መጽሐፈ ኢያሱ ወልደ ነዌ 6
6
የኢያሪኮ ቅጥር መውደቅ
1ኢያሪኮም በግንብ ታጥራ#ዕብ. “ኢያሪኮም ከእስራኤል ልጆች የተነሣ” የሚል ይጨምራል። ተዘግታ ነበር፤ ወደ እርስዋ የሚገባ፥ ከእርስዋም የሚወጣ አልነበረም። 2እግዚአብሔርም ኢያሱን አለው፥ “እነሆ፥ ኢያሪኮንና ንጉሥዋን ጽኑዓን፥ ኀያላንዋንም በእጅህ ሰጥቼአለሁ። 3አንተም ተዋጊዎችን ሁሉ በዙሪያው አሰልፋቸው። ተዋጊዎቻችሁም ሁሉ በከተማዪቱ ዙሪያ አንድ ጊዜ ይዙሩ፤ እንዲሁም ስድስት ቀን አድርጉ።#“ተዋጊዎቻችሁም ሁሉ በከተማዪቱ ዙሪያ ይዙሩ ፤ እንዲሁም ስድስት ቀን አድርጉ” የሚለው በግሪክ ሰባ. ሊ. የለም። 4ሰባትም ካህናት ሰባት ቀንደ መለከት በታቦቱ ፊት ይያዙ፤ በሰባተኛውም ቀን ከተማዪቱን ሰባት ጊዜ ዙሩ፤ ካህናቱም ቀንደ መለከቱን ይንፉ።#ምዕ. 6 ቍ. 4 በግሪክ ሰባ. ሊ. የለም። 5ቀንደ መለከቱም ባለማቋረጥ ሲነፋ፥ የመለከቱን ድምፅ ስትሰሙ፥ ሕዝቡ ሁሉ ታላቅ ጩኸት ይጩኹ፤ የከተማዪቱም ቅጥር ይወድቃል፤ ሕዝቡም ሁሉ እያንዳንዱ ፊት ለፊት እየሮጠ ይገባባታል።” 6የነዌም ልጅ ኢያሱ ካህናቱን ጠርቶ፥ “የቃል ኪዳኑን ታቦት ተሸከሙ፤ ሰባትም ካህናት ሰባት ቀንደ መለከት ወስደው በእግዚአብሔር ታቦት ፊት ይሂዱ” አላቸው። 7ሕዝቡንም፥ “ሂዱ፤ ከተማዪቱንም ዙሩ፤ ተዋጊዎችም ከጦር መሣሪያዎቻቸው ጋር በእግዚአብሔር ታቦት ፊት ይሂዱ ብላችሁ እዘዙአቸው” አላቸው።
8በእግዚአብሔርም ፊት ይሄዱ ዘንድ ኢያሱ እንደ ነገራቸው ሰባቱ ካህናት የተቀደሱ ሰባቱን ቀንደ መለከት ይዘው ሄዱ፤ በሄዱም ጊዜ አሰምተው በምልክት ነፉ፤ የእግዚአብሔርም የሕጉ ታቦት ትከተላቸው ነበር። 9ሰልፈኞችም ፊት ፊት ይሄዱ ነበር፤ ካህናቱም ነጋሪት ይመቱ ነበር፤ ከታቦቱ በኋላ ይከተሉ የነበሩትም ቀንደ መለከቱን እየነፉ ይሄዱ ነበር። 10ኢያሱም ሕዝቡን፦ እንዳይጮኹ ማንም ድምፃቸውን እንዳይሰማ፥ እንዲጮኹ እስኪያዛቸውም ድረስ ከአፋቸው ቃል እንዳይወጣ አዘዛቸው። 11የእግዚአብሔርም የቃል ኪዳኑ ታቦት ሄደች፤ ከተማዪቱንም ዞረች፤ ወደ ሰፈርም ተመልሳ በዚያ አደረች።#ዕብ. “እንዲሁ የእግዚአብሔርን ታቦት አንድ ጊዜ ከተማዪቱን አዙረው፥ እነርሱም ወደ ሰፈሩ ተመልሰው አደሩ” ይላል።
12ኢያሱም በማግሥቱ ማለዳ ተነሣ፤ ካህናቱም የእግዚአብሔርን የሕጉን ታቦት ተሸከሙ። 13ሰባቱም ካህናት ሰባቱን ቀንደ መለከት ይዘው በእግዚአብሔር ታቦት ፊት ይሄዱ ነበር፤ ቀንደ መለከቱንም ይነፉ ነበር፤ ተዋጊዎችም በፊታቸው ይሄዱ ነበር፤ የቀሩትም ሕዝብ ከእግዚአብሔር የቃል ኪዳን ታቦት በኋላ ይሄዱ ነበር፤ ካህናቱም ቀንደ መለከቱን ይነፉ ነበር። 14በሁለተኛውም ቀን የቀረው ሕዝብ ሁሉ ከተማዪቱን አንድ ጊዜ ዞረው ወደ ሰፈር ተመለሱ፤ ስድስት ቀንም እንዲህ አደረጉ።
15በሰባተኛውም ቀን በነጋ ጊዜ ማልደው ተነሡ፤ እንደዚህም ከተማዪቱን ሰባት ጊዜ ዞሩ፤ በዚያም ቀን ብቻ ከተማዪቱን ሰባት ጊዜ ዞሩ። 16እንዲህም ሆነ፤ ከተማዪቱን ሰባት ጊዜ በዞሩና ካህናቱ ቀንደ መለከቱን በነፉ ጊዜ፤ ኢያሱ ለእስራኤል ልጆች አለ፥ “እግዚአብሔር ከተማዪቱን ሰጥቶአችኋልና ጩኹ። 17ከተማዪቱም በእርስዋም ያለው ሁሉ ለሠራዊት ጌታ ለእግዚአብሔር እርም ይሆናሉ፤ የላክናቸውን መልእክተኞች ስለ ሸሸገች#“የላክናቸውን መልእክተኞች ስለ ሸሸገች” የሚለው በግሪክ ሰባ. ሊ. የለም። ዘማዊቱ ረዓብ፥ ከእርስዋም ጋር በቤቷ ውስጥ ያሉ ሁሉ ብቻ በሕይወት ይኖራሉ። 18እናንተ ግን እርም ብለን ከተውነው እንዳትወስዱ ተጠንቀቁ፤ ከእርሱም ተመኝታችሁ አትውሰዱ፤ ብትወስዱ ግን የእስራኤልን ሰፈር የተረገመች ታደርጓታላችሁ፤ እኛንም ታጠፉናላችሁ። 19ነገር ግን ብርና ወርቅ ሁሉ፥ የናስና የብረትም ዕቃ ለእግዚአብሔር የተቀደሰ ይሁን፤ ወደ እግዚአብሔርም ግምጃ ቤት ይግባ።” 20ሕዝቡም ጮኹ፥#“ሕዝቡም ጮኹ” የሚለው በግሪክ ሰባ. ሊ. የለም። ካህናቱም ቀንደ መለከቱን ነፉ፤ ሕዝቡም የቀንደ መለከቱን ድምፅ በሰሙ ጊዜ ታላቅ ጩኸት ጮኹ፤ ቅጥሩም ወደቀ፤ ሕዝቡም ሁሉ ወደ ከተማዪቱ ገቡ፤ ሁሉም ወደ ፊታቸው ወደ ከተማዪቱ ሮጡ፤ ከተማዪቱንም እጅ አደረጉ። 21ኢያሱም ከተማዋን፥ በከተማዪቱም ውስጥ የነበሩትን ሁሉ፥ ከወንድ እስከ ሴት፥ ከሕፃን እስከ ሽማግሌ፥ ከበሬ እስከ በግና እስከ አህያ በሰይፍ ስለት ፈጽሞ አጠፋ።
22ኢያሱም ምድሪቱን የሰለሉ ሁለቱን ሰዎች፥ “ወደ ዘማዪቱ ቤት ግቡ፤ ከዚያም ሴቲቱንና ያላትን ሁሉ እንደማላችሁላት አውጡ” አላቸው። 23እነዚያም ከተማዪቱን የሰለሉ ሁለቱ ጐልማሶች ወደ ዘማዪቱ ረዓብ ቤት ገብተው ረዓብን፥ አባቷንና እናቷን፥ ወንድሞችዋንም፥ ያላትንም ሁሉ፥ ቤተ ዘመዶችዋንም ሁሉ አወጡአቸው፤ ከእስራኤልም ሰፈር በውጭ አስቀመጡአቸው።
24ከተማዪቱንም፥ በእርስዋም የነበረውን ሁሉ በእሳት አቃጠሉ፤ ነገር ግን ብሩንና ወርቁን፥ የናሱንና የብረቱንም ዕቃ በእግዚአብሔር ግምጃ ቤት ውስጥ አገቡ። 25ኢያሪኮን ሊሰልሉ ኢያሱ የላካቸውንም መልእክተኞች ስለ ሸሸገች ዘማዊቱን ረዓብን፥ የአባቷንም ቤተ ሰብ፥ ያላትንም ሁሉ ኢያሱ አዳናቸው፤ እርስዋም በእስራኤል መካከል እስከ ዛሬ ድረስ ተቀምጣለች።
26በዚያችም ቀን ኢያሱ፥ “ይህችን ከተማ ኢያሪኮን ለመሥራት የሚነሣ ሰው በእግዚአብሔር ፊት ርጉም ይሁን፤ መሠረቷን በበኵር ልጁ የሚጥል፥ በሮችዋንም በታናሹ ልጁ የሚያቆም ርጉም ይሁን” ብሎ ማለ።#ግሪክ ሰባ. ሊ. “የቤቴሉ ኦዛን በበኵር ልጁ በአቤሮን መሠረቷን ጣለ ፤ በሕይወት በነበረው በታናሹ ልጁም በሮችዋን አቆመ” የሚል ይጨምራል። 27እግዚአብሔርም ከኢያሱ ጋር ነበረ፤ ስሙም በምድር ሁሉ ላይ ደረሰ።
Currently Selected:
መጽሐፈ ኢያሱ ወልደ ነዌ 6: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ