ማቴዎስ 13:24-43

ማቴዎስ 13:24-43 NASV

ኢየሱስም ሌላ ምሳሌ እንዲህ ሲል ነገራቸው፤ “መንግሥተ ሰማይ በዕርሻው ቦታ ጥሩ ዘር የዘራን ሰው ትመስላለች። ነገር ግን ሰው ሁሉ ተኝቶ ሳለ፣ ጠላቱ መጥቶ በስንዴው መካከል እንክርዳድ ዘርቶ ሄደ። ስንዴው በቅሎ ማፍራት ሲጀምር እንክርዳዱም ዐብሮ ብቅ አለ። “የዕርሻው ባለቤት ባሪያዎችም ወደ እርሱ ቀርበው፣ ‘ጌታ ሆይ፤ በዕርሻህ ቦታ ጥሩ ዘር ዘርተህ አልነበረምን? እንክርዳዱ ከየት መጣ?’ አሉት። “እርሱም፣ ‘የጠላት ሥራ ነው’ አላቸው። “ባሮቹም፣ ‘እንክርዳዱን ሄደን እንድንነቅለው ትፈልጋለህ?’ ብለው ጠየቁት። “እርሱ ግን፣ ‘አይሆንም፤ ምክንያቱም እንክርዳዱን እንነቅላለን ስትሉ ስንዴውንም ዐብራችሁ ልትነቅሉ ትችላላችሁ፤ ተዉአቸው፤ እስከ መከር ጊዜ ዐብረው ይደጉ። በዚያ ጊዜ ዐጫጆቹን እንክርዳዱን አስቀድማችሁ ንቀሉ፤ በእሳትም እንዲቃጠል በየነዶው እሰሩት፤ ስንዴውን ግን ሰብስባችሁ በጐተራዬ ክተቱ እላቸዋለሁ’ አላቸው።” ሌላ ምሳሌ እንዲህ ሲል ነገራቸው፤ “መንግሥተ ሰማይ አንድ ሰው ወስዶ በዕርሻው ቦታ የዘራትን የሰናፍጭ ዘር ትመስላለች። የሰናፍጭ ዘር ከሌሎች ሁሉ ያነሰች ብትሆንም፣ ስታድግ ግን ከአትክልት ሁሉ በልጣ፣ የሰማይ ወፎች መጥተው በቅርንጫፎቿ ላይ እስኪያርፉ ድረስ ዛፍ ትሆናለች።” አሁንም ሌላ ምሳሌ እንዲህ ሲል ነገራቸው፤ “መንግሥተ ሰማይ ሴት ወስዳ ሊጡ በሙሉ እስኪቦካ ድረስ በሦስት መስፈሪያ ዱቄት ውስጥ በመደባለቅ የሸሸገችውን እርሾ ትመስላለች።” ኢየሱስ ለሕዝቡ ይህን ሁሉ በምሳሌ ተናገረ፤ ምንም ነገር ያለ ምሳሌ አይነግራቸውም ነበር። በዚህም በነቢዩ እንዲህ ተብሎ የተነገረው ተፈጸመ፤ “አፌን በምሳሌ እከፍታለሁ፤ ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ የተሰወረውንም እናገራለሁ።” ከዚያም ሕዝቡን ትቶ ወደ ቤት ገባ። ደቀ መዛሙርቱም ወደ እርሱ ቀርበው፣ “በዕርሻው ውስጥ ስላለው እንክርዳድ የተናገርኸውን ምሳሌ ትርጕም ንገረን” አሉት። እርሱም እንዲህ ሲል መለሰ፤ “ጥሩውን ዘር የዘራው የሰው ልጅ ነው፤ ዕርሻውም ይህ ዓለም ነው፤ ጥሩው ዘር የእግዚአብሔርን መንግሥት ልጆች ያመለክታል፤ እንክርዳዱም የክፉው ልጆች ናቸው፤ ዘርቶት የሄደው ጠላትም ዲያብሎስ ነው፤ መከሩ የዓለም መጨረሻ ሲሆን፣ ዐጫጆቹም መላእክት ናቸው። “እንክርዳዱ ተነቅሎ በእሳት እንደሚቃጠል ሁሉ በዓለም መጨረሻም እንዲሁ ይሆናል። የሰው ልጅ መላእክቱን ይልካል፤ እነርሱም ለኀጢአት ምክንያት የሆኑትንና ክፉ የሚያደርጉትን ሁሉ ለቅመው ከመንግሥቱ ያወጣሉ። ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ወዳለበት ወደ እቶን እሳት ይጥሏቸዋል። በዚያ ጊዜ ጻድቃን በአባታቸው መንግሥት እንደ ፀሓይ ያበራሉ። ሰሚ ጆሮ ያለው ይስማ።