ዕብራውያን 11:24-27
ዕብራውያን 11:24-27 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ሙሴ ካደገ በኋላ የፈርዖን የልጅ ልጅ እንዳይባል በእምነት እምቢ አለ፤ ከግብፅም ብዙ ገንዘብ ይልቅ ስለ ክርስቶስ መነቀፍ እጅግ የሚበልጥ ባለ ጠግነት እንዲሆን አስቦአልና ለጊዜው በኃጢአት ከሚገኝ ደስታ ይልቅ ከእግዚአብሔር ሕዝብ ጋር መከራ መቀበልን መረጠ፤ ብድራቱን ትኵር ብሎ ተመልክቶአልና። የንጉሡን ቍጣ ሳይፈራ የግብፅን አገር የተወ በእምነት ነበር፤ የማይታየውን እንደሚያየው አድርጎ ጸንቶአልና።
ዕብራውያን 11:24-27 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ሙሴም በአደገ ጊዜ የፈርዖን የልጅ ልጅ እንዳይባል በእምነት እንቢ አለ፤ ለጊዜው በኀጢአት ከሚገኝ ደስታ ይልቅ ከእግዚአብሔር ሕዝብ ጋር መከራ መቀበልን መረጠ። የክርስቶስ የመስቀሉ ተግዳሮት ከግብፅ ሀብት ሁሉ ይልቅ እጅግ የሚበልጥ ባለጠግነት እንደሚሆን ዐውቆአልና፥ ዋጋውንም ተመልክቶአልና። የንጉሡንም ቍጣ ሳይፈራ፥ የግብፅን ሀገር በእምነት ተወ፤ ከሚያየው ይልቅ የማይታየውን ሊፈራ ወዶአልና።
ዕብራውያን 11:24-27 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ሙሴም ካደገ በኋላ “የፈርዖን የልጅ ልጅ” ተብሎ መጠራትን ያልፈቀደው በእምነት ነው፤ ስለዚህም እርሱ በኃጢአት ከሚገኘው ጊዜያዊ ደስታ ይልቅ ከእግዚአብሔር ሕዝብ ጋር መከራ መቀበልን መረጠ። ወደፊትም የሚቀበለውን ዋጋ ስለ ተመለከተ ከግብጽ ሀብት ይልቅ ስለ መሲሑ መዋረድ የበለጠ መሆኑን አሰበ። የንጉሡንም ቊጣ ሳይፈራ ከግብጽ የወጣው በእምነት ነው፤ በዐይን የማይታየውንም አምላክ እንዳየው ያኽል ሆኖ በዓላማው ጸና።
ዕብራውያን 11:24-27 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ሙሴ ካደገ በኋላ የፈርዖን የልጅ ልጅ ተብሎ ላለመጠራት በእምነት እምቢ አለ፤ በኃጢአት ከሚገኝ ጊዜያዊ ደስታ ይልቅ፥ ከእግዚአብሔር ሕዝብ ጋር መከራን መቀበል መረጠ። ወደ ፊት የሚቀበለውን ብድራት ከሩቅ ተመልክቶአልና፥ ከግብጽ ሀብት ይልቅ ስለ ክርስቶስ መነቀፍ እጅግ የሚበልጥ ሀብት መሆኑን ተገነዘበ። የማይታየውን እንደሚያየው አድርጎ ጸንቶአልና፥ የንጉሡን ቍጣ ሳይፈራ የግብጽን አገር ትቶ የሄደው በእምነት ነበር።