የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

መጽሐፈ መሳፍንት 12

12
1የኤፍሬም ሰዎች ተሰበሰቡ፥ ወደ ጻፎንም ተሻግረው ዮፍታሔን፦ ከአሞን ልጆች ጋር ለመዋጋት ስታልፍ ከአንተ ጋር እንድንሄድ ስለ ምን አልጠራኸንም? ቤትህን በአንተ ላይ በእሳት እናቃጥለዋለን አሉት። 2ዮፍታሔም፦ ከአሞን ልጆች ጋር ለእኔና ለሕዝቤ ጽኑ ጠብ ነበረን፥ በጠራኋችሁም ጊዜ ከእጃቸው አላዳናችሁኝም። 3እንዳላዳናችሁኝም ባየሁ ጊዜ ነፍሴን በእጄ አድርጌ በአሞን ልጆች ላይ አለፍሁ፥ እግዚአብሔርም በእጄ አሳልፎ ሰጣቸው፥ ለምንስ ዛሬ ልትወጉኝ ወደ እኔ መጣችሁ? አላቸው። 4ዮፍታሔም የገለዓድን ሰዎች ሁሉ ሰበሰበ፥ ከኤፍሬምም ጋር ተዋጋ፥ ኤፍሬምም፦ ገለዓዳውያን ሆይ፥ እናንተ በኤፍሬምና በምናሴ መካከል የተቀመጣችሁት ከኤፍሬም ሸሽታችሁ ነው ስላሉ የገለዓድ ሰዎች ኤፍሬምን መቱ። 5ገለዓዳውያንም ኤፍሬም የሚያልፍበትን የዮርዳኖስን መሻገርያ ያዙባቸው፥ የሸሸም የኤፍሬም ሰው፦ ልለፍ ባለ ጊዜ፥ የገለዓድ ሰዎች፦ አንተ ኤፍሬማዊ ነህን? አሉት፥ እርሱም፦ አይደለሁም ቢል፥ 6እነርሱ፦ አሁን ሺቦሌት በል አሉት፥ እርሱም አጥርቶ መናገር አልቻለምና፦ ሲቦሌት አለ፥ ይዘውም በዮርዳኖስ መሻገርያ አረዱት፥ በዚያም ጊዜ ከኤፍሬም አርባ ሁለት ሺህ ሰዎች ወደቁ።
7ዮፍታሔም በእስራኤል ላይ ስድስት ዓመት ፈረደ። ገለዓዳዊውም ዮፍታሔ ሞተ፥ ከገለዓድም ከተሞች በአንዲቱ ተቀበረ።
8ከእርሱም በኋላ የቤተ ልሔሙ ኢብጻን በእስራኤል ላይ ፈራጅ ሆነ። 9ሠላሳም ወንዶች ልጆችና ሠላሳ ሴቶች ልጆች ነበሩት፥ ሠላሳ ሴቶች ልጆቹንም ወደ ውጭ አገር ዳረ፥ ለወንዶች ልጆቹም ከውጭ አገር ሴቶች ልጆችን አመጣ። በእስራኤልም ላይ ሰባት ዓመት ፈረደ። 10ኢብጻንም ሞተ፥ በቤተ ልሔምም ተቀበረ።
11ከእርሱም በኋላ ዛብሎናዊው ኤሎም በእስራኤል ላይ ፈራጅ ሆነ፥ እርሱም በእስራኤል ላይ አሥር ዓመት ፈረደ። 12ዛብሎናዊውም ኤሎም ሞተ፥ በዛብሎንም ምድር ባለችው በኤሎም ተቀበረ።
13ከእርሱም በኋላ የጲርዓቶናዊው የሂሌል ልጅ ዓብዶን በእስራኤል ላይ ፈራጅ ሆነ። 14አርባም ልጆች ሠላሳም የልጅ ልጆች ነበሩት፥ በሰባም አህያ ግልገሎች ላይ ይቀመጡ ነበር። በእስራኤልም ላይ ስምንት ዓመት ፈረደ። 15የጲርዓቶናዊውም የሂሌል ልጅ ዓብዶን ሞተ፥ በተራራማውም በአማሌቃውያን ምድር በኤፍሬም ባለችው በጲርዓቶን ተቀበረ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ