ዘፍጥረት 45:26-28
ዘፍጥረት 45:26-28 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
እንዲህም ብለው ነገሩት፥ “ልጅህ ዮሴፍ በሕይወቱ ነው፤ እርሱም በግብፅ ምድር ሁሉ ላይ ገዥ ሆኖአል።” ያዕቆብም ልቡ ደነገጠ፤ አላመናቸውምም፤ እነርሱም ዮሴፍ ያላቸውን፥ የተናገራቸውንም ነገር ሁሉ ነገሩት፤ ይወስዱት ዘንድ ዮሴፍ የላካቸውን ሰረገሎች በአየ ጊዜ የአባታቸው የያዕቆብ ልቡ፥ መንፈሱም ታደሰ። እስራኤልም፥ “ልጄ ዮሴፍ ገና በሕይወት ከሆነ ይህ ለእኔ ታላቅ ነገር ነው፤ ሳልሞት እንዳየው እሄዳለሁ” አለ።
ዘፍጥረት 45:26-28 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
አባታቸውንም፣ “እነሆ ዮሴፍ በሕይወት አለ፤ እንዲያውም በግብጽ ምድር ሁሉ ገዥ ሆኗል” ብለው ነገሩት። ያዕቆብም በድንጋጤ ክው አለ፤ ሊያምናቸውም አልቻለም። ነገር ግን ዮሴፍ የነገራቸውን ሁሉ ሲያጫውቱትና እርሱንም ወደ ግብጽ ለማጓጓዝ ዮሴፍ የላከለትን ሠረገላዎች ሲያይ የአባታቸው የያዕቆብ መንፈስ ታደሰ። ከዚያም እስራኤል፤ “ልጄ ዮሴፍ በሕይወት አለ፤ ከመሞቴ በፊት ሄጄ ልየው” አለ።
ዘፍጥረት 45:26-28 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
እንዲህም ብለው ነገሩት፦ ዮሴፍ ገና በሕይወት ነው እርሱም በግብፅ ምድር ሁሉ ላይ ገዥ ሆኖአል። ያዕቆብም ልቡ ደነገጠ አላመናቸውም ነበርና። እነርሱም ዮሴፍ የነገራቸውን ነገር ሁሉ ነገሩት እርሱን ያነሡት ዘንድ ዮሴፍ የሰደዳቸውን ሰረገሎች ባያ ጊዜ የአብዝታችው የያዕቆብ የነፍሱ ሕይወት ታደስች። እስራኤልም፦ ልጄ ዮሴፍ ገና በሕይወት ከሆነ ይበቃኛል ሳልሞት እንዳየው እሄዳለሁ አለ።
ዘፍጥረት 45:26-28 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
እዚያም እንደ ደረሱ አባታቸውን “ዮሴፍ በሕይወት አለ፤ እንዲያውም በመላው ግብጽ ላይ አስተዳዳሪ ሆኖአል” አሉት። ያዕቆብ ግን እጅግ ደነገጠ፤ ሊያምናቸውም አልቻለም። ነገር ግን ዮሴፍ ያላቸውን ሁሉ በነገሩት ጊዜና እርሱን ወደ ግብጽ የሚወስዱበትን ዮሴፍ የላከለትን ሠረገላ ባየ ጊዜ ሕይወቱ በደስታ ታደሰ፤ ከዚህ በኋላ ያዕቆብ “ልጄ ዮሴፍ በሕይወት መኖሩን ካረጋገጥሁ ይበቃኛል፤ ከመሞቴ በፊት ሄጄ አየዋለሁ” አለ።