መዝሙር 118
118
መዝሙር 118
1 እግዚአብሔር ቸር ነውና አመስግኑ፤
ፍቅሩም ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል።
2የእስራኤል ሕዝብ፣ “ምሕረቱ ለዘላለም ነው” ይበል።
3የአሮን ቤት፣ “ምሕረቱ ለዘላለም ነው” ይበል።
4 እግዚአብሔርን የሚፈሩ ሁሉ፣
“ምሕረቱ ለዘላለም ነው” ይበሉ።
5በተጨነቅሁ ጊዜ እግዚአብሔርን ጠራሁት፤
እግዚአብሔርም መለሰልኝ፤ ከመጠበብም አወጣኝ።
6 እግዚአብሔር ከእኔ ጋራ ነው፤ አልፈራም፤
ሰው ምን ሊያደርገኝ ይችላል?
7ይረዳኝ ዘንድ እግዚአብሔር ከእኔ ጋራ ነው፤
የጠላቶቼንም ውድቀት አያለሁ።
8ሰውን መከታ ከማድረግ ይልቅ፣
በእግዚአብሔር መታመን ይሻላል።
9በገዦች ተስፋ ከማድረግ ይልቅ፣
በእግዚአብሔር መታመን ይሻላል።
10ሕዝቦች ሁሉ ከበቡኝ፤
ነገር ግን በእግዚአብሔር ስም አስወግዳቸዋለሁ።
11መክበቡንስ በየአቅጣጫው ከበቡኝ፤
ነገር ግን በእግዚአብሔር ስም አስወግዳቸዋለሁ።
12እንደ ንብ መንጋ ከበቡኝ፤
ነገር ግን እንደሚነድድ እሾኽ ከሰሙ፤
በርግጥም በእግዚአብሔር ስም አስወግዳቸዋለሁ።
13ተገፍትሬ ልወድቅ ተንገደገድሁ፤
እግዚአብሔር ግን ረዳኝ።
14 እግዚአብሔር ብርታቴና ዝማሬዬ ነው፤
አዳኝ ሆነልኝ።
15በጻድቃን ድንኳን የእልልታና የሆታ ድምፅ፣
እንዲህ እያለ ያስተጋባል፤
“የእግዚአብሔር ቀኝ እጅ ብርቱ ሥራ ሠራች፤
16የእግዚአብሔር ቀኝ እጅ ከፍ ከፍ አለች፤
የእግዚአብሔር ቀኝ እጅ ብርቱ ሥራ ሠራች።”
17ተርፌ በሕይወት እኖራለሁ እንጂ አልሞትም፤
የእግዚአብሔርንም ሥራ ገና እናገራለሁ።
18መገሠጹን እግዚአብሔር እጅግ ገሥጾኛል፤
ነገር ግን ለሞት አሳልፎ አልሰጠኝም።
19የጽድቅን ደጆች ክፈቱልኝ፤
በዚያ ገብቼ እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ።
20ይህች የእግዚአብሔር ደጅ ናት፤
ጻድቃን በርሷ በኩል ይገባሉ።
21ሰምተህ መልሰህልኛልና፣
አዳኝም ሆነህልኛልና አመሰግንሃለሁ።
22ግንበኞች የናቁት ድንጋይ፣
እርሱ የማእዘን ራስ ሆነ።
23 እግዚአብሔር ይህን አድርጓል፤
ይህም ለዐይናችን ድንቅ ነው።
24 እግዚአብሔር የሠራት ቀን ይህች ናት፤
በርሷ ሐሤት እናድርግ፤ ደስም ይበለን።
25 እግዚአብሔር ሆይ፤ እባክህ አድነን፤
እግዚአብሔር ሆይ፤ እባክህ አሳካልን።
26በእግዚአብሔር ስም የሚመጣ ቡሩክ ነው።
ከእግዚአብሔር ቤት ባረክናችሁ።
27 እግዚአብሔር አምላክ ነው፤
ብርሃኑንም በላያችን አበራ፤
እስከ መሠዊያው#118፥27 ወይም የክብረ በዓልን መሥዋዕት በገመድ ማሰር ወይም መውሰድ ቀንዶች ድረስ በመውጣት፣
ዝንጣፊ ይዛችሁ በዓሉን ከሚያከብሩት ጋራ ተቀላቀሉ።
28አንተ አምላኬ ነህ፤ አመሰግንሃለሁ፤
አንተ አምላኬ ነህ፤ ከፍ ከፍ አደርግሃለሁ።
29ቸር ነውና እግዚአብሔርን አመስግኑ፤
ፍቅሩም ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል።
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጂ መብት © 2001, 2024 በBiblica, Inc.
በፈቃድ የሚወሰድ። በዓለም ዐቀፍ ባለቤትነቱ።
The Holy Bible, New Amharic Standard Version™
Copyright © 2001, 2024 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.