ዘፀአት 16:3-4
ዘፀአት 16:3-4 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
“ምነው በግብጽ ሳለን እግዚአብሔር በገደለን ኖሮ፥ በዚያ ሌላው ቢቀር ሥጋም ሆነ ሌላ ምግብ የፈለግነውን ያኽል መመገብ እንችል ነበረ፤ እናንተ ግን ሁላችንም በራብ እንድናልቅ ወደዚህ በረሓ አወጣችሁን።” እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ አለው፦ “እነሆ፥ እኔ ለሁላችሁም የሚበቃ ምግብ ከሰማይ ላዘንብላችሁ ነው፤ ሕዝቡ በየዕለቱ ወጥተው ለዚያው ቀን የሚበቃቸውን ምግብ ይሰብስቡ፤ በዚህ ዐይነት እኔ የምሰጣቸውን መመሪያ ይጠብቁ እንደ ሆነ እፈትናቸዋለሁ።
ዘፀአት 16:3-4 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
የእስራኤልም ልጆች አሉአቸው፥ “በሥጋው ምንቸት አጠገብ ተቀምጠን እስክንጠግብ ድረስ እንጀራና ሥጋ በምንበላበት ጊዜ በግብፅ ምድር በእግዚአብሔር እጅ ምነው በሞትን! ይህን ጉባኤ ሁሉ በራብ ልትገድሉ እኛን ወደዚች ምድረ በዳ አምጥታችኋልና።” እግዚአብሔርም ሙሴን፥ “በሕጌ ይሄዱ ወይም አይሄዱ እንደ ሆነ እኔ እንድፈትናቸው፥ እነሆ፥ ከሰማይ እንጀራን አዘንብላችኋለሁ፤ ሕዝቡም ወጥተው ለዕለት ለዕለት የሚበቃቸውን ይሰብስቡ።
ዘፀአት 16:3-4 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
የእስራኤልም ልጆች፦ ይህን ጉባኤ ሁሉ በራብ ልትገድሉ እኛን ወደዚች ምድረ በዳ አውጥታችኋል፤ በሥጋው ምንቸት አጠገብ ተቀምጠን እንጀራ ስንበላ ስንጠግብ ሳለን በግብፅ ምድር በእግዚአብሔር እጅ ምነው በሞትን! አሉአቸው። እግዚአብሔርም ሙሴን፦ በሕጌ ይሄዱ ወይም አይሄዱ እንደሆነ እኔ እንድፈትናቸው፥ እነሆ ከሰማይ እንጀራን አዘንብላችኋለሁ፤ ሕዝቡም ወጥተው ለዕለት ለዕለት የሚበቃቸውን ይልቀሙ።
ዘፀአት 16:3-4 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
የእስራኤልም ልጆች እንዲህ አሉአቸው፦ “በሥጋው ምንቸት አጠገብ ተቀምጠን ሳለን፥ ምግብ ተትረፍርፎ ስንበላ ሳለን፥ በግብጽ ምድር ሳለን በጌታ እጅ ምነው በሞትን! ይህን ጉባኤ ሁሉ በራብ ልትገድሉ ወደዚህ ምድረ በዳ አወጣችሁን።” ጌታም ሙሴን እንዲህ አለው፦ “እነሆ ከሰማይ እንጀራን ላዘንብላችሁ ነው፤ ሕዝቡም ወጥተው ለቀኑ የሚበቃቸውን በቀኑ ይልቀሙ በሕጌ ይሄዱ ወይም አይሄዱ እንደሆነ እፈትናቸዋለሁ።