ሉቃስ 15:11-32
ሉቃስ 15:11-32 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ደግሞም ኢየሱስ እንዲህ አላቸው፤ “አንድ ሰው ሁለት ልጆች ነበሩት። ከእነርሱም ታናሹ ልጅ አባቱን፣ ‘አባቴ ሆይ፤ ከሀብትህ ድርሻዬን ስጠኝ’ አለው፤ አባትየውም ሀብቱን ለልጆቹ አካፈላቸው። “ብዙም ቀን ሳይቈይ፣ ታናሹ ልጅ ድርሻውን ሁሉ ጠቅልሎ ወደ ሩቅ አገር ሄደ፤ በዚያም በማጋጣነት ንብረቱን አባከነ። እርሱም ያለውን ሁሉ ከጨረሰ በኋላ፣ በዚያ አገር ሁሉ ጽኑ ራብ ሆነ፤ ይቸገርም ጀመር። ስለዚህ ከዚያ አገር ነዋሪዎች አንዱን ተጠጋ፤ ሰውየውም ዐሣማ እንዲቀልብለት ወደ ዕርሻው ላከው። ዐሣማዎቹ የሚመገቡትን ዐሠር እንኳ ለመብላት ይመኝ ነበር፤ ነገር ግን ይህን እንኳ የሚሰጠው ሰው አልነበረም። “ልብ በገዛ ጊዜ ግን እንዲህ አለ፤ ‘ስንቱ የአባቴ ሠራተኛ ምግብ ተርፎታል፤ እኔ ግን እዚህ በራብ ልሞት ተቃርቤአለሁ ተነሥቼ ወደ አባቴ ልሂድና፣ እንዲህ ልበለው፤ አባቴ ሆይ፤ በሰማይና በአንተ ፊት በድያለሁ፤ ከእንግዲህ ልጅህ ተብዬ ልጠራ አይገባኝም፤ ከተቀጠሩት አገልጋዮችህ እንደ አንዱ ቍጠረኝ።’ ስለዚህም ተነሥቶ ወደ አባቱ ሄደ። “ነገር ግን፣ እርሱ ገና ሩቅ ሳለ፣ አባቱ አይቶት ራራለት፤ ወደ እርሱም እየሮጠ ሄዶ ዐቅፎ ሳመው። “ልጁም፣ ‘አባቴ ሆይ፤ በሰማይና በአንተ ፊት በድያለሁ፤ ከእንግዲህ ልጅህ ተብዬ ልጠራ አይገባኝም’ አለው። “አባቱ ግን ባሮቹን እንዲህ አላቸው፤ ‘ፈጥናችሁ ከሁሉ ምርጥ የሆነውን ልብስ አምጡና አልብሱት፤ ለጣቱ ቀለበት፣ ለእግሩም ጫማ አድርጉለት፤ የሠባውንም ፍሪዳ አምጡና ዕረዱ፤ እንብላ፤ እንደሰት፤ ይህ ልጄ ሞቶ ነበር፤ አሁን ግን ሕያው ሆኗል፤ ጠፍቶም ነበር፤ ተገኝቷል።’ ከዚያም ይደሰቱ ጀመር። “በዚህ ጊዜ ታላቁ ልጅ በዕርሻ ቦታ ነበረ፤ ከዚያም ተመልሶ ወደ ቤት በተቃረበ ጊዜ፣ የሙዚቃና የጭፈራ ድምፅ ሰማ፤ እርሱም ከብላቴኖቹ አንዱን ጠርቶ ነገሩ ምን እንደ ሆነ ጠየቀው። አገልጋዩም፣ ‘ወንድምህ መጥቷል፤ በሰላም በጤና ስለ መጣም አባትህ የሠባውን ፍሪዳ ዐርዶለታል’ አለው። “ታላቅ ወንድሙም ተቈጣ፤ ወደ ቤትም መግባት አልፈለገም፤ አባቱም ወደ ውጭ ወጥቶ እንዲገባ ለመነው። እርሱ ግን መልሶ አባቱን እንዲህ አለው፤ ‘እነሆ፤ ይህን ያህል ዘመን እንደ ባሪያ አገልግዬሃለሁ፤ ከትእዛዝህም አንዱን እንኳ አላጓደልሁም፤ አንተ ግን ከባልንጀሮቼ ጋራ እንድደሰት አንዲት የፍየል ግልገል እንኳ አልሰጠኸኝም፤ ነገር ግን ይህ ልጅህ ንብረትህን ከጋለሞቶች ጋራ አውድሞ ሲመጣ፣ የሠባውን ፍሪዳ ዐረድህለት።’ “አባቱም እንዲህ አለው፤ ‘ልጄ ሆይ፤ አንተ ሁልጊዜ ከእኔ ጋራ ነህ፤ የእኔ የሆነው ሁሉ የአንተ ነው፤ ይህ ወንድምህ ግን ሞቶ ነበር፤ ሕያው ሆነ፤ ጠፍቶ ነበር ተገኘ፤ ስለዚህ ደስ ሊለንና ፍሥሓ ልናደርግ ይገባናል።’ ”
ሉቃስ 15:11-32 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ዳግመኛም እንዲህ አለ፥ “አንድ ሰው ሁለት ልጆች ነበሩት። ታናሹ ልጁም አባቱን፦ ‘አባቴ ሆይ፥ ከገንዘብህ የሚደርሰኝን ከፍለህ ስጠኝ’ አለው፤ ገንዘቡንም ከፍሎ ሰጠው። ከጥቂት ቀን በኋላም ያ ትንሹ ልጁ ገንዘቡን ሁሉ ሰብስቦ ወደ ሩቅ ሀገር ሄደ፤ በዚያም በመዳራት እየኖረ ገንዘቡን ሁሉ በተነ፤ አጠፋም። ገንዘቡንም ሁሉ በጨረሰ ጊዜ፥ በዚያ ሀገር ጽኑ ራብ መጣ፤ እርሱም ተቸገረ። ሄዶም ከዚያ ሀገር ሰዎች ለአንዱ ተቀጠረ፤ እሪያዎችንም ይጠብቅ ዘንድ ወደ እርሻው ቦታ ሰደደው። እሪያዎች ከሚመገቡት ተረንቃሞም ይጠግብ ዘንድ ተመኘ፤ ግን የሚሰጠው አልነበረም። በልቡም እንዲህ ብሎ ዐሰበ፦ እህል የሚተርፋቸው የአባቴ ሠራተኞች ምን ያህል ናቸው? እኔ ግን በዚህ በረኃብ ልሞት ነው። ተነሥቼ ወደ አባቴ ልሂድና እንዲህ ልበለው፦ ‘አባቴ ሆይ፥ በሰማይም፥ በፊትህም በደልሁ። እንግዲህ ወዲህስ ልጅህ ልባል አይገባኝም፤ ከአገልጋዮችህ እንደ አንዱ አድርገኝ።’ ተነሥቶም ወደ አባቱ ሄደ፤ አባቱም ከሩቅ አየውና ራራለት፤ ሮጦም አንገቱን አቅፎ ሳመው። ልጁም፦ ‘አባቴ ሆይ፥ በሰማይም፥ በፊትህም በደልሁ፤ ከእንግዲህ ወዲህ ልጅህ ልባል አይገባኝም፤ ነገር ግን ከአገልጋዮችህ እንደ አንዱ አድርገኝ’ አለው። አባቱም አገልጋዮቹን እንዲህ አላቸው፦ ‘ያማሩ ልብሶችን ቶሎ አምጡና አልብሱት፤ ለጣቱም ቀለበት፥ ለእግሩም ጫማ አድርጉለት፤’ የሰባውን ፍሪዳም አምጡና እረዱ፤ እንብላ፤ ደስም ይበለን። ይህ ልጄ ሞቶ ነበር፤ አሁን ግን ሕያው ሆኖአልና፥ ጠፍቶም ነበር፤ ተገኝቶአልና ደስ ይላቸውም ጀመር። “ታላቁ ልጁም በእርሻ ነበርና ተመልሶ ወደ ቤቱ አጠገብ በደረሰ ጊዜ የዘፈኑንና የመሰንቆውን ድምፅ ሰማ። ከአባቱ ብላቴኖችም አንዱን ጠርቶ፦ ‘ይህ የምሰማው ምንድን ነው?’ አለው። እርሱም፦ ‘ወንድምህ ከሄደበት መጣ፤ አባትህም የሰባውን ፍሪዳ አረደ፤ በሕይወት አግኝቶታልና’ አለው። ተቈጥቶም ‘አልገባም’ አለ፤ አባቱም ወጥቶ ማለደው። መልሶም አባቱን እንዲህ አለው፦ ‘እነሆ፥ ይህን ያህል ዓመት ተገዛሁልህ፤ ፈጽሞ ከትእዛዝህ አልወጣሁም፤ ለእኔ ግን ከባልንጀሮች ጋር ደስ እንዲለኝ አንድ የፍየል ጠቦት እንኳ አልሰጠኸኝም። ከአመንዝሮች ጋር ገንዘብህን ሁሉ የጨረሰ ይህ ልጅህ በተመለሰ ጊዜ ግን የሰባውን ፍሪዳ አረድህለት።’ አባቱም እንዲህ አለው፦ ‘ልጄ አንተማ እኮ ዘወትር ከእኔ ጋር ነህ፤ የእኔ የሆነው ሁሉ የአንተ ነው። ነገር ግን ይህ ወንድምህ ሞቶ ነበረ፤ ሕያው ሆኖአልና፥ ጠፍቶም ተገኝቶአልና፥ ደስ ሊለን፥ ሐሤትም ልናደርግ ይገባል።”
ሉቃስ 15:11-32 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
እንዲህም አለ፦ አንድ ሰው ሁለት ልጆች ነበሩት። ከእነርሱም ታናሹ አባቱን፦ አባቴ ሆይ፥ ከገንዘብህ የሚደርሰኝን ክፍል ስጠኝ አለው። ገንዘቡንም አካፈላቸው። ከጥቂት ቀንም በኋላ ታናሹ ልጅ ገንዘቡን ሁሉ ሰብስቦ ወደ ሩቅ አገር ሄደ፥ ከዚያም እያባከነ ገዘቡን በተነ። ሁሉንም ከከሰረ በኋላ በዚያች አገር ጽኑ ራብ ሆነ፥ እርሱም ይጨነቅ ጀመር። ሄዶም ከዚያች አገር ሰዎች ከአንዱ ጋር ተዳበለ፥ እርሱም እሪያ ሊያሰማራ ወደ ሜዳ ሰደደው። እሪያዎችም ከሚበሉት አሰር ሊጠግብ ይመኝ ነበር፥ የሚሰጠውም አልነበረም። ወደ ልቡም ተመልሶ እንዲህ አለ፦ እንጀራ የሚተርፋቸው የአባቴ ሞያተኞች ስንት ናቸው? እኔ ግን ከዚህ በራብ እጠፋለሁ። ተነሥቼም ወደ አባቴ እሄዳለሁና፦ አባቴ ሆይ፥ በሰማይና በፊትህ በደልሁ፥ ወደ ፊትም ልጅህ ልባል አይገባኝም፤ ከሞያተኞችህ እንደ አንዱ አድርገኝ እለዋለሁ። ተነሥቶም ወደ አባቱ መጣ። እርሱም ገና ሩቅ ሳለ አባቱ አየውና አዘነለት፥ ሮጦም አንገቱን አቀፈውና ሳመው። ልጁም፦ አባቴ ሆይ፥ በሰማይና በፊትህ በደልሁ፥ ወደ ፊትም ልጅህ ልባል አይገባኝም አለው። አባቱ ግን ባሪያዎቹን አለ፦ ፈጥናችሁ ከሁሉ የተሻለ ልብስ አምጡና አልብሱት፥ ለእጁ ቀለበት ለእግሩም ጫማ ስጡ፤ የሰባውን ፊሪዳ አምጥታችሁ እረዱት፥ እንብላም ደስም ይበለን፤ ይህ ልጄ ሞቶ ነበርና ደግሞም ሕያው ሆኖአል፤ ጠፍቶም ነበር ተገኝቶአልም። ደስም ይላቸው ጀመር። ታላቁ ልጁ በእርሻ ነበረ፤ መጥቶም ወደ ቤት በቀረበ ጊዜ የመሰንቆና የዘፈን ድምፅ ሰማ፤ ከብላቴናዎችም አንዱን ጠርቶ፦ ይህ ምንድር ነው? ብሎ ጠየቀ። እርሱም፦ ወንድምህ መጥቶአልና በደኅና ስላገኘው አባትህ የሰባውን ፊሪዳ አረደለት አለው። ተቈጣም ሊገባም አልወደደም፤ አባቱም ወጥቶ ለመነው። እርሱ ግን መልሶ አባቱን፦ እነሆ፥ ይህን ያህል ዓመት እንደ ባሪያ ተገዝቼልሃለሁ ከትእዛዝህም ከቶ አልተላለፍሁም፤ ለእኔም ከወዳጆቼ ጋር ደስ እንዲለኝ አንድ ጥቦት ስንኳ አልሰጠኸኝም፤ ነገር ግን ገንዘብህን ከጋለሞቶች ጋር በልቶ ይህ ልጅህ በመጣ ጊዜ፥ የሰባውን ፊሪዳ አረድህለት አለው። እርሱ ግን፦ ልጄ ሆይ፥ አንተ ሁልጊዜ ከእኔ ጋር ነህ፥ ለእኔም የሆነ ሁሉ የአንተ ነው፤ ዳሩ ግን ይህ ወንድምህ ሞቶ ነበረ ሕያው ስለ ሆነ ጠፍቶም ነበር ስለ ተገኘ ደስ እንዲለን ፍሥሐም እንድናደርግ ይገባናል አለው።
ሉቃስ 15:11-32 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ቀጥሎም ኢየሱስ እንዲህ አለ፤ “አንድ ሰው ሁለት ልጆች ነበሩት፤ ታናሽዮው አባቱን ‘አባባ፥ ከሀብትህ ከፍለህ ድርሻዬን ስጠኝ’ አለው። ስለዚህ አባትየው ሀብቱን ለሁለት ልጆቹ አካፈለ። ከጥቂት ቀን በኋላ ታናሽዮው ገንዘቡን ሁሉ ሰብስቦ ወደ ሩቅ አገር ሄደ፤ በዚያም አገር ገንዘቡን ሁሉ በከንቱ አባከነ። ገንዘቡንም ሁሉ ከጨረሰ በኋላ በዚያ አገር ብርቱ ራብ በመግባቱ በችግር ላይ ወደቀ። ስለዚህ ከዚያ አገር ሰዎች ወደ አንዱ ተጠጋ፤ ሰውየውም የዐሣማ እረኛ አደረገው። ዐሣማዎቹ ከሚመገቡት ብጣሪ ዐሠር ሆዱን ለመሙላት ይመኝ ነበር፤ ግን ይህንኑ እንኳ የሚሰጠው አልነበረም። በዚህ ጊዜ ልጁ ስሕተቱን ተገንዝቦ እንዲህ ሲል አሰበ፤ ‘በአባቴ ቤት ተቀጥረው የሚሠሩ አገልጋዮች እንጀራ እስኪጠግቡ በልተው የሚተርፋቸው ስንት ናቸው! እኔ ግን እዚህ በረሀብ መሞቴ ነው፤ ተነሥቼ ወደ አባቴ ልሂድና፦ አባባ፥ በእግዚአብሔርና በአንተ ፊት በድያለሁ፤ ከእንግዲህ ወዲህ ያንተ ልጅ ልባል አይገባኝም፤ ነገር ግን ከቅጥረኞች አገልጋዮችህ እንደ አንዱ አድርገኝ ልበለው።’ ስለዚህ ተነሥቶ ወደ አባቱ ሄደ። “አባቱም ገና በሩቅ ሳለ ልጁን አየው፤ ራርቶለትም ወደ እርሱ ሮጠ፤ ዕቅፍ አድርጎም ሳመው። ልጁም ‘አባባ፥ በእግዚአብሔርና በአንተ ፊት በድያለሁ፤ ከእንግዲህ ወዲህ ልጅህ ልባል አይገባኝም’ አለ። አባቱ ግን አገልጋዮቹን ጠርቶ እንዲህ አለ፦ ‘ቶሎ ብላችሁ ከሁሉ የበለጠውን ልብስ አምጡና አልብሱት! በጣቱ ቀለበት፥ በእግሩም ጫማ አድርጉለት! የሰባውን ወይፈን አምጡና ዕረዱ! እንብላ! እንደሰት! ይህ ልጄ ሞቶ ነበር፥ እነሆ፥ አሁን በሕይወት አለ፤ ጠፍቶ ነበር፤ ተገኘ’፤ መደሰትም ጀመሩ። “በዚህ ጊዜ ታላቁ ልጅ ለሥራ ወደ እርሻ ወጥቶ ነበር፤ ተመልሶ ሲመጣ ወደ ቤቱ በተቃረበ ጊዜ የሙዚቃና የጭፈራ ድምፅ ሰማ፤ ከአገልጋዮቹ አንዱን ጠርቶ ‘ምንድን ነው ነገሩ?’ ብሎ ጠየቀው። አገልጋዩም ‘ወንድምህ ተመልሶ ስለ መጣ ነው፤ አባትህ በደኅና ስላገኘው የሰባውን ወይፈን ዐርዶለታል’ አለው። “ታላቅ ወንድሙም በጣም ተቈጥቶ፥ ‘ወደ ቤት አልገባም’ አለ። ስለዚህ አባቱ ወደ ደጅ ወጥቶ እንዲገባ ለመነው፤ ልጁ ግን ለአባቱ እንዲህ ሲል መለሰ፤ ‘እነሆ! ይህን ያኽል ዓመት አገለገልኩህ፤ ከትእዛዝህም ከቶ ዝንፍ ብዬ አላውቅም፤ ታዲያ እኔ ከጓደኞቼ ጋር የምደሰትበት አንድ ጠቦት እንኳ ሰጥተኸኝ አታውቅም! ይህ ልጅህ ግን ሀብትህን ከአመንዝራ ሴቶች ጋር አባክኖ በተመለሰ ጊዜ የሰባውን ወይፈን ዐረድክለት።’ አባቱም እንዲህ አለው፤ ‘ልጄ ሆይ፥ አንተ ሁልጊዜ ከእኔ ጋር ነህ፤ የእኔ የሆነ ሁሉ የአንተ ነው። ይህ ወንድምህ ግን ሞቶ ነበር፤ አሁን በሕይወት አለ፤ ጠፍቶ ነበር፤ አሁን ተገኘ፤ ስለዚህ በጣም ልንደሰት ይገባናል።’ ”
ሉቃስ 15:11-32 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
እንዲህም አለ “አንድ ሰው ሁለት ልጆች ነበሩት። ከእነርሱም ታናሹ አባቱን ‘አባቴ ሆይ! ከገንዘብህ የሚደርሰኝን ክፍል ስጠኝ፤’ አለው። ገንዘቡንም አካፈላቸው። ከጥቂት ቀንም በኋላ ታናሹ ልጅ ገንዘቡን ሁሉ ሰብስቦ ወደ ሩቅ አገር ሄደ፤ ከዚያም እያባከነ ገንዘቡን በተነ። ሁሉንም ከከሰረ በኋላ በዚያች አገር ጽኑ ራብ ሆነ፤ እርሱም ይጨነቅ ጀመር። ሄዶም ከዚያች አገር ሰዎች አንዱ ጋር ተጠጋ፤ እርሱም ዐሣማ እንዲያሰማራ ወደ ሜዳ ላከው። ዐሣማዎችም ከሚበሉት ፍልፋይ ለመጥገብ ይመኝ ነበር፤ የሚሰጠውም አልነበረም። ወደ ልቡም ተመልሶ እንዲህ አለ ‘ምግብ የሚተርፋቸው የአባቴ ተቀጣሪዎች ስንት ናቸው? እኔ ግን ከዚህ በራብ እጠፋለሁ። ተነሥቼም ወደ አባቴ እሄዳለሁና “አባቴ ሆይ! በሰማይና በፊትህ በደልሁ፤ ወደፊትም ልጅህ ልባል አይገባኝም፤ ከተቀጣሪዎችህ እንደ አንዱ አድርገኝ፤”’ እለዋለሁ። ተነሥቶም ወደ አባቱ መጣ። እርሱም ገና ሩቅ ሳለ አባቱ አየውና አዘነለት፤ ሮጦም አንገቱን አቀፈውና ሳመው። ልጁም ‘አባቴ ሆይ! በሰማይና በፊትህ በደልሁ፤ ወደፊትም ልጅህ ልባል አይገባኝም፤’ አለው። አባቱ ግን አገልጋዮቹን እንዲህ አላቸው ‘ፈጥናችሁ ከሁሉ የተሻለ ልብስ አምጡና አልብሱት፤ በጣቱ ቀለበት በእግሩም ጫማ አጥልቁለት፤ የሰባውን ፍሪዳ አምጥታችሁ እረዱት፤ እንብላም ደስም ይበለን፤ ይህ ልጄ ሞቶ ነበርና ደግሞም ሕያው ሆኖአል፤ ጠፍቶም ነበር ተገኝቶአልም።’ ደስ ይላቸውም ጀመር። “ታላቁ ልጁ በእርሻ ነበረ፤ መጥቶም ወደ ቤት በቀረበ ጊዜ የሙዚቃና የውዝዋዜ ድምፅ ሰማ፤ ከአገልጋዮቹም አንዱን ጠርቶ ‘ይህ ምንድነው?’ ብሎ ጠየቀ። እርሱም ‘ወንድምህ መጥቷል፤ በደኅና ስላገኘውም አባትህ የሰባውን ፍሪዳ አረደለት፤’ አለው። እርሱም ተቈጣ፤ ሊገባም አልፈለገም፤ አባቱም ወጥቶ ለመነው። እርሱ ግን መልሶ አባቱን ‘እነሆ፥ ይህን ያህል ዓመት አገለገልኩህ፤ ከትእዛዝህም ከቶ አልተላለፍሁም፤ ከወዳጆቼ ጋር እንድደሰት ለእኔ አንድ ጥቦት እንኳን ሰጥተኸኝ አታውቅም፤ ነገር ግን ይህ ልጅህ ገንዘብህን ከአመንዝራ ሴቶች ጋር አባክኖ በመጣ ጊዜ፥ የሰባውን ፍሪዳ አረድህለት፤’ አለው። እርሱ ግን እንዲህ አለው፦ ‘ልጄ ሆይ! አንተ ሁልጊዜ ከእኔ ጋር ነህ፤ ለእኔም የሆነ ሁሉ የአንተ ነው፤ ዳሩ ግን ይህ ወንድምህ ሞቶ ነበረ፤ ሕያው ስለ ሆነ ጠፍቶም ነበር፤ ስለ ተገኘ ደስ እንዲለን ፍሥሐም እንድናደርግ ይገባናል’።”