ኦሪት ዘጸአት 17
17
በተአምር ከአለት የፈለቀ ውሃ
(ዘዳ. 20፥1-13)
1መላው የእስራኤል ሕዝብ በእግዚአብሔር ትእዛዝ ከቦታ ወደ ቦታ በመዘዋወር “ሲን” ተብሎ የሚጠራውን ምድረ በዳ ትተው በረፊዲም ሰፈሩ፤ ነገር ግን በዚያ የሚጠጣ ውሃ አልነበረም። 2ስለዚህም “የምንጠጣው ውሃ ስጠን” ብለው በሙሴ ላይ አጒረመረሙ።
ሙሴም “ስለምን ትወቅሱኛላችሁ? ስለምንስ እግዚአብሔርን ትፈታተናላችሁ?” አላቸው።
3ሕዝቡ ግን እጅግ ተጠምተው ስለ ነበር “ከግብጽ ምድር ያወጣኸን ለምንድን ነው? እኛንና ልጆቻችንን እንስሶቻችንንም ጭምር በውሃ ጥም ለመፍጀት ነውን?” እያሉ በሙሴ ላይ ማጒረምረማቸውን ቀጠሉ።
4ሙሴም “ከቶ ይህን ሕዝብ ምን ባደርገው ይሻላል? እነሆ፥ በድንጋይ ሊወግሩኝ ተዘጋጅተዋል” እያለ ወደ እግዚአብሔር ጮኸ።
5እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ አለው፦ “ከእስራኤል ሕዝብ አለቆች፥ ጥቂቶቹን ውሰድ፤ ከሕዝቡም ቀድመህ ወደ ፊት ሂድ፤ የዐባይን ወንዝ የመታህበትንም በትር በእጅህ ያዝ፤ 6እነሆ፥ እኔ በሲና ተራራ በአለት ላይ በፊትህ እቆማለሁ፤ አንተም አለቱን ምታው፤ ሕዝቡም የሚጠጡት ውሃ ከውስጡ ይፈልቃል፤” ሙሴም በእስራኤል አለቆች ፊት እንደዚሁ አደረገ።
7እስራኤላውያን “እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ነው ወይስ አይደለም?” በማለት በማጒረምረማቸውና እግዚአብሔርን በመፈታተናቸው ያ ስፍራ ማሳህና እና መሪባ ተብሎ ተጠራ። #17፥7 ማሳህ፦ በዕብራይስጥ “መፈታተን” ማለት ነው። #17፥7 መሪባ፦ በዕብራይስጥ “ማጒረምረም” ወይም “መፈታተን” ማለት ነው።
በዐማሌቃውያን ላይ የተደረገ ጦርነት
8እስራኤላውያን በረፊዲም ሳሉ ዐማሌቃውያን መጥተው አደጋ ጣሉባቸው፤ 9ሙሴም ኢያሱን “ጥቂት ሰዎች ምረጥና በነገው ዕለት ዐማሌቃውያንን ውጋ፤ እኔም ተአምራት እንድፈጽምባት እግዚአብሔር የሰጠኝን በትር ይዤ በኮረብታው ጫፍ ላይ እቆማለሁ” አለው። 10ኢያሱም የሙሴን ትእዛዝ በመፈጸም ዐማሌቃውያንን ለመውጋት ወጣ፤ ሙሴ፥ አሮንና ሑር ወደ ኮረብታው ጫፍ ወጡ፤ 11ሙሴ እጆቹን ወደ ሰማይ በዘረጋ ጊዜ እስራኤላውያን ድል ያደርጉ ነበር፤ እጆቹን ባጠፈ ጊዜ ግን ዐማሌቃውያን እንደገና አንሰራርተው ያሸንፉ ነበር። 12የሙሴ እጆች ስለ ዛሉ አሮንና ሑር ድንጋይ አምጥተው ሙሴ እንዲቀመጥበት አደረጉ፤ በግራና በቀኝ ክንዶቹን ደግፈው በመቆም ፀሐይ እስከምትጠልቅበት ጊዜ ድረስ ቈዩ። 13በዚህ ሁኔታ ኢያሱ ዐማሌቃውያንን በሰይፍ ጠራርጎ አጠፋ።
14ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር ሙሴን “ዘወትር ሲታወስ እንዲኖር የዚህን ድል ታሪክ ጻፈው፤ ለኢያሱም ዐማሌቃውያንን ከምድር ጨርሼ የማጠፋቸው መሆኔን ንገረው” አለው። #ዘዳ. 25፥17-19፤ 1ሳሙ. 15፥2-9። 15ሙሴም መሠዊያ ሠርቶ “እግዚአብሔር የድል ሰንደቅ ዓላማዬ ነው” ብሎ ሰየመው፤ 16እንዲህም አለ “የእግዚአብሔርን ሰንደቅ ዓላማ ከፍ አድርጋችሁ ያዙ! እግዚአብሔር ዐማሌቃውያንን ለዘለዓለም ይዋጋቸዋል።” #17፥16 ያዙ፦ ወይም “እጁን በእግዚአብሔር ዙፋን ላይ ስለ ጫነ።”
Currently Selected:
ኦሪት ዘጸአት 17: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997