ዘፍጥረት 41
41
የፈርዖን ሕልም
1ድፍን ሁለት ዓመት ካለፈ በኋላ ፈርዖን ሕልም ዐለመ፤ በሕልሙም፣ በአባይ ወንዝ ዳር ቆሞ ነበር፤ 2እነሆ መልካቸው ያማረ፣ ሥጋቸው የወፈረ ሰባት ላሞች ከወንዙ ወጥተው በወንዙ ዳር የበቀለውን ሣር ይበሉ ጀመር። 3ቀጥሎም መልካቸው የከፋ ዐጥንታቸው የወጣ፣ ሌሎች ሰባት ላሞች ከወንዙ ወጥተው አስቀድመው ከወጡት ላሞች አጠገብ ቆሙ። 4እነዚህ መልካቸው የከፋና ዐጥንታቸው የወጣ ላሞች፣ እነዚያን ያማሩና የወፈሩ ላሞች ሲውጧቸው አየ፤ ከዚያም ፈርዖን ከእንቅልፉ ነቃ።
5ፈርዖንም እንደ ገና እንቅልፍ ወስዶት ሳለ፣ ሌላ ሕልም አየ። በሕልሙም በአንድ የእህል አገዳ ላይ፣ ፍሬያቸው የተንዠረገገና ያማረ ሰባት የእሸት ዛላዎች ሲወጡ አየ። 6ከዚያም የቀጨጩና በምሥራቅ ነፋስ ተመትተው የደረቁ ሰባት የእሸት ዛላዎች ወጡ። 7የቀጨጩት የእሸት ዛላዎች፣ ፍሬያቸው የተንዠረገገውን ሰባቱን ያማሩ ዛላዎች ዋጧቸው። በዚህ ጊዜ ፈርዖን ከእንቅልፉ ነቃ፤ ነገሩ ሕልም ነበር።
8በነጋታውም ፈርዖን መንፈሱ ታወከበት፤ ስለዚህ በግብፅ አገር ያሉትን አስማተኞችና ጥበበኞች በሙሉ አስጠርቶ ሕልሞቹን ነገራቸው፤ ይሁን እንጂ ሕልሞቹን ሊተረጕምለት የቻለ አንድም ሰው አልተገኘም።
9በዚያን ጊዜ የመጠጥ አሳላፊዎች አለቃ ፈርዖንን እንዲህ አለው፤ “የሠራሁት በደል ዛሬ ታወሰኝ። 10በአንድ ወቅት ፈርዖን እኔንና የእንጀራ ቤት አዛዡን ተቈጥቶ በዘበኞቹ አለቃ ግቢ አስሮን ነበር። 11ሁለታችንም በአንዲት ሌሊት የተለያየ ሕልም አየን፤ የእያንዳንዳችንም ሕልም የየራሱ ትርጕም ነበረው። 12በዚያን ጊዜ የዘበኞች አለቃ አገልጋይ የሆነ አንድ ዕብራዊ ወጣት ከእኛ ጋር እስር ቤት ነበር። ሕልማችንን በነገርነው ጊዜ፣ ፍቺውን ነገረን፤ ለእያንዳንዳችንም እንደ ሕልማችን ተረጐመልን፤ 13ነገሩም ልክ እርሱ እንደ ተረጐመልን ሆነ፤ እኔ ወደ ቀድሞ ሹመቴ ተመለስሁ፤ የእንጀራ ቤት አዛዡም ተሰቀለ#41፥13 ወይም ተወጋ።”
14ፈርዖን ዮሴፍን እንዲያመጡት ትእዛዝ ሰጠ፤ ከእስር ቤትም በጥድፊያ ይዘውት መጡ፤ ጠጕሩንም ከተላጨና ልብሱን ከለወጠ በኋላ ፈርዖን ፊት ቀረበ።
15ፈርዖንም ዮሴፍን፣ “ሕልም አይቼ ነበር፤ ሕልሜን ሊተረጕምልኝ የቻለ አንድም ሰው አልተገኘም፤ አንተ ግን ሕልም ሲነገርህ የመተርጐም ችሎታ እንዳለህ ሰማሁ” አለው።
16ዮሴፍም ፈርዖንን፣ “እኔ የመተርጐም ችሎታ የለኝም፤ ነገር ግን እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ለፈርዖን የሚሻውን ትርጕም ይሰጠዋል” አለው።
17ከዚህ በኋላ ፈርዖን ዮሴፍን እንዲህ አለው፤ “በሕልሜ በአባይ ወንዝ ዳር ቆሜ ነበር። 18ሥጋቸው የወፈረና መልካቸው ያማረ ሰባት ላሞች ከወንዙ ወጥተው በወንዙ ዳር የበቀለውን ሣር ሲበሉ አየሁ። 19ከእነርሱም በኋላ፣ ዐቅመ ደካማ፣ መልካቸው እጅግ የከፋና ዐጥንታቸው የወጣ ሌሎች ሰባት ላሞች ወጡ፤ እነዚያን የመሰሉ የሚያስከፋ መልክ ያላቸው ላሞች በግብፅ ምድር ከቶ አይቼ አላውቅም። 20ዐጥንታቸው የወጣና አስከፊ መልክ ያላቸው ላሞች መጀመሪያ የወጡትን፣ ሥጋቸው የወፈረውን ሰባቱን ላሞች ዋጧቸው። 21ከዋጧቸውም በኋላ፣ ያው የበፊቱ መልካቸው ስላልተለወጠ እንደ ዋጧቸው ማንም ሊያውቅ አይችልም ነበር፤ ከዚያም ከእንቅልፌ ነቃሁ።
22“እንደዚሁም፣ በሕልሜ በአንድ የእህል አገዳ ላይ ፍሬያቸው የፋፋና ያማሩ ሰባት እሸት ዛላዎች ወጥተው አየሁ። 23ቀጥሎም በምሥራቅ ነፋስ ተመትተው የቀጨጩና የደረቁ ሌሎች ሰባት ዛላዎች ወጡ። 24የቀጨጩት የእሸት ዛላዎችም ሰባቱን ያማሩ የእሸት ዛላዎች ዋጧቸው፤ ይህንኑም ለአስማተኞች ነገርሁ፤ ነገር ግን ማንም ሊፈታው አልቻለም።”
25ዮሴፍም ለፈርዖን እንዲህ አለው፤ “ሁለቱም የፈርዖን ሕልሞች ተመሳሳይና አንድ ዐይነት ናቸው፤ እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ወደ ፊት የሚያደርገውን ለፈርዖን ገልጦለታል። 26ሰባቱ የሚያማምሩ ላሞች፣ ሰባት ዓመታት ናቸው፣ ሰባቱም የሚያማምሩ የእሸት ዛላዎች ሰባት ዓመታት ናቸው፤ ሕልሙም አንድና ተመሳሳይ ነው። 27ከእነርሱም በኋላ ዐጥንታቸው የወጣ አስከፊ መልክ ያላቸው ሰባት ላሞች፣ ሰባት ዓመታት ናቸው፤ እንደዚሁም ፍሬ አልባ የሆኑትና በምሥራቅ ነፋስ ተመትተው የደረቁት ሰባት የእሸት ዛላዎች ሰባት የራብ ዓመታት ናቸው።
28“አስቀድሜ ለፈርዖን እንደ ተናገርሁት፣ እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ወደ ፊት የሚያደርገውን ነገር ለፈርዖን ገልጦለታል። 29በመላው የግብፅ ምድር እጅግ የተትረፈረፈ ጥጋብ የሚሆንባቸው ሰባት ዓመታት ይመጣሉ። 30ከዚህ በኋላ ግን በተከታታይ ሰባት የራብ ዓመታት ይሆናሉ። የራቡ ዘመን አገሪቱን እጅግ ስለሚጐዳት፣ በግብፅ የነበረው ያለፈው የጥጋብ ዘመን ሁሉ ጨርሶ አይታወስም። 31ከጥጋቡ ዓመታት በኋላ የሚመጣው የራብ ዘመን እጅግ ጽኑ ከመሆኑ የተነሣ፣ ቀደም ሲል የነበረው የጥጋብ ዘመን ፈጽሞ ይረሳል። 32ሕልሙ ለፈርዖን በሁለት መልክ በድጋሚ መታየቱ፣ ነገሩ ከእግዚአብሔር (ኤሎሂም) ዘንድ የተቈረጠ ስለሆነ ነው፤ ይህንም እግዚአብሔር (ኤሎሂም) በቅርብ ጊዜ ይፈጽመዋል።
33“እንግዲህ ፈርዖን ብልኅና አስተዋይ ሰው ፈልጎ፣ በመላው የግብፅ ምድር ላይ አሁኑኑ ይሹም። 34እንደዚሁም በሰባቱ የጥጋብ ዓመታት ከሚገኘው ምርት፣ አንድ አምስተኛው እንዲሰበሰብ የሚያደርጉ ኀላፊዎችን ይሹም። 35እነርሱም በሚመጡት የጥጋብ ዓመታት ከሚገኘው ምርት ሁሉ ይሰብስቡ፤ በፈርዖንም ሥልጣን ሥር ያከማቹ፤ ለምግብ እንዲሆኑም በየከተማው ይጠበቁ። 36ሚከማቸው እህል፣ ወደ ፊት በግብፅ አገር ላይ ለሚመጣው የሰባት ዓመት ራብ መጠባበቂያ ይሁን፤ በዚህም ሁኔታ አገሪቱ በራብ አትጠፋም።”
37ዕቅዱንም ፈርዖንና ሹማምቱ ሁሉ መልካም ሆኖ አገኙት። 38ፈርዖንም፣ “የእግዚአብሔር (ኤሎሂም) መንፈስ#41፥38 ወይም የአማልክት መንፈስ ያለበት እንደዚህ ያለ ሰው ማንን ልናገኝ እንችላለን?” ብሎ ጠየቃቸው።
39ፈርዖን ዮሴፍን እንዲህ አለው፤ “እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ይህን ሁሉ ስለ ገለጠልህ፣ እንደ አንተ ያለ አስተዋይና ብልኅ ሰው የለም። 40አንተ በቤተ መንግሥቴ የበላይ ትሆናለህ፤ ሕዝቤም ሁሉ ለሥልጣንህ ይገዛል፤ እኔ ከአንተ የምበልጠው በዙፋኔ ብቻ ይሆናል።”
ዮሴፍ በግብፅ ተሾመ
41ከዚያም፣ ፈርዖን ዮሴፍን፣ “በመላዪቱ የግብፅ ምድር ላይ ኀላፊ አድርጌሃለሁ” አለው። 42ፈርዖንም ባለ ማኅተሙን ቀለበት ከጣቱ አውልቆ በዮሴፍ ጣት ላይ አደረገው፤ እንዲሁም ከጥሩ የተልባ እግር የተሠራ ልብስ አለበሰው፤ በዐንገቱም የወርቅ ሐብል አጠለቀለት። 43በማዕረግ ከእርሱ ሁለተኛ ሰው አድርጎ፣ በሠረገላ ላይ አስቀመጠው።#41፥43 ወይም በማዕረግ ሁለተኛ በሆነው የእርሱ ሠረገላ ላይ፤ ወይም በሁለተኛ ሠረገላው ላይ ሰዎችም በፊቱ፣ “እጅ ንሡ#41፥43 ወይም ስገዱ” እያሉ ይጮኹ ነበር፤ በዚህ ሁኔታም በግብፅ ምድር ሁሉ ላይ ሾመው።
44ከዚህ በኋላ ፈርዖን ዮሴፍን፣ “እኔ ፈርዖን ነኝ፤ ሆኖም በመላዪቱ ግብፅ ያላንተ ትእዛዝ እጁንም ሆነ እግሩን ልውስ የሚያደርግ አይኖርም” አለው። 45ፈርዖንም ዮሴፍን ጸፍናት ፐዕናህ ብሎ ስም አወጣለት። እንዲሁም የሄልዮቱ#41፥45 በ50 ላይ ያለውንም ጨምሮ ሆልዮፓሊስን ያመለክታል። ከተማ ካህን የጶጥፌራ ልጅ አስናትን አጋባው። ዮሴፍም በመላዪቱ የግብፅ ምድር ተዘዋወረ።
46ዮሴፍ የግብፅ ንጉሥ ፈርዖንን ማገልገል ሲጀምር፣ ዕድሜው ሠላሳ ዓመት ነበር። ዮሴፍም ከፈርዖን ፊት ወጥቶ የግብፅን ምድር በሙሉ ዞረ።
47በሰባቱም የጥጋብ ዓመታት ምድሪቱ የተትረፈረፈ ሰብል ሰጠች። 48በእነዚያ ሰባት የጥጋብ ዓመታት፣ ዮሴፍ በግብፅ አገር የተገኘውን ምርት ሰብስቦ በየከተሞቹ አከማቸ፤ በእያንዳንዱ ከተማ ከየአቅራቢያው የተመረተውን እህል እንዲከማች አደረገ። 49ዮሴፍ ብዛቱ እንደ ባሕር አሸዋ የሚሆን የእህል ሰብል አከማቸ፤ ሰብሉ እጅግ ከመብዛቱ የተነሣ ልኩን መስፈርና መመዝገብ አልቻለም ነበር።
50ሰባቱ የራብ ዓመታት ከመምጣቱ በፊት፣ የሄልዮቱ ካህን የጶጥፌራ ልጅ አስናት ለዮሴፍ ሁለት ወንዶች ልጆች ወለደችለት። 51ዮሴፍም፣ “እግዚአብሔር (ኤሎሂም) መከራዬን ሁሉ፣ የአባቴንም ቤት እንድረሳ አድርጎኛል” በማለት የመጀመሪያ ልጁን ስም ምናሴ#41፥51 ምናሴ የሚለው ቃል መርሳት የሚል ትርጕም ካለው የዕብራይስጥ ቃል የወጣ ሲሆን፣ ከዚሁ ቃል ጋር አንድ ዐይነት ድምፅ አለው። አለው። 52እንደዚሁም፣ “መከራ በተቀበልሁበት ምድር እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ፍሬያማ አደረገኝ” ሲል ሁለተኛ ልጁን ኤፍሬም#41፥52 ኤፍሬም የሚለው ቃል በዕብራይስጥ ዕጥፍ ፍሬያማ የሚል ትርጕም ካለው ቃል ጋር አንድ ዐይነት ድምፅ አለው። አለው።
53በግብፅ ምድር የነበረው ሰባቱ የጥጋብ ዘመን ዐለፈና 54ዮሴፍ አስቀድሞ እንደ ተናገረው የሰባቱ ዓመት የራብ ዘመን ጀመረ። ሌሎች አገሮች ሁሉ ሲራቡ፣ በመላው የግብፅ ምድር ግን ምግብ ነበር። 55ራቡ በመላው የግብፅ ምድር መስፋፋት ሲጀምር፣ ሕዝቡ ምግብ ይሰጠን በማለት ወደ ፈርዖን ጮኸ። ፈርዖንም ግብፃውያኑን፣ “ወደ ዮሴፍ ሂዱና የሚላችሁን አድርጉ” አላቸው።
56ራቡ በአገሩ ላይ እየተስፋፋ ስለ ሄደ፣ ዮሴፍ ጐተራዎቹን ከፍቶ እህሉ ለግብፃውያን እንዲሸጥ አደረገ፤ ምክንያቱም ራቡ በመላዪቱ ግብፅ ጸንቶ ነበር። 57ራቡ በመላው ዓለም ጸንቶ ስለ ነበር፣ የየአገሩ ሰዎች ሁሉ ከዮሴፍ ዘንድ እህል ለመሸመት ወደ ግብፅ ምድር መጡ።
Kasalukuyang Napili:
ዘፍጥረት 41: NASV
Haylayt
Ibahagi
Kopyahin
Gusto mo bang ma-save ang iyong mga hinaylayt sa lahat ng iyong device? Mag-sign up o mag-sign in
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጅ መብት © 2001 በ Biblica, Inc.
ፈቃድ የተገኘባቸው ናቸው። መብቱ በመላው ዓለም በሕግ የተጠበቀ።
Holy Bible, New Amharic Standard Version™ (Addisu Medebegna Tirgum™)
Copyright © 2001 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.