤ ይቅርም አልላቸውም። 7ሕዝቤንም ወደ ዳርቻ ፈጽሜ እበትናቸዋለሁ፤ የወላድ መካን አድርጌአቸዋለሁ፤ ሕዝቤንም ስለ ኀጢአታቸው አጥፍቻቸዋለሁ፤ ከመንገዳቸውም አልተመለሱም።#“ከመንገዳቸው አልተመለሱም” የሚለው በግሪክ ሰባ. ሊ. የለም። 8መበለቶቻቸውም ከባሕር አሸዋ ይልቅ በዝተዋል፤ በብላቴኖች እናት ላይ በቀትር ጊዜ አጥፊውን አምጥቻለሁ፤ ጭንቀትንና ድንጋጤን በድንገት አምጥቼባታለሁ። 9ሰባት የወለደች ባዶ ቀረች፤ ነፍስዋም ተጨንቃለች፤ በቀትር ጊዜ ፀሐይዋ ገብታባታለች፤ አፍራለች፤ ተዋርዳማለች፤ የተረፉትንም በጠላቶቻቸው ፊት ለሰይፍ አሳልፌ እሰጣለሁ፥” ይላል እግዚአብሔር።
ኤርምያስ ኀዘኑን እንደ ገለጠ
10እናቴ ሆይ! ለምድር ሁሉ የክርክርና የጥል ሰው የሆንሁትን እኔን ወልደሽኛልና ወዮልኝ! ለማንም አልጠቀምሁም፤ ማንም እኔን አልጠቀመኝም፤ ከሚረግሙኝም የተነሣ ኀይሌ አለቀ። 11አቤቱ! በመከራቸውና በጭንቃቸው ጊዜ በጠላቶቻቸው ዘንድ ስለ እነርሱ በጎ ነገር በአንተ ፊት የቆምሁ ባልሆን ይህ ለእነርሱ መከናወን ይሁን።#ዕብ. “እግዚአብሔር እንዲህ አለ፦ በእውነት ለደኅንነትህ አጸናሃለሁ ፤ በእውነት በመከራና በጭንቅ ጊዜ ጠላትህ እንዲለምንህ አደርገዋለሁ” ይላል። 12በውኑ ብረትን፥ የሰሜንን ብረት፥ ናስንም የሚሰብር አለን?#ምዕ. 15 ቍ. 12 በብዙ ዘሮች ይለያያል።
13በዳርቻህ ሁሉ ስላለ ኀጢአትህ ሁሉ ፋንታ ባለጠግነትህንና መዝገብህን ለመበዝበዝ በከንቱ እሰጣለሁ። 14እሳት ከቍጣዬ ትነድዳለችና፥ እናንተንም ታቃጥላችኋለችና በማታውቀው ሀገር ለጠላቶችህ አስገዛሃለሁ።
15አቤቱ! አንተ ታውቃለህ፤#“አቤቱ! አንተ ታውቃለህ” የሚለው በግሪክ ሰባ. ሊ. የለም። አስበኝ፤ ጐብኘኝም፤ ከሚያሳድዱኝም አድነኝ እንጂ፥ አትታገሣቸው፤ ስለ አንተ እንደ ሰደቡኝ አስብ። 16ቃልህ ተገኝቶአል፤ እኔም በልችዋለሁ፤#“ቃልህ ተገኝቶአል ፤ እኔም በልችዋለሁ” የሚለው በዕብ. ብቻ። አቤቱ! የሠራዊት አምላክ ሆይ! ቃልህን የከዱ ሰዎችን አጥፋቸው፤ ስምህ በእኔ ላይ ተጠርትዋልና፥ ቃልህ ሐሤትና የልብ ደስታ ሆነኝ። 17በዋዘኞች ጉባኤ አልተቀመጥሁም፤ ነገር ግን በእጅህ ፊት ፈርቻለሁ፤ ምሬትን ሞልተህብኛልና ለብቻዬ ተቀመጥሁ። 18የሚያሳዝኑኝ በእኔ ላይ ለምን ይበረታሉ?#ዕብ. “ስለ ምን ሕመሜ አዘወተረኝ” ይላል። ቍስሌስ ስለ ምን የማይፈወስ ሆነ? ስለ ምንስ አልሽርም አለ? እንደ ሐሰተኛ ምንጭ፥ እንዳልታመነች ውኃም ሆነብኝ።
19ስለዚህ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ብትመለስ እመልስሃለሁ፤ በፊቴም ትቆማለህ፤ የከበረውንም ከተዋረደው ብትለይ እንደ አፌ ትሆናለህ፤ እነርሱ ወደ አንተ ይመለሳሉ፤ አንተ ግን ወደ እነርሱ አትመለስም። 20ለዚህም ሕዝብ የተመሸገ የናስ ቅጥር አደርግሃለሁ፤ ይዋጉሃል፤ እኔ ግን ለማዳን ከአንተ ጋር ነኝና አያሸንፉህም። 21ከክፉ ሰዎችም እጅ እታደግሃለሁ፤ ከጨካኞችም ጡጫ እቤዥሃለሁ።
Currently Selected:
ትንቢተ ኤርምያስ 15: አማ2000
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ