ዳግመኛም እንዲህ አለ፥ “አንድ ሰው ሁለት ልጆች ነበሩት። ታናሹ ልጁም አባቱን፦ ‘አባቴ ሆይ፥ ከገንዘብህ የሚደርሰኝን ከፍለህ ስጠኝ’ አለው፤ ገንዘቡንም ከፍሎ ሰጠው። ከጥቂት ቀን በኋላም ያ ትንሹ ልጁ ገንዘቡን ሁሉ ሰብስቦ ወደ ሩቅ ሀገር ሄደ፤ በዚያም በመዳራት እየኖረ ገንዘቡን ሁሉ በተነ፤ አጠፋም። ገንዘቡንም ሁሉ በጨረሰ ጊዜ፥ በዚያ ሀገር ጽኑ ራብ መጣ፤ እርሱም ተቸገረ። ሄዶም ከዚያ ሀገር ሰዎች ለአንዱ ተቀጠረ፤ እሪያዎችንም ይጠብቅ ዘንድ ወደ እርሻው ቦታ ሰደደው። እሪያዎች ከሚመገቡት ተረንቃሞም ይጠግብ ዘንድ ተመኘ፤ ግን የሚሰጠው አልነበረም። በልቡም እንዲህ ብሎ ዐሰበ፦ እህል የሚተርፋቸው የአባቴ ሠራተኞች ምን ያህል ናቸው? እኔ ግን በዚህ በረኃብ ልሞት ነው። ተነሥቼ ወደ አባቴ ልሂድና እንዲህ ልበለው፦ ‘አባቴ ሆይ፥ በሰማይም፥ በፊትህም በደልሁ። እንግዲህ ወዲህስ ልጅህ ልባል አይገባኝም፤ ከአገልጋዮችህ እንደ አንዱ አድርገኝ።’ ተነሥቶም ወደ አባቱ ሄደ፤ አባቱም ከሩቅ አየውና ራራለት፤ ሮጦም አንገቱን አቅፎ ሳመው። ልጁም፦ ‘አባቴ ሆይ፥ በሰማይም፥ በፊትህም በደልሁ፤ ከእንግዲህ ወዲህ ልጅህ ልባል አይገባኝም፤ ነገር ግን ከአገልጋዮችህ እንደ አንዱ አድርገኝ’ አለው። አባቱም አገልጋዮቹን እንዲህ አላቸው፦ ‘ያማሩ ልብሶችን ቶሎ አምጡና አልብሱት፤ ለጣቱም ቀለበት፥ ለእግሩም ጫማ አድርጉለት፤’ የሰባውን ፍሪዳም አምጡና እረዱ፤ እንብላ፤ ደስም ይበለን። ይህ ልጄ ሞቶ ነበር፤ አሁን ግን ሕያው ሆኖአልና፥ ጠፍቶም ነበር፤ ተገኝቶአልና ደስ ይላቸውም ጀመር። “ታላቁ ልጁም በእርሻ ነበርና ተመልሶ ወደ ቤቱ አጠገብ በደረሰ ጊዜ የዘፈኑንና የመሰንቆውን ድምፅ ሰማ። ከአባቱ ብላቴኖችም አንዱን ጠርቶ፦ ‘ይህ የምሰማው ምንድን ነው?’ አለው። እርሱም፦ ‘ወንድምህ ከሄደበት መጣ፤ አባትህም የሰባውን ፍሪዳ አረደ፤ በሕይወት አግኝቶታልና’ አለው። ተቈጥቶም ‘አልገባም’ አለ፤ አባቱም ወጥቶ ማለደው። መልሶም አባቱን እንዲህ አለው፦ ‘እነሆ፥ ይህን ያህል ዓመት ተገዛሁልህ፤ ፈጽሞ ከትእዛዝህ አልወጣሁም፤ ለእኔ ግን ከባልንጀሮች ጋር ደስ እንዲለኝ አንድ የፍየል ጠቦት እንኳ አልሰጠኸኝም። ከአመንዝሮች ጋር ገንዘብህን ሁሉ የጨረሰ ይህ ልጅህ በተመለሰ ጊዜ ግን የሰባውን ፍሪዳ አረድህለት።’ አባቱም እንዲህ አለው፦ ‘ልጄ አንተማ እኮ ዘወትር ከእኔ ጋር ነህ፤ የእኔ የሆነው ሁሉ የአንተ ነው። ነገር ግን ይህ ወንድምህ ሞቶ ነበረ፤ ሕያው ሆኖአልና፥ ጠፍቶም ተገኝቶአልና፥ ደስ ሊለን፥ ሐሤትም ልናደርግ ይገባል።”
የሉቃስ ወንጌል 15 ያንብቡ
ያዳምጡ የሉቃስ ወንጌል 15
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የሉቃስ ወንጌል 15:11-32
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos