ኦሪት ዘኍልቍ 8
8
የሰባቱ መብራቶች አቀማመጥ
1እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ 2“መብራቶቹን ስታበራ ሰባቱ መብራቶች በመቅረዙ ፊት ያበራሉ ብለህ ለአሮን ንገረው።” 3አሮንም እንዲሁ አደረገ፤ እግዚአብሔር ሙሴን እንዳዘዘ በመቅረዙ ፊት መብራቶቹን አበራ። 4የመቅረዝዋም ሥራዋ እንዲህ ነበረ። ሁለንተናቸው ወርቅ የሆነ አፅቆችዋ ሥረ-ወጥ ነበሩ፤ አበቦችዋም ሁለንተናቸው ሥረ-ወጥ ነበሩ። እግዚአብሔር ሙሴን እንዳሳየው ምሳሌ መቅረዝዋን እንዲሁ አደረገ።
የሌዋውያን መቀደስና አገልግሎት
5እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ 6“ከእስራኤል ልጆች መካከል ሌዋውያንን ወስደህ አንጻቸው። 7ታነጻቸው ዘንድ እንዲህ ታደርግላቸዋለህ፤ በማንጻት ውኃ ትረጫቸዋለህ፤ ሰውነታቸውን ሁሉ ይላጩ፤ ልብሳቸውንም ይጠቡ፤ ንጹሓንም ይሆናሉ። 8ከላሞች አንድ ወይፈን፥ ለእህሉም ቍርባን በዘይት የተለወሰ መልካም ዱቄትን ይውሰዱ፤ ሌላውንም የአንድ ዓመት ወይፈን ለኀጢአት መሥዋዕት ይውሰዱ። 9ሌዋውያንንም በምስክሩ ድንኳን ፊት አቅርብ፤ የእስራኤልንም ልጆች ማኅበር ሁሉ ሰብስብ። 10ሌዋውያንንም በእግዚአብሔር ፊት አቅርባቸው፤ የእስራኤልም ልጆች በሌዋውያን ላይ እጃቸውን ይጫኑባቸው። 11አሮንም ሌዋውያን እግዚአብሔርን ያገለግሉ ዘንድ ከእስራኤል ልጆች መካከል ስጦታ አድርጎ፥ ሌዋውያንን በእግዚአብሔር ፊት ይለያቸዋል። 12ሌዋውያኑም በወይፈኖቹ ራሶች ላይ እጆቻቸውን ይጫኑ፤ ለሌዋውያንም ስለ ማስተስረያ አንዱን ለኀጢአት መሥዋዕት፥ ሁለተኛውንም ለሚቃጠል መሥዋዕት ለእግዚአብሔር አቅርብ። 13ሌዋውያንንም በአሮንና በልጆቹ ፊት አቁማቸው፤ በእግዚአብሔርም ፊት ስጦታ አድርገህ አቅርባቸው። 14እንዲሁ ሌዋውያንን ከእስራኤል ልጆች መካከል ለይ፤ እነርሱም ለእኔ ይሁኑ።
15“ከዚያም በኋላ ሌዋውያን የምስክሩን ድንኳን አገልግሎት ያገለግሉ ዘንድ ይገባሉ፤ ታነጻቸውማለህ፤ ስጦታም አድርገህ በፊቴ ታቀርባቸዋለህ። 16እነርሱም ከእስራኤል ልጆች መካከል ፈጽሞ ለእኔ ተሰጥተዋልና በእስራኤል ልጆች በኵራት ሁሉ፥ መጀመሪያ በሚወለድ ሁሉ ፋንታ ለእኔ ወስጄአቸዋለሁ። 17በግብፅ ምድር ያለውን በኵር ሁሉ በገደልሁበት ቀን የእስራኤልን ልጆች በኵራት ሁሉ፥ ሰው ወይም እንስሳ፥ ለእኔ ቀድሼአቸዋለሁና የእኔ ናቸው። 18በእስራኤልም ልጆች በኵር ሁሉ ፋንታ ሌዋውያንን ወስጄአለሁ። 19ሌዋውያንንም ስጦታ አድርጌ አገባኋቸው፤ ልዩ በሆነች ድንኳን ውስጥ የእስራኤልን ልጆች ሥራ ይሠሩ ዘንድ፥ የእስራኤልንም ልጆች ኀጢአት ያቃልሉ ዘንድ ከእስራኤል ልጆች መካከል ለአሮንና ለልጆቹ ተሰጡ፤ ከእስራኤልም ልጆች ወደ መቅደስ የሚቀርብ አይኑር።”
20ሙሴና አሮን የእስራኤልም ልጆች ማኅበር ሁሉ እንዲሁ በሌዋውያን ላይ አደረጉ፤ እግዚአብሔር ሙሴን ስለ ሌዋውያን እንዳዘዘው እንዲሁ የእስራኤል ልጆች አደረጉላቸው። 21ሌዋውያንም ከኀጢአት ራሳቸውን አነጹ፤ ልብሳቸውንም አጠቡ፤ አሮንም ስጦታ አድርጎ በእግዚአብሔር ፊት አቀረባቸው፤ አሮንም ያነጻቸው ዘንድ አስተሰረየላቸው። 22ከዚያም በኋላ ሌዋውያን በምስክሩ ድንኳን ውስጥ በአሮንና በልጆቹ ፊት አገልግሎታቸውን ይፈጽሙ ዘንድ ገቡ፤ እግዚአብሔር ሙሴን ስለ ሌዋውያን እንዳዘዘው እንዲሁ አደረጉላቸው።
23እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ 24“የሌዋውያን ሕግ ይህ ነው፤ ከሃያ አምስት ዓመት ጀምሮ ከዚያም በላይ ያሉት እስከ አምሳ ዓመት ድረስ በምስክሩ ድንኳን ሥራ ያገለግሉ ዘንድ ይገባሉ። 25ከአምሳ ዓመት በኋላ ከሥራው ይሰናበት። ከዚያም ወዲያ እርሱ አያገልግል። 26ወንድሙንም በምስክሩ ድንኳን ውስጥ ያገልግል፤ ሰሞናቸውንም ይጠብቅ። ነገር ግን አገልግሎቱን ይተው። እንዲሁ በየሰሞናቸው ለሌዋውያን ታደርጋለህ።”
Currently Selected:
ኦሪት ዘኍልቍ 8: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ