በክርስቶስ ያለን ማንነትናሙና
ሥፍራችንን አንልቀቅ
ይህ ክፍል ቀድሞ በአብርሃም ዘመን ተከስቶ እንደነበረው ዓይነት ረሃብ በልጁ በይስሐቅ መከሰቱን የሚያወሳ ነው፡፡ ነገር ግን ፀሐፊው ከዚህ ታሪክ የሚያስገነዝበን አንዳንድ ክስተቶች በዘመን የሚደገሙ እንደሆነና ከተከናወነው ታሪክ ግን ስህተትን ሳንደግም መማር ያለብን ነገር እንድናስተውል ነው።
በዘፍ. 12÷10-20 ላይ በአብርሃም ዘመን ረሃብ በመከሰቱ አብርሃም ስፍራውን ለቆ ወደ ግብፅ በመውረዱ ምክንያት ሁለት ነገሮች እንደተከሰቱ እናስተውላለን፡፡ አንደኛ በመዋሸቱ የሞራል ውድቀት ደረሰበት ወይም ከልኩ ወረደ። ሁለተኛ ለሌላው በረከት የተጠራው አብርሃም በፈርዖንና በቤቱ ላይ ታላቅ መቅሠፍት እንዲመጣ አደረገ። ስለዚህ እግዚአብሔር ይስሐቅን ምንም እንኳ በአባትህ ዘመን እንደነበረው ታላቅ ረሃብ ቢሆንም ስፍራህን ሳትለቅ ብትቀመጥ እኔ ካንተ ጋር እሆናለሁ። እባርክሃለሁ። እነዚህን ምድሮች ለአንተና ለዘርህ እሰጣለሁ። ለአባትህ የገባሁትን ኪዳን እፈፅማለሁ አለው።
ዛሬም ውድ የቤዛ ቤተሰቦች ስለ ረሃብ ለመናገር ፈልጌ ሳይሆን አብርሃም በረሃቡ ምክንያት ስፍራውን በመልቀቅ ወደ ግብፅ ወርዶ የደረሰበት ነገር በይስሐቅ እንዳይደርስበት በማሰብ እግዚአብሔር ተገለጠለትና “ወደ ግብፅ አትውረድ እኔ በምልህ ምድር ተቀመጥ” - "ሥፍራህን አትልቀቅ" ብሎ እንዳስጠነቀቀው ሁሉ ይህ ታሪክ ዛሬም ለእኛ ትልቅ ትምህርት ነው።
መቼም የእኛ ስፍራ የቦታ፣የሃገር ወይም የምድር ጉዳይ ሳይሆን ጳውሎስ በኤፌ. 1÷ 3 እና በፊሊ. 3÷20 ላይ እንደ ተናገረው፣ የእኛ ስፍራ ወይም ሀገር በሰማይ ነው። እግዚአብሔር ይስሐቅን አትውረድ እንዳለው ሁሉ እኛም ከተቀመጥንበት የእግዚአብሔር ክልልና መገኘት በሌላ ቋንቋ /ከአገራችን/ ወጥተን አሁን በተፈጠረው ሁኔታ ልባችን ወደ ፍርሃት፣ ጭንቀት፣ ጥርጥርና አለማመን እንዳንወርድ እላለሁ። ነገር ግን በስፍራችን ፀንተን ስንቀመጥ እርሱ የይስሐቅ አምላክ ከእኛ ጋር ስለሆነ በእኛ ምድራችንን ይፈውሳል።
የሕይወት ተዛምዶ
ምንም እንኳ ታሪክ ራሱን ቢደግምም ከታሪክ በሚፈጠር ስህተት ግን መማር አለብን። ይስሐቅ ከአብርሃም እንደተማረ ሁሉ ስለዚህ እግዚአብሔር እኛን በክርስቶስ በኩል ካስቀመጠን ሥፍራ ባለ መውረድ ውስጣችን የተጠበቀና የትኩረት አቅጣጫችንን ሳንስት በእርሱ ላይ ካደረግን ለሌሎች የበረከትና የፈውስ ምክንያት እንሆናለን።
ፀሎት
እግዚአብሔር ሆይ በተፈጠረው የበሽታ ሁኔታ ከሥፍራችን ወርደን ከመገኘቱ እንዳንጎድልና እንደ ሌሎች ተስፋ እንደሌላቸው እንዳይደለን እንድናስብ ዛሬ ማስተዋል ይብዛልን።
ቅዱሳት መጻሕፍት
ስለዚህ እቅድ
በእውነት በክርስቶስ ማን እንደሆንን ራሳችንን ለማስታወስ የ5 ቀን ጉዞ። ክርስቶስ ምን እንዳደረገልንና ይህ ከእርሱ ጋር በየቀኑ የምንጓዝበት መንገድ ላይ ምን ሚና እንደሚጫወት እናስታውስ።
More
ቤዛ ዓለም አቀፍ ሚኒስትሮችን ይህንን እቅድ ስላቀረቡልን እናመሰግናለን ፡፡ ለበለጠ መረጃ ይጎብኙ http://bezainternational.org