የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ትንቢተ ዳንኤል 11

11
1እኔም በሜዶናዊው በዳርዮስ መጀመሪያ ዓመት አጸናውና አበረታው ዘንድ ቆሜ ነበር።
2አሁንም እውነትን አሳይሃለሁ። እነሆ፥ ሦስት ነገሥታት ደግሞ በፋርስ ይነሣሉ፥ አራተኛውም ከሁሉ ይልቅ እጅግ ባለጠጋ ይሆናል፥ በባለጠግነቱም በበረታ ጊዜ በግሪክ መንግሥት ላይ ሁሉን ያስነሣል። 3ኃያልም ንጉሥ ይነሣል፥ በትልቅ አገዛዝም ይገዛል፥ እንደ ፈቃዱም ያደርጋል። 4እርሱም በተነሣ ጊዜ መንግሥቱ ይሰበራል፥ እስከ አራቱ የሰማይ ነፋሳት ይከፋፈላል። ለዘሩ ግን አይከፋፈልም፥ እንደ ገዛበትም አገዛዝ አይሆንም፥ መንግሥቱ ይነቀላልና፥ ከእነዚህም ለሌሎች ይሆናልና።
5የደቡብም ንጉሥ ከአለቆቹም አንዱ ይበረታሉ፥ እርሱም ይበረታበታል ይሠለጥንማል፥ ግዛቱም ታላቅ ግዛት ይሆናል። 6ከዘመናትም በኋላ ይጋጠማሉ፥ የደቡብም ንጉሥ ሴት ልጅ ቃል ኪዳን ለማድረግ ወደ ሰሜን ንጉሥ ትመጣለች፥ የክንድዋ ኃይል ግን አይጸናም፥ እርሱና ክንዱም አይጸናም፥ እርስዋና እርስዋን ያመጡ የወለዳትም በዚያም ዘመን ያጸናት አልፈው ይሰጣሉ።
7ነገር ግን ከሥርዋ ቍጥቋጥ አንዱ በስፍራው ይነሣል፥ ወደ ሠራዊቱም ይመጣል፥ ወደ ሰሜንም ንጉሥ አምባ ይገባል፥ በላያቸውም ያደርጋል፥ ያሸንፍማል። 8አማልክቶቻቸውንና ቀልጠው የተሠሩትን ምስሎቻቸውን ከብርና ከወርቅም የተሠሩትን የከበሩትን ዕቃዎች ወደ ግብጽ ይማርካል፥ እስከ ጥቂትም ዓመት ድረስ ከሰሜን ንጉሥ ጋር ሳይዋጋ ይቀመጣል። 9ይህም ወደ ደቡብ ንጉሥ መንግሥት ይገባል፥ ነገር ግን ወደ ገዛ ምድሩ ይመለሳል።
10ልጆቹም ይዋጋሉ፥ ብዙ ሠራዊትንና ሕዝብን ይሰበስባል፥ እርሱም ይመጣል፥ ይጐርፍማል፥ ያልፍማል፥ ተመልሶም እስከ አምባው ድረስ ይዋጋል። 11የደቡብም ንጉሥ ይቈጣል ወጥቶም ከሰሜን ንጉሥ ጋር ይዋጋል፥ ብዙ ሕዝብንም ለሰልፍ ያቆማል፥ ሕዝቡም አልፎ በእጁ ይሰጣል። 12ሕዝቡም በተወሰደ ጊዜ ልቡ ይታበያል፥ አእላፋትንም ይጥላል፥ ነገር ግን አያሸንፍም። 13የሰሜንም ንጉሥ ይመለሳል፥ ከቀደመውም የበለጠ ብዙ ሕዝብ ለሰልፍ ያቆማል፥ በዘመናትና በዓመታትም ፍጻሜ ከታላቅ ሠራዊትና ከብዙ ሀብት ጋር ይመጣል። 14በዚያም ዘመን ብዙ ሰዎች በደቡብ ንጉሥ ላይ ይነሣሉ፥ ከሕዝብህም መካከል የዓመፅ ልጆች ራእዩን ያጸኑ ዘንድ ይነሣሉ፥ ነገር ግን ይወድቃሉ። 15የሰሜንም ንጉሥ ይመጣል፥ አፈርንም ይደለድላል፥ የተመሸገችንም ከተማ ይወስዳል፥ የደቡብም ሠራዊት የተመረጡትም ሕዝቡ አይቆሙም፥ ለመቋቋምም ኃይል የላቸውም። 16በእርሱም ላይ የሚመጣው ግን እንደ ፈቃዱ ያደርጋል፥ በፊቱም የሚቆም የለም፥ በመልካሚቱም ምድር ይቆማል፥ በእጁም ውስጥ ጥፋት ይሆናል። 17ከመንግሥቱም ሁሉ ኃይል ጋር ይመጣ ዘንድ ፊቱን ያቀናል፥ ከእርሱም ጋር አንድነትን ያደርጋል፥ ያረክሳትም ዘንድ ሴትን ልጅ ይሰጠዋል፥ እርስዋም አትጸናም ለእርሱም አትሆንም። 18ከዚህም በኋላ ፊቱን ወደ ደሴቶች ይመልሳል፥ ብዙዎችንም ይወስዳል፥ አንድ አለቃ ግን ስድቡን ይሽራል፥ ስድቡንም በራሱ ላይ ይመልሳል። 19ፊቱንም ወደ ገዛ ምድሩ አምባዎች ይመልሳል፥ ተሰናክሎም ይወድቃል፥ አይገኝምም።
20የዚያን ጊዜም በመንግሥቱ ክብር መካከል አስገባሪውን የሚያሳልፍ በስፍራው ይነሣል፥ ነገር ግን በቍጣው ሳይሆን በሰልፍም ሳይሆን በጥቂት ቀን ይሰበራል።
21በእርሱም ስፍራ የተጠቃ ሰው ይነሣል የመንግሥቱንም ክብር አይሰጡትም፥ በቀስታ መጥቶ መንግሥቱን በማታለል ይገዛል። 22የሚጐርፍም ሠራዊት ከፊቱ ይወሰዳል፥ እርሱና የቃል ኪዳኑ አለቃ ይሰበራሉ። 23ከእርሱም ጋር ከተወዳጀ በኋላ በተንኰል ያደርጋል፥ ከጥቂትም ሕዝብ ጋር ወጥቶ ይበረታል። 24በቀስታ ከአገር ሁሉ ወደ ለመለመችው ክፍል ይገባል፥ አባቶቹና የአባቶቹ አባቶች ያላደረጉትንም ያደርጋል፥ ብዝበዛውንና ምርኮውንም ሀብቱንም በመካከላቸው ይበትናል፥ በምሽጎችም ላይ እስከ ጊዜው ድረስ አሳቡን ይፈጥራል። 25በታላቅም ሠራዊት ሆኖ ኃይሉንና ልቡን በደቡብ ንጉሥ ላይ ያስነሣል፥ የደቡብም ንጉሥ በታላቅና በብዙ ሠራዊት ሆኖ በሰልፍ ይዋጋል፥ ነገር ግን አሳብ በእርሱ ላይ ይፈጥራሉና አይጸናም። 26መብሉንም የሚበሉ ሰዎች ይሰብሩታል፥ ሠራዊቱም ይጐርፋል፥ ብዙዎችም ተገድለው ይወድቃሉ። 27እነዚህም ሁለት ነገሥታት ክፋትን ያደርጉ ዘንድ በልባቸው ያስባሉ፥ በአንድ ገበታም ተቀምጠው ሐሰት ይናገራሉ፥ ነገር ግን ፍጻሜው እስከ ተወሰነው ጊዜ ነውና አይከናወንላቸውም።
28ከብዙም ሀብት ጋር ወደ ምድሩ ይመለሳል፥ ልቡም በተቀደሰ ቃል ኪዳን ላይ ይሆናል፥ ፈቃዱንም ያደርጋል፥ ወደ ገዛ ምድሩም ይመለሳል። 29በተወሰነውም ጊዜ ይመለሳል ወደ ደቡብም ይመጣል፥ ነገር ግን ኋለኛው እንደ ፊተኛው አይሆንም። 30የኪቲም መርከቦች ይመጡበታልና ስለዚህ አዝኖ ይመለሳል፥ በቅዱሱም ቃል ኪዳን ላይ ይቈጣል፥ ፈቃዱንም ያደርጋል፥ ተመልሶም ቅዱሱን ቃል ኪዳን የተዉትን ሰዎች ይመለከታል። 31ከእርሱም ጋር ሠራዊቶች ይቆማሉ፥ መቅደሱንም ግንቡንም ያረክሳሉ፥ የዘወትሩንም መሥዋዕት ያስቀራሉ፥ የጥፋትንም ርኵሰት ያቆማሉ። 32ቃል ኪዳኑን የሚበድሉትንም በማታለል ያስታል፥ ነገር ግን አምላካቸውን የሚያውቁ ሕዝብ ይበረታሉ፥ ያደርጋሉም። 33በሕዝቡም መካከል ያሉ ጥበበኞች ብዙ ሰዎችን ያስተምራሉ፥ ነገር ግን በሰይፍና በእሳት ነበልባል በምርኮና በመበዝበዝ ብዙ ዘመን ይወድቃሉ። 34በወደቁም ጊዜ በጥቂት እርዳታ ይረዳሉ፥ ብዙ ሰዎችም በግብዝነት ወደ እነርሱ ተባብረው ይሰበሰባሉ። 35እስከ ተወሰነውም ዘመን ይሆናልና ከጥበበኞቹ አያሌዎቹ እስከ ፍጻሜ ዘመን ይነጥሩና ይጠሩ ይነጡም ዘንድ ይወድቃሉ።
36ንጉሡም እንደ ፈቃዱ ያደርጋል፥ ራሱንም ከፍ ከፍ ያደርጋል፥ በአማልክት ሁሉ ላይ ራሱን ታላቅ ያደርጋል፥ በአማልክትም አምላክ ላይ በትዕቢት ይናገራል፥ ቍጣም እስኪፈጸም ድረስ ይከናወንለታል፥ የተወሰነው ይደረጋልና። 37የአባቶቹንም አማልክት የሴቶችንም ምኞት አይመለከትም፥ ራሱም በሁሉ ላይ ታላቅ ያደርጋልና አማልክትን ሁሉ አይመለከትም። 38በእነዚህ ፋንታ ግን የአምባዎቹን አምላክ ያከብራል፥ አባቶቹም ያላወቁትን አምላክ በወርቅና በብር በዕንቍና በከበረ ነገር ያከብረዋል። 39በእንግዳም አምላክ እርዳታ በጽኑ አምባ ላይ ያደርጋል፥ ለሚያውቁት ክብር ያበዛላቸዋል፥ በብዙም ላይ ያስገዛቸዋል፥ ምድርንም በዋጋ ይከፍላል።
40በፍጻሜ ዘመንም የደቡብ ንጉሥ ከእርሱ ጋር ይዋጋል፥ የሰሜንም ንጉሥ ከሰረገሎችና ከፈረሰኞች ከብዙም መርከቦች ጋር እንደ ዐውሎ ነፋስ ይመጣበታል፥ ወደ አገሮችም ይገባል፥ ይጐርፍማል፥ ያልፍማል። 41ወደ መልካሚቱም ምድር ይገባል፥ ብዙ አገሮችም ይወድቃሉ፥ ነገር ግን ኤዶምያስና ሞዓብ ከአሞንም ልጆች የበለጡት ከእጁ ይድናሉ። 42እጁን በአገሮች ላይ ይዘረጋል፥ የግብጽም ምድር አታመልጥም። 43በወርቅና በብርም መዝገብ ላይ፥ በከበረችም በግብጽ ዕቃ ሁሉ ላይ ይሠለጥናል፥ የልብያና የኢትዮጵያ ሰዎችም ይከተሉታል። 44ከምሥራቅና ከሰሜን ግን ወሬ ያውከዋል፥ ብዙ ሰዎችንም ይገድል ዘንድና ፈጽሞ ያጠፋ ዘንድ በታላቅ ቍጣ ይወጣል። 45ንጉሣዊ ድንኳኑንም በባሕርና በከበረው በቅዱስ ተራራ መካከል ይተክላል፥ ወደ ፍጻሜው ግን ይመጣል፥ ማንም አይረዳውም።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ