የማቴዎስ ወንጌል 13:24-43

የማቴዎስ ወንጌል 13:24-43 አማ05

እንዲሁም ኢየሱስ እንዲህ ሲል ሌላ ምሳሌ ነገራቸው፤ “መንግሥተ ሰማይ በእርሻው መልካም ዘር የዘራውን ሰው ትመስላለች፤ ነገር ግን ሰው ሁሉ ከተኛ በኋላ ጠላት መጣና በስንዴው ውስጥ እንክርዳድ ዘርቶ ሄደ። ስንዴው አድጎ ባፈራ ጊዜ እንክርዳዱም በዚያኑ ወቅት ታየ። ስለዚህ የእርሻው ባለቤት አገልጋዮች ወደ እርሱ ቀርበው ‘ጌታ ሆይ፥ በእርሻህ መልካም ዘር ዘርተህ አልነበረምን? ታዲያ፥ እንክርዳዱ ከወዴት መጣ?’ አሉት። እርሱም ‘ይህን ያደረገ ጠላት ነው’ አላቸው። አገልጋዮቹም ‘ታዲያ ሄደን እንክርዳዱን እንድንነቅለው ትፈልጋለህን?’ አሉት። እርሱ ግን እንዲህ ሲል መለሰላቸው ‘አይሆንም እንክርዳዱን ስትነቅሉ ስንዴውን አብራችሁ ትነቅላላችሁ። ስለዚህ ተዉአቸው፤ እስከ መከር ጊዜ ድረስ ስንዴውም እንክርዳዱም አብረው ይደጉ፤ በመከር ጊዜ ዐጫጆችን እንክርዳዱን አስቀድማችሁ ንቀሉ፤ በእሳት እንዲቃጠልም በየነዶው እሰሩ፤ ስንዴውን ግን ሰብስቡና በጐተራዬ ክተቱ’ እላቸዋለሁ።” ኢየሱስ ሌላ ምሳሌም እንዲህ ሲል ነገራቸው፦ “መንግሥተ ሰማይ አንድ ሰው ወስዶ በእርሻው የዘራትን የሰናፍጭ ዘር ትመስላለች። እርስዋ ከዘር ሁሉ ያነሰች ናት ባደገች ጊዜ ግን፥ ከአትክልቶች ሁሉ ትበልጣለች፤ ዛፍም ትሆናለች፤ ወፎችም መጥተው በቅርንጫፎችዋ ላይ ጎጆአቸውን ሠርተው ይሰፍሩባታል።” ደግሞም ኢየሱስ ይህን ምሳሌ ነገራቸው፦ “መንግሥተ ሰማይ አንዲት ሴት ወስዳ ከሦስት መስፈሪያ ዱቄት ጋር የለወሰችውን እርሾ ትመስላለች፤ እርሾውም ሊጡን ሁሉ እንዲቦካ አደረገው።” ኢየሱስ ይህን ሁሉ ነገር በምሳሌ ለሕዝቡ ተናገረ፤ ያለ ምሳሌም ምንም ነገር አልተናገራቸውም። ይህም የሆነበት ምክንያት በነቢይ እንዲህ ተብሎ የተጻፈው እንዲፈጸም ነው፦ “ንግግሬን በምሳሌ እገልጣለሁ፤ ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ የተሰወረውን እናገራለሁ።” ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ሕዝቡን አሰናብቶ ወደ ቤት ገባ፤ ደቀ መዛሙርቱም ወደ እርሱ ቀርበው፥ “የእርሻውን እንክርዳድ ምሳሌ ትርጒም አስረዳን” አሉት። ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “መልካሙን ዘር የዘራው የሰው ልጅ ነው፤ እርሻው ይህ ዓለም ነው፤ መልካሙ ዘር የእግዚአብሔር መንግሥት ልጆች ናቸው፤ እንክርዳዱ የሰይጣን ልጆች ናቸው። እንክርዳዱን የዘራው ጠላት ዲያብሎስ ነው፤ መከሩ የዓለም መጨረሻ ነው፤ ዐጫጆቹ መላእክት ናቸው። ልክ እንክርዳዱ ተነቅሎና በየነዶው ታስሮ እንደሚቃጠል ሁሉ በዓለም መጨረሻም እንዲሁ ይሆናል። በዚያን ጊዜ የሰው ልጅ መላእክቱን ይልካል፤ እነርሱም የኃጢአት ምክንያት የሆኑትንና ክፉ አድራጊዎችን ሁሉ ከእርሱ መንግሥት ሰብስበው ያወጣሉ፤ ወደ እቶን እሳትም ይጥሉአቸዋል፤ በዚያ ለቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል። ጻድቃን ግን በአባታቸው መንግሥት እንደ ፀሐይ ያበራሉ፤ ሰሚ ጆሮ ያለው ይስማ!”