መጽሐፈ ኢያሱ ወልደ ነዌ 10
10
አሞራውያን በእስራኤል እንደ ተሸነፉ
1እንዲህም ሆነ፤ የኢየሩሳሌም ንጉሥ አዶኒቤዜቅ#ዕብ. “አዶኒጼዴቅ” ይላል። ኢያሱ ጋይን እንደ ያዘ፥ ፈጽሞም እንዳጠፋት፥ በኢያሪኮና በንጉሥዋም ያደረገውን እንዲሁ በጋይና በንጉሥዋም እንዳደረገ፥ የገባዖንም ሰዎች ከኢያሱና ከእስራኤል ጋር ሰላም እንዳደረጉ፥ በመካከላቸውም እንደ ሆኑ በሰማ ጊዜ፥ 2ገባዖን ከመንግሥታት ከተሞች እንደ አንዲቱ ታላቅ ከተማ ስለሆነች፥ ከጋይም ስለ በለጠች፥#“ከጋይም ስለ በለጠች” የሚለው በግሪክ ሰባ. ሊ. የለም። ሰዎችዋም ሁሉ ኀያላን ስለ ነበሩ እጅግ ፈራ። 3ስለዚህም የኢየሩሳሌም ንጉሥ አዶኒቤዜቅ ወደ ኬብሮን ንጉሥ ወደ ኤላም፥ ወደ የርሙት ንጉሥም ወደ ፊዶን፥ ወደ ለኪስ ንጉሥም ወደ ኤፍታ፥ ወደ አዶላም ንጉሥም ወደ ዳቤር ልኮ፥ 4“ወደ እኔ ኑ፤ ከኢያሱና ከእስራኤልም ልጆች ጋር ሰላም አድርገዋልና ገባዖንን ለመውጋት አግዙኝ” አለ። 5አምስቱም የኢያቡሴዎን#ዕብ. “አሞራውያን” ይላል። ነገሥት፥ የኢየሩሳሌም ንጉሥ የኬብሮን ንጉሥ፥ የየርሙት ንጉሥ፥ የላኪስ ንጉሥ፥ የአዶላም ንጉሥ፥ ከሠራዊቶቻቸው ሁሉ ጋር ተሰብስበው ወጡ፤ ከገባዖንም ጋር ሊጋጠሙ ከበቡአት።
6የገባዖንም ሰዎች ኢያሱ ወደ ሰፈረበት ወደ ጌልገላ ልከው፥ “ባሪያዎችህን ለመርዳት እጅህን አትመልስ፤ በተራራማው ሀገር የሚኖሩ የአሞሬዎናውያን ነገሥት ሁሉ ተሰብስበውብናልና ፈጥነህ ወደ እኛ ውጣ፤ አድነንም፤ ርዳንም፤” አሉት። 7ኢያሱም ከእርሱም ጋር የነበሩ ተዋጊዎች ሁሉ፥ ጽኑዓን ኀያላኑም ሁሉ ከጌልጌላ ወጡ። 8እግዚአብሔርም ኢያሱን፥ “በእጅህ አሳልፌ ሰጥቼአቸዋለሁና አትፍራቸው፤ ከእነርሱም አንድ ሰው በፊትህ የሚተርፍ የለም፤” አለው። 9ኢያሱም ከጌልገላ ሌሊቱን ሁሉ ገሥግሦ በድንገት ደረሰባቸው። 10እግዚአብሔርም በእስራኤል ፊት አስደነገጣቸው፤ በገባዖንም ታላቅ መምታት መታቸው። 11ከእስራኤልም ልጆች ፊት እየሸሹ በቤትሖሮን ቍልቍለት ሲወርዱ፥ ወደ ዓዜቃና ወደ መቄዳ እስኪደርሱ ድረስ እግዚአብሔር ከሰማይ ታላላቅ የበረዶ ድንጋይ አወረደባቸውና ሞቱ፤ የእስራኤል ልጆች በሰይፍ ከገደሉአቸው ይልቅ በበረዶ ድንጋይ የሞቱት በለጡ።
12ያን ጊዜም እግዚአብሔር በእስራኤል ልጆች እጅ አሞሬዎናውያንን አሳልፎ ሰጠ፤ እርሱ በገባዖን እነርሱን ባጠፋበት፥ እነርሱም ከእስራኤል ልጆች ፊት በጠፉበት ቀን ኢያሱ ከእግዚአብሔር ጋር ተነጋገረ፤ እንዲህም አለ፥ “በገባዖን ላይ ፀሐይ ትቁም፤ በኢሎንም ሸለቆ ጨረቃ፤” 13እግዚአብሔርም ጠላቶቻቸውን እስኪያጠፋ ድረስ ፀሐይና ጨረቃ በየቦታቸው ቆሙ። ይህም እነሆ በዚህ መጽሐፍ በጊዜው ተጻፈ።#ዕብ. “ይህስ በያሻር መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን” ይላል። ፀሐይም በሰማይ መካከል ቆመች፤ አንድ ቀንም ሙሉ ያህል አልጠለቀችም። 14እግዚአብሔር ለእስራኤል ይዋጋ ነበርና እግዚአብሔር የሰውን ቃል የሰማበት እንደዚያ ያለ ቀን ከዚያም በፊት ከዚያም በኋላ አልነበረም።
15ኢያሱም፥ ከእርሱም ጋር እስራኤል ሁሉ ወደ ሰፈራቸው ወደ ጌልገላ ተመለሱ።
ኢያሱ አምስቱን አሞራውያን ነገሥት እንደ ገደለ
16እነዚህም አምስት ነገሥት ሸሽተው በመቄዳ ዋሻ ተሸሸጉ። 17ለኢያሱም “አምስቱ ነገሥት በመቄዳ ዋሻ ተሸሽገው ተገኙ፤” ብለው ነገሩት። 18ኢያሱም እንዲህ አለ፥ “ወደ ዋሻው አፍ ታላላቅ ድንጋይ አንከባልላችሁ፥ ይጠብቋቸው ዘንድ ሰዎችን በዚያ አኑሩ፤ 19እናንተ ግን አትዘግዩ፤ ጠላቶቻችሁንም እስከ መጨረሻው ተከታትላችሁ ያዙአቸው፤ አምላካችሁም እግዚአብሔር በእጃችሁ አሳልፎ ሰጥቶአቸዋልና ወደ ከተሞቻቸው እንዳይገቡ ከልክሉአቸው፤” አለ። 20እስኪጠፉም ድረስ ኢያሱና የእስራኤል ልጆች በታላቅ መምታት መምታታቸውን በፈጸሙ ጊዜ፥ ከእነርሱም ያመለጡት ወደ ተመሸገ ከተማ በገቡ ጊዜ፥ 21ሕዝቡ ሁሉ ኢያሱ ወደ ሰፈረበት ወደ መቄዳ በደኅና ተመለሱ፤ በእስራኤል ልጆች ላይ ምላሱን ማንቀሳቀስ የደፈረ ማንም ሰው የለም።
22ኢያሱም፥ “የዋሻውን አፍ ክፈቱ፤ እነዚያንም አምስት ነገሥት ከዋሻው ወደ እኔ አውጡአቸው” አለ። 23እንዲህም አደረጉ፤ አምስቱንም ነገሥት፥ የኢየሩሳሌምን ንጉሥ፥ የኬብሮንንም ንጉሥ፥ የየርሙትንም ንጉሥ፥ የላኪስንም ንጉሥ፥ የአዶላምንም ንጉሥ ከዋሻው ወደ እርሱ አወጡአቸው። 24እነዚያንም ነገሥት ወደ ኢያሱ ባመጡአቸው ጊዜ ኢያሱ የእስራኤልን ሰዎች ሁሉ ጠራ፤ ከእርሱም ጋር የሄዱትን የተዋጊዎችን አለቆች “ቅረቡ፤ በእነዚህም ነገሥት አንገት ላይ እግራችሁን አኑሩ” አላቸው። ቀረቡም በአንገታቸውም ላይ እግራቸውን አኖሩ። 25ኢያሱም፥ “በምትወጉአቸው በጠላቶቻችሁ ሁሉ ላይ እንዲሁ እግዚአብሔር ያደርጋልና አትፍሩ፤ አትደንግጡ፤ ጽኑ፤ አይዞአችሁ” አላቸው። 26ከዚህም በኋላ መትተው ገደሉአቸው፤ በአምስቱም ዛፎች ላይ ሰቀሉአቸው፤ እስከ ማታም ደረስ በዛፎቹ ላይ ተሰቅለው ቈዩ። 27ፀሐይም ልትገባ በቀረበች ጊዜ ኢያሱ አዘዘ፤ ከዛፎችም አወረዱአቸው፤ ተሸሽገውም በነበሩበት ዋሻ ጣሉአቸው፤ እስከ ዛሬም ድረስ በዋሻው አፍ ታላላቅ ድንጋይ ተደርጎአል።
ኢያሱ ሌሎች ከተሞችን እንደ ያዘ
28በዚያም ቀን መቄዳን ያዟት፤ እርስዋንና ንጉሥዋንም በሰይፍ ስለት ገደሉ፤ በእርስዋም ያሉትን ነፍሳት ሁሉ ፈጽመው አጠፉአቸው፤ ከእነርሱም አንዱን ስንኳ አላስቀሩም፤ የዳነም፥ ያመለጠም የለም፤ በኢያሪኮም ንጉሥ እንዳደረጉ በመቄዳ ንጉሥ አደረጉ።
29ኢያሱም፥ ከእርሱም ጋር እስራኤል ሁሉ ከመቄዳ ወደ ልብና አለፉ፤ ልብናንም ወጉ። 30እግዚአብሔርም እርስዋንና ንጉሥዋን በእስራኤል እጅ አሳልፎ ሰጠ፤ እርስዋንም በእርስዋም ያሉትን ነፍሳት ሁሉ በሰይፍ ስለት መታ፤ በእርስዋም አንዱን ስንኳ አላስቀረም፤ በኢያሪኮም ንጉሥ እንዳደረገው በልብና ንጉሥ አደረገ።
31ኢያሱም ከእርሱም ጋር እስራኤል ሁሉ ከልብና ወደ ላኪስ አለፉ፤ በዙሪያዋም ሰፈሩ፤ ከበቡአትም። 32እግዚአብሔርም ላኪስን በእስራኤል እጅ አሳልፎ ሰጣት፤ በሁለተኛውም ቀን ያዙአት፤ በልብናም እንዳደረጉት ሁሉ፥ እርስዋን፥ በእርስዋም ያሉትን ነፍሳት ሁሉ በሰይፍ ስለት መቱአቸው።
33በዚያ ጊዜም የጋዜር ንጉሥ ኤላም ላኪስን ለመርዳት ወጣ፤ ኢያሱም አንድ ስንኳ ሳይቀር በሰይፍ ስለት እርሱንና ሕዝቡን መታ፤ የዳነም፥ ያመለጠም የለም።
34ኢያሱም ከእርሱም ጋር እስራኤል ሁሉ ከላኪስ ወደ አዶላም አለፉ፤ ከበቡአትም፤ ወጉአትም፤ 35እግዚአብሔርም በእስርኤል እጅ አሳልፎ ሰጣት፤ በዚያም ቀን ያዙአት፤ በሰይፍም ስለት መቱአት፤ በላኪስም እንዳደረገው ሁሉ፥ በእርስዋ ያሉትን ነፍሳት ሁሉ ፈጽሞ አጠፋ።
36ኢያሱም ከእርሱም ጋር እስራኤል ሁሉ ከአዶላም ወደ ኬብሮን ወጡ፤ ወጉአትም፤ ያዙአትም፤ 37እርስዋንም፥ ንጉሥዋንም፥ ከተሞችዋንም ሁሉ፥ በእርስዋም ያሉትን ነፍሳት ሁሉ በሰይፍ ስለት መቱ፤ በአዶላም እንዳደረገው ሁሉ ማንንም አላስቀረም ፤ እርስዋንም፥ በእርስዋም ያሉትን ነፍሳት ሁሉ ፈጽሞ አጠፋ።
38ኢያሱም፥ ከእርሱም ጋር እስራኤል ሁሉ ወደ ዳቤር ተመለሱ፤ ወጉአትም፤ 39እርስዋንም፥ ንጉሥዋንም፥ ከተሞችዋንም ያዙ፤ በሰይፍም ስለት መቱአቸው፤ በእነርሱም ውስጥ ያሉትን ነፍሳት ሁሉ ፈጽመው አጠፉ፤ ማንንም አላስቀረም፤ በኬብሮንና በንጉሥዋም እንዳደረገው እንዲሁ በዳቤርና በንጉሥዋ አደረገ።
40እንዲሁም ኢያሱ ምድሪቱን ሁሉ፥ ተራራማውን ሀገር፥ ደቡቡንም፥ ቆላውንም፥ ቍልቍለቱንም፥ ንጉሦቻቸውንም ሁሉ መታ፤ ማንንም አላስቀረም፤ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዳዘዘውም ነፍስ ያለበትን ሁሉ ፈጽሞ አጠፋ። 41ኢያሱም ከቃዴስ በርኔ እስከ ጋዛ ድረስ፥ የጎሶምንም ምድር ሁሉ እስከ ገባዖን ድረስ መታ። 42የእስራኤልም አምላክ እግዚአብሔር ለእስራኤል ስለ ተዋጋላቸው ኢያሱ እነዚህን ነገሥታት ሁሉ ምድራቸውንም በአንድ ጊዜ ያዘ። 43ኢያሱም፥ ከእርሱም ጋር እስራኤል ሁሉ ወደ ሰፈሩ ወደ ጌልገላ ተመለሱ።#ምዕ. 10 ቍጥር 43 በግሪክ ሰባ. ሊ. የለም።
Currently Selected:
መጽሐፈ ኢያሱ ወልደ ነዌ 10: አማ2000
Highlight
Share
Copy
Want to have your highlights saved across all your devices? Sign up or sign in