ዘፍጥረት 3
3
የሰው ውድቀት
1እባብ እግዚአብሔር አምላክ ከፈጠራቸው የዱር አራዊት ሁሉ ተንኰለኛ ነበረ፤ ሴቲቱንም፣ “በርግጥ እግዚአብሔር፣ ‘በአትክልቱ ስፍራ ካሉ ዛፎች ከማናቸውም እንዳትበሉ’ ብሏልን?” አላት።
2ሴቲቱም እባቡን እንዲህ አለችው፤ “በአትክልቱ ስፍራ ካሉት ዛፎች ፍሬ መብላት እንችላለን፤ 3ነገር ግን እግዚአብሔር ‘በአትክልቱ ስፍራ መካከል ከሚገኘው ዛፍ ፍሬ እንዳትበሉ፤ እንዳትነኩትም፤ አለዚያ ትሞታላችሁ’ ብሏል።”
4እባቡም ሴቲቱን እንዲህ አላት፤ “መሞት እንኳ አትሞቱም፤ 5ከፍሬው በበላችሁ ጊዜ ዐይናችሁ እንደሚከፈትና መልካምና ክፉን በማወቅ፣ እንደ እግዚአብሔር እንደምትሆኑ እግዚአብሔር ስለሚያውቅ ነው።”
6ሴቲቱ የዛፉ ፍሬ ለመብል መልካም፣ ለዐይን የሚያስደስትና ጥበብንም ለማግኘት የሚያጓጓ እንደ ሆነ ባየች ጊዜ፣ ከፍሬው ወስዳ በላች፤ ከርሷም ጋራ ለነበረው ለባሏ ሰጠችው፤ እርሱም በላ። 7የሁለቱም ዐይኖች ተከፈቱ፤ ዕራቍታቸውን መሆናቸውንም ተገነዘቡ። ስለዚህ የበለስ ቅጠል ሰፍተው አገለደሙ።
8ቀኑ መሸትሸት ሲል፣ እግዚአብሔር አምላክ በአትክልቱ ስፍራ ሲመላለስ አዳምና ሚስቱ ድምፁን ሰምተው ከእግዚአብሔር አምላክ ፊት በዛፎቹ መካከል ተሸሸጉ። 9እግዚአብሔር አምላክ ግን አዳምን ተጣርቶ፣ “የት ነህ?” አለው።
10አዳምም፣ “ድምፅህን በአትክልቱ ስፍራ ሰማሁ፤ ዕራቍቴን ስለ ሆንሁ ፈራሁ፤ ተሸሸግሁም” ብሎ መለሰ።
11 እግዚአብሔርም፣ “ዕራቍትህን መሆንህን ማን ነገረህ? ‘ከርሱ እንዳትበላ’ ብዬ ካዘዝሁህ ዛፍ በላህን?” አለው።
12አዳምም፣ “ይህች ከእኔ ጋራ እንድትኖር የሰጠኸኝ ሴት፣ እርሷ ከዛፉ ፍሬ ሰጠችኝና በላሁ” አለ።
13 እግዚአብሔር አምላክ ሴቲቱን፣ “ይህ ያደረግሽው ምንድን ነው?” አላት።
እርሷም፣ “እባብ አሳሳተኝና በላሁ” አለች።
14 እግዚአብሔር አምላክ እባብን እንዲህ አለው፤ “ይህን ስለ ሠራህ፣
“ከከብቶችና ከዱር እንስሳት ሁሉ
ተለይተህ የተረገምህ ሁን፤
በሕይወትህ ዘመን ሁሉ፣ በደረትህ
እየተሳብህ ትሄዳለህ፤
ዐፈርም ትበላለህ።
15በአንተና በሴቲቱ፣
በዘርህና በዘሯ መካከል፣
ጠላትነትን አደርጋለሁ፤
እርሱ ራስህን ይቀጠቅጣል፤#3፥15 ወይም ይመታል
አንተም ተረከዙን ትቀጠቅጣለህ።”
16ሴቲቱንም እንዲህ አላት፤
“በምጥ ጊዜ ጭንቅሽን አበዛለሁ፤
በሥቃይም ትወልጃለሽ፤
ፍላጎትሽም ወደ ባልሽ ይሆናል፤
እርሱም የበላይሽ ይሆናል።”
17አዳምንም እንዲህ አለው፤ “የሚስትህን ቃል ሰምተህ፣ ‘ከርሱ አትብላ’ ብዬ ያዘዝሁህን ዛፍ በልተሃልና፣
“ከአንተ የተነሣ ምድር የተረገመች ትሁን፤
በሕይወትህ ዘመን ሁሉ
ምግብህን ጥረህ ግረህ ከርሷ ታገኛለህ።
18ምድርም እሾኽና አሜከላ
ታበቅልብሃለች፤
ከቡቃያዋም ትበላለህ።
19ከምድር ስለ ተገኘህ፣
ወደ መጣህበት መሬት እስክትመለስ
ድረስ
እንጀራህን በፊትህ ላብ ትበላለህ፤
ዐፈር ነህና
ወደ ዐፈር ትመለሳለህ።”
20አዳምም#3፥20 ወይም ሰውየው የሕያዋን ሁሉ እናት ናትና ሚስቱን ሔዋን#3፥20 ሔዋን ማለት ሕያው ማለት ሳይሆን አይቀርም። ብሎ ጠራት።
21 እግዚአብሔር አምላክ ከቈዳ ልብስ አዘጋጅቶ አዳምንና ሚስቱን አለበሳቸው። 22ከዚያም እግዚአብሔር አምላክ፣ “ሰው መልካምንና ክፉውን ለይቶ በማወቅ ረገድ አሁን ከእኛ እንደ አንዱ ሆኗል፤ አሁን ደግሞ እጁን ዘርግቶ ከሕይወት ዛፍ ቀጥፎ እንዳይበላ፣ ለዘላለምም እንዳይኖር ይከልከል” አለ። 23ስለዚህ የተገኘበትን ምድር እንዲያርስ፣ እግዚአብሔር አምላክ ሰውን ከዔድን የአትክልት ስፍራ አስወጣው፤ 24ሰውንም ካስወጣው በኋላ፣ ወደ ሕይወት ዛፍ የሚወስደውን መንገድ ለመጠበቅ ኪሩቤልንና በየአቅጣጫው የምትገለባበጥ ነበልባላዊ ሰይፍ ከዔድን በስተምሥራቅ አኖረ።#3፥24 ወይም ፊት ለፊት አስቀመጠ
موجودہ انتخاب:
ዘፍጥረት 3: NASV
سرخی
شئیر
کاپی
کیا آپ جاہتے ہیں کہ آپ کی سرکیاں آپ کی devices پر محفوظ ہوں؟ Sign up or sign in
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.