ዘፍጥረት 40
40
የመጠጥ አሳላፊውና የእንጀራ ቤቱ
1ከዚህም በኋላ የግብፅ ንጉሥ የመጠጥ አሳላፊና እንጀራ ቤቱ ጌታቸውን የግብፅን ንጉሥ በደሉት። 2ፈርዖንም በመጠጥ አሳላፊዎቹ አለቃና በእንጀራ ቤቱ አዛዥ፣ በሁለቱም ሹማምቱ ላይ ክፉኛ ተቈጣ፤ 3በዘበኞቹ አለቃ ቤት ወዳለው ዮሴፍ ወደ ተጋዘበትም እስር ቤት አስገባቸው።
4የዘበኞቹም አለቃ እስረኞቹን ለዮሴፍ አስረከባቸው፤ ዮሴፍም በሚያስፈልጋቸው ይረዳቸው ነበር።
እስር ቤት ገብተው ጥቂት እንደ ቈዩም፣ 5ታስረው የነበሩት የግብፅ የንጉሥ የመጠጥ አሳላፊዎች አለቃና የእንጀራ ቤቱ አዛዥ፣ በአንድ ሌሊት የየራሳቸውን ሕልም አዩ፤ የሁለቱም ሕልም ለየራሱ የተለየ ፍቺ ነበረው።
6በማግስቱም ጧት ዮሴፍ ወደ እነርሱ ሲገባ ተክዘው አገኛቸው። 7ስለዚህም፣ “ምነው ዛሬስ ፊታችሁ ላይ ሐዘን ይነበባል?” በማለት አብረውት በጌታው ግቢ የታሰሩትን የፈርዖን ሹማምት ጠየቃቸው።
8እነርሱም “ሁለታችንም ሕልም አየን፤ ነገር ግን የሚተረጕምልን ሰው አጣን” ሲሉ መለሱለት።
ዮሴፍም፣ “ሁልጊዜስ ቢሆን የሕልም ትርጓሜ ከእግዚአብሔር (ኤሎሂም) የሚገኝ አይደለምን? እስቲ ያያችሁትን ሕልም ንገሩኝ” አላቸው።
9ስለዚህ የመጠጥ አሳላፊዎቹ አለቃ እንዲህ ሲል ሕልሙን ለዮሴፍ ነገረው፤ “ከፊት ለፊቴ አንዲት የወይን ተክል አየሁ፤ 10ተክሏም ሦስት ሐረጎች ነበሯት፤ ወዲያው አቈጥቍጣ አበበች፤ ዘለላዎቿም ተንዠርግገው በሰሉ። 11የፈርዖንንም ጽዋ ይዤ ነበረ፤ የወይኑን ፍሬ ለቅሜ በጽዋው ውስጥ ጨምቄ ጽዋውን በእጁ ሰጠሁት።”
12ዮሴፍም እንዲህ አለው፤ “እንግዲህ የሕልሙ ትርጓሜ ይህ ነው፤ ሦስቱ ሐረግ ሦስት ቀን ነው፤ 13በሦስት ቀን ውስጥ ፈርዖን ከእስር ቤት ያወጣሃል፣ ወደ ቀድሞ ሹመትህም ይመልስሃል፤ በፊት የመጠጥ አሳላፊ በነበርህበት ጊዜ ታደርግ እንደ ነበረው ሁሉ የፈርዖንን ጽዋ በእጁ ትሰጣለህ። 14እንግዲህ፣ በጎ ነገር በገጠመህ ጊዜ፣ እኔን አስበህ ቸርነት አድርግልኝ፤ ስለ እኔም ለፈርዖን ንገርልኝ፤ ከዚህም እስር ቤት አስወጣኝ፤ 15ከዕብራውያን ምድር ወደዚህ የመጣሁት በዐፈና ነው፤ አሁንም ቢሆን እዚህ እስር ቤት የተጣልሁት አንዳች ጥፋት ኖሮብኝ አይደለም።”
16የእንጀራ ቤት አዛዡም፣ ለመጠጥ አሳላፊዎቹ አለቃ ሕልም፣ የተሰጠው ፍቺ ደስ የሚያሰኝ መሆኑን ሲሰማ፣ የራሱን ሕልም ለዮሴፍ እንዲህ ሲል ነገረው፤ “እኔም ደግሞ ሕልም አይቻለሁ፤ ሦስት መሶቦች#40፥16 ወይም ሦስት የሸንበቆ ቅርጫቶች በራሴ ላይ ተሸክሜ ነበር፤ 17በላይኛው መሶብ ውስጥ ለፈርዖን የተዘጋጀ የተለያየ ምግብ ነበረበት፤ ወፎችም ራሴ ላይ ካለው መሶብ ይበሉ ነበር።”
18ዮሴፍም እንዲህ ሲል መለሰለት፤ “የሕልሙ ፍቺ ይህ ነው፤ ሦስቱ መሶብ ሦስት ቀን ነው፤ 19በሦስት ቀን ውስጥ ፈርዖን ከእስር ቤት ያወጣሃል፤ በዕንጨትም ላይ ይሰቅልሃል፤#40፥19 ወይም በእንጨትም ላይ ይወጋሃል ወፎችም ሥጋህን ይበሉታል።”
20በሦስተኛውም ቀን የፈርዖን የልደት በዓል ነበረ፤ ለሹማምቱም ሁሉ ግብር አበላ። በዚያኑ ዕለትም የመጠጥ አሳላፊዎችን አለቃና የእንጀራ ቤት አዛዡን ሹማምቱ ባሉበት ከእስር ቤት አወጣቸው።
21የመጠጥ አሳላፊዎቹን አለቃ ወደ ቀድሞ ሹመቱ መለሰው፤ እርሱም እንደ ቀድሞው ጽዋውን ለፈርዖን በእጁ ይሰጠው ጀመር። 22የእንጀራ ቤት አዛዡን ግን ልክ ዮሴፍ እንደ ተረጐመላቸው ሰቀለው።#40፥22 ወይም ወጋው
23የሆነው ሆኖ፣ የመጠጥ አሳላፊዎቹ አለቃ ዮሴፍን አላስታወሰውም፤ ረሳው እንጂ።
Kasalukuyang Napili:
ዘፍጥረት 40: NASV
Haylayt
Ibahagi
Kopyahin
Gusto mo bang ma-save ang iyong mga hinaylayt sa lahat ng iyong device? Mag-sign up o mag-sign in
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጅ መብት © 2001 በ Biblica, Inc.
ፈቃድ የተገኘባቸው ናቸው። መብቱ በመላው ዓለም በሕግ የተጠበቀ።
Holy Bible, New Amharic Standard Version™ (Addisu Medebegna Tirgum™)
Copyright © 2001 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.