መዝሙረ ዳዊት 48
48
ለመዘምራን አለቃ የቆሬ ልጆች መዝሙር።
1አሕዛብ ሁላችሁ፥ ይህን ስሙ፤
በዓለም የምትኖሩም ሁላችሁ፥ አድምጡ፤
2የሰው ልጆች ባለጠጎችና ድሆች፥ በየሀገራችሁ በአንድነት።
3አፌ ጥበብን ይናገራል፥
የልቤም ዐሳብ ምክርን፥
4በጆሮዬ ምሳሌ አደምጣለሁ፥
በበገናም ነገሬን እገልጣለሁ።
5ከክፉ ቀን ለምን እፈራለሁ?
ኀጢአት ተረከዜን ከበበኝ፤
6በኀይላቸው የሚታመኑ፥
በባለጠግነታቸውም ብዛት የሚኮሩ፤
7ወንድም ወንድሙን አያድንም፥ ሰውም አያድንም፤
ቤዛውንም ለእግዚአብሔር አይሰጥም፥
8የነፍሱንም ዋጋ ለውጥ፥
9በዓለም የደከመ ለዘለዓለም ይድናል፥
ጥፋትን አያይምና።
10ጠቢባንን ሲሞቱ ባየሃቸው ጊዜ፥
እንደዚሁ ልብ የሌላቸው ሰነፎች ይጠፋሉ፥
ገንዘባቸውንም ለሌሎች ይተዋሉ።
11መቃብራቸው ለዘለዓለም ቤታቸው ነው፥
ማደሪያቸውም ለልጅ ልጅ ነው፤
በየሀገራቸውም ስማቸው ይጠራል።
12ሰው ግን ክቡር ሆኖ ሳለ አላወቀም፤
ልብ እንደሌላቸው እንስሶችም ሆነ፥ መሰላቸውም።
13በአፋቸው ሲወዱ፥ ራስዋ መንገዳቸው መሰናክላቸው ናት፥
14እንደ በጎች ሞት በሲኦል ይጠብቃቸዋል፥
ቅኖችም በማለዳ ይገዙአቸዋል፥
ረድኤታቸውም ከክብራቸው ተለይታ በሲኦል ትጠፋለች።
15ነገር ግን በሚወስዱኝ ጊዜ
እግዚአብሔር ነፍሴን ከሲኦል እጅ ያድናታል።
16በበለጸገ ጊዜ፥ የቤቱም ክብር በበዛ ጊዜ ሰውን አትፍራው፥
17በሚሞት ጊዜ ከእርሱ ጋር ምንም አይወስድምና፥
የቤቱም ክብር ሁሉ ከእርሱ ጋር አይወርድምና።
18በሕይወቱ ሳለ ሰውነቱ ደስ ብሎአታልና
ሰው መልካም ብታደርግለት ያመሰግንሃል።
19ወደ አባቶቹም ዓለም ይወርዳል፤
ከእንግዲህ ወዲህ ለዘለዓለም ብርሃንን አያይም።
20ሰው ግን ክቡር ሲሆን አላወቀም።
ልብ እንደሌላቸው እንስሶችም ሆነ፥ መሰላቸውም።
Currently Selected:
መዝሙረ ዳዊት 48: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ