የማቴዎስ ወንጌል 13:24-43

የማቴዎስ ወንጌል 13:24-43 አማ54

ሌላ ምሳሌ አቀረበላቸው እንዲህም አለ፦ መንግሥተ ሰማያት በእርሻው መልካም ዘርን የዘራን ሰው ትመስላለች። ሰዎቹ ሲተኙ ግን ጠላቱ መጣና በስንዴው መካከል እንክርዳድን ዘርቶ ሄደ። ስንዴውም በበቀለና በአፈራ ጊዜ እንክርዳዱ ደግሞ ያን ጊዜ ታየ። የባለቤቱም ባሮች ቀርበው፦ ጌታ ሆይ፥ መልካምን ዘር በእርሻህ ዘርተህ አልነበርህምን? እንክርዳዱንስ ከወዴት አገኘ? አሉት። እርሱም፦ ጠላት ይህን አደረገ አላቸው። ባሮቹም፦ እንግዲህ ሄደን ብንለቅመው ትወዳለህን? አሉት። እርሱ ግን፦ እንክርዳዱን ስትለቅሙ ስንዴውን ከእርሱ ጋር እንዳትነቅሉት አይሆንም። ተዉአቸው፤ እስከ መከር ጊዜ አብረው ይደጉ፤ በመከር ጊዜም አጫጆችን፦ እንክርዳዱን አስቀድማችሁ ልቀሙ በእሳትም ለማቃጠል በየነዶው እሰሩ፥ ስንዴውን ግን በጎተራዬ ክተቱ እላለሁ አለ። ሌላ ምሳሌ አቀረበላቸው እንዲህም አለ፦ መንግሥተ ሰማያት ሰው ወስዶ በእርሻው የዘራትን የሰናፍጭ ቅንጣት ትመስላለች፤ እርስዋም ከዘር ሁሉ ታንሳለች፥ በአደገች ጊዜ ግን፥ ከአታክልቶች ትበልጣለች የሰማይም ወፎች መጥተው በቅርንጫፎችዋ እስኪሰፍሩ ድረስ ዛፍ ትሆናለች። ሌላ ምሳሌ ነገራቸው እንዲህም አለ፦ መንግሥተ ሰማያት ሁሉ እስኪቦካ ድረስ ሴት ወስዳ በሦስት መስፈሪያ ዱቄት የሸሸገችውን እርሾ ትመስላለች። ኢየሱስም ለሕዝቡ ይህን ሁሉ በምሳሌ ተናገረ፤ በነቢዩም፦ በምሳሌ አፌን እከፍታለሁ፥ ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ የተሰወረውንም እናገራለሁ የተባለው ይፈጸም ዘንድ ያለ ምሳሌ አልተናገራቸውም። በዚያን ጊዜ ሕዝቡን ትቶ ወደ ቤት ገባ። ደቀ መዛሙርቱም ወደ እርሱ ቀርበው፦ የእርሻውን እንክርዳድ ምሳሌ ተርጕምልን አሉት። እርሱም መልሶ እንዲህ አላቸው፦ መልካምን ዘር የዘራው የሰው ልጅ ነው፤ እርሻውም ዓለም ነው፤ መልካሙም ዘር የመንግሥት ልጆች ናቸው፤ እንክርዳዱም የክፉው ልጆች ናቸው፥ የዘራውም ጠላት ዲያብሎስ ነው፤ መከሩም የዓለም መጨረሻ ነው፥ አጫጆችም መላእክት ናቸው። እንግዲህ እንክርዳድ ተለቅሞ በእሳት እንደሚቃጠል፥ በዓለም መጨረሻ እንዲሁ ይሆናል። የሰው ልጅ መላእክቱን ይልካል፥ ከመንግሥቱም እንቅፋትን ሁሉ ዓመፃንም የሚያደርጉትን ይለቅማሉ፥ ወደ እቶነ እሳትም ይጥሉአቸዋል፤ በዚያ ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል። በዚያን ጊዜ ጻድቃን በአባታቸው መንግሥት እንደ ፀሐይ ይበራሉ። የሚሰማ ጆሮ ያለው ይስማ።