ዘፍጥረት 6
6
የጥፋት ውሃ
1ሰዎች በምድር ላይ እየበዙ ሲሄዱ ሴቶች ልጆች ተወለዱላቸው። 2የእግዚአብሔር ወንዶች ልጆች የሰዎችን ሴቶች ልጆች ውብ ሆነው አዩአቸው፤ ከመካከላቸውም የመረጧቸውን አገቡ። 3እግዚአብሔርም፣ “ሰው ሟች#6፥3 ወይም በስባሽ ስለ ሆነ መንፈሴ እያዘነ#6፥3 ወይም መንፈሴ አይኖርም ከርሱ ጋራ ለዘላለም አይኖርም፤ ዕድሜው 120 ዓመት ይሆናል” አለ።
4የእግዚአብሔርም ልጆች የሰዎችን ሴቶች ልጆች ተገናኝተው ልጆች በወለዱ ጊዜም ሆነ ከዚያም በኋላ ኔፊሊም የተባሉ ሰዎች በምድር ላይ ነበሩ። እነርሱም በጥንቱ ዘመን በጀግንነታቸው ከፍ ያለ ዝና ያተረፉ ናቸው።
5 እግዚአብሔር አምላክ የሰው ዐመፅ በምድር ላይ የበዛና የልቡም ሐሳብ ዘወትር ወደ ክፋት ብቻ ያዘነበለ መሆኑን ተመለከተ። 6እግዚአብሔር ሰውን በምድር ላይ በመፍጠሩ ተጸጸተ፤ ልቡም እጅግ ዐዘነ። 7ስለዚህም እግዚአብሔር፣ “የፈጠርሁትን የሰው ዘር ከምድረ ገጽ አጠፋለሁ፤ ከሰው እስከ እንስሳ በምድር ላይ ከሚሳቡ ፍጥረታት እስከ ሰማይ ወፎች አጠፋለሁ፤ ስለ ፈጠርኋቸው ተጸጽቻለሁና” አለ። 8ኖኅ ግን በእግዚአብሔር ዘንድ ሞገስን አገኘ።
9የኖኅ ታሪክ እንደሚከተለው ነው።
ኖኅ በዘመኑ ከነበሩት ሰዎች ሁሉ ይልቅ ጻድቅና ነቀፋ የሌለበት ሰው ነበር፤ አካሄዱንም ከእግዚአብሔር ጋራ አደረገ። 10ኖኅም ሴም፣ ካምና ያፌት የሚባሉ ሦስት ወንዶች ልጆች ነበሩት።
11ምድር በእግዚአብሔር ፊት በክፉ ሥራ ረከሰች፤ በዐመፅም ተሞላች። 12እግዚአብሔር ምድር ምን ያህል በክፉ ሥራ እንደ ረከሰች አየ። እነሆ፤ ሰው ሁሉ አካሄዱን አበላሽቶ ነበርና 13ስለዚህ እግዚአብሔር ኖኅን እንዲህ አለው፦ “ሰውን ሁሉ ላጠፋ ነው፤ ምድር በሰው ዐመፅ ስለ ተሞላች በርግጥ ሰውንም ምድርንም አጠፋለሁ። 14አንተ ግን በጎፈር#6፥14 በዕብራይስጥ የዚህ ቃል ትርጕም አይታወቅም። ዕንጨት መርከብ ሥራ፤ ለመርከቧም ክፍሎች አብጅላት፤ ውስጧንና ውጭዋን በቅጥራን ለብጠው። 15እንዲህ አድርገህ ሥራት፦ ርዝመቷ መቶ አርባ ሜትር፣ ወርዷ ሃያ ሦስት ሜትር፣ ከፍታዋ ዐሥራ ሦስት ነጥብ ዐምስት ሜትር ይሁን። 16ለመርከቧ ጣራ አብጅላት፣ ጣራና ግድግዳው በሚጋጠምበት ቦታ ግማሽ ሜትር ክፍተት ተው፤#6፥16 ወይም ለብርሃን መግቢያ አድርገህ ሥራ ከጐኗ በር አውጣላት፤ ባለሦስት ፎቅ አድርገህ ሥራት። 17እኔም ከሰማይ በታች የሕይወት እስትንፋስ ያለባቸውን ሕያዋን ፍጥረታት ሁሉ ለማጥፋት እነሆ፤ በምድር ላይ የጥፋት ውሃ አወርዳለሁ፤ በምድር ላይ ያለ ሁሉ ይጠፋል። 18ከአንተ ጋራ ግን ቃል ኪዳን እመሠርታለሁ። አንተና ወንዶች ልጆችህ፣ ሚስትህና የልጆችህ ሚስቶች ከአንተ ጋራ ወደ መርከቧ ትገባላችሁ። 19ከአንተ ጋራ በሕይወት እንዲቈዩ ከሕያዋን ፍጥረታት ሁሉ ተባዕትና እንስት እያደረግህ ሁለት ሁለቱን ወደ መርከቧ ታስገባለህ። 20ከእያንዳንዱ የወፍ ወገን፣ ከእያንዳንዱ የእንስሳ ወገን፣ በምድር ላይ ከሚሳቡ ፍጥረታት ሁሉ በየወገናቸው በሕይወት ይቈዩ ዘንድ ሁለት ሁለት እየሆኑ ወደ አንተ ይመጣሉ። 21ለአንተና ለእነርሱ የሚያስፈልገውን ምግብ ሁሉ አከማች።”
22ኖኅም ሁሉን እግዚአብሔር እንዳዘዘው አደረገ።
موجودہ انتخاب:
ዘፍጥረት 6: NASV
سرخی
شئیر
کاپی
کیا آپ جاہتے ہیں کہ آپ کی سرکیاں آپ کی devices پر محفوظ ہوں؟ Sign up or sign in
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.