ኦሪት ዘጸአት 34
34
እንደገና የተሠሩት ሌሎች ሁለት የድንጋይ ጽላቶች
(ዘዳ. 10፥1-5)
1እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፦ “የመጀመሪያዎቹን የሚመስሉ ሁለት የድንጋይ ጽላቶች ቅረጽ፤ እኔም አንተ በሰበርካቸው ጽላቶች ላይ የነበሩትን ቃላት እጽፍባቸዋለሁ። 2ነገ ጠዋት ተዘጋጅተህ ከእኔ ጋር ለመገናኘት ወደ ሲና ተራራ ጫፍ ና። 3ከአንተ ጋር ማንም ሰው አይምጣ፤ በተራራው በማንኛውም በኩል ቢሆን ማንም ሰው አይታይ፤ በግ ወይም ከብት ማንኛውም እንስሳ በተራራው ግርጌ አይሰማራ።” 4ስለዚህ ሙሴ ሁለት የድንጋይ ጽላቶችን ልክ እንደ ፊተኞቹ ቀረጸ፤ በማግስቱም ጠዋት በማለዳ ተነሥቶ ልክ እግዚአብሔር እንዳዘዘው ጽላቶቹን ይዞ ወደ ሲና ተራራ ወጣ።
5እግዚአብሔርም በደመና ወርዶ ከእርሱ ጋር በዚያ ቆመ፦ “እኔ እግዚአብሔር ነኝ” ብሎ ቅዱስ ስሙንም አስታወቀው። 6እግዚአብሔር በፊቱ ሲያልፍ እንዲህ ብሎ ዐወጀ፤ “እኔ እግዚአብሔር ርኅሩኅና መሐሪ አምላክ ነኝ፤ እኔ ለቊጣ የዘገየሁ፤ ዘለዓለማዊ ፍቅሬና ታማኝነቴ የበዛ ነው፤ 7ዘለዓለማዊ ፍቅሬንም እስከ ብዙ ሺህ ትውልድ እጠብቃለሁ፤ በደልን መተላለፍንና ኃጢአትን ሁሉ ይቅር እላለሁ፤ ነገር ግን እስከ ሦስትና አራት ትውልድ ድረስ ስለ ወላጆቻቸው ኃጢአት ከመቅጣት አልገታም።” #ዘፀ. 20፥5-6፤ ዘኍ. 14፥18፤ ዘዳ. 5፥9-10፤ 7፥9-10።
8ሙሴም ወዲያውኑ በምድር ላይ ተደፍቶ ሰገደ፤ 9እንዲህም አለ፦ “እግዚአብሔር ሆይ፥ በአንተ ዘንድ ሞገስን አግኝቼ ከሆነ ከእኛ ጋር አብረህ እንድትወጣ እለምንሃለሁ፤ ይህ ሕዝብ እልኸኛ ነው፤ ነገር ግን ኃጢአታችንንና ክፉ ሥራችንን ሁሉ ይቅር በል፤ የራስህ ሕዝብ አድርገህ ተቀበለን።”
የቃል ኪዳኑ መታደስ
(ዘፀ. 23፥14-19፤ ዘዳ. 7፥1-5፤ 16፥1-17)
10እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፦ “እነሆ ከእስራኤል ሕዝብ ጋር ቃል ኪዳን እገባለሁ፤ ከዚህ በፊት በምድር ላይ በማንኛውም ሕዝብ ዘንድ ሆኖ የማያውቅ ድንቅ ነገር በሕዝብህ ፊት አደርጋለሁ፤ አስፈሪ የሆነ ድንቅ ነገር ስለማደርግ እኔ እግዚአብሔር የማደርጋቸውን ድንቅ ነገሮች በመካከላቸው የምትኖርባቸው ሕዝቦች ሁሉ ያያሉ። 11ዛሬ ለእናንተ የምሰጠውን ሕግ ጠብቁ፤ እኔም አሞራውያንን፥ ከነዓናውያንን፥ ሒታውያንን፥ ፈሪዛውያንን፥ ሒዋውያንንና ኢያቡሳውያንን ከፊታችሁ አባርራለሁ፤ 12አጥፊ ወጥመድ ስለሚሆኑባችሁ ከምትሄዱባቸው ሕዝቦች ጋር ቃል ኪዳን አትግቡ። 13ይልቅስ መሠዊያዎቻቸውን ሰባብሩ፤ የማምለኪያ ዐምዶቻቸውንም አፈራርሱ፤ አሼራ የተባለች አምላካቸውንም ምስሎች ሰባብራችሁ ጣሉ። #ዘዳ. 16፥21።
14“እኔ እግዚአብሔር ቀናተኛ አምላክ ስለ ሆንኩ ከእኔ በቀር ለሌሎች አማልክት አትስገዱ፤ 15ለከንቱ አማልክታቸው ሲሰግዱና መሥዋዕት ሲሠዉላቸው እንድትተባበሩአቸው ስለሚጠይቁአችሁ፥ እናንተም እነርሱ ለአማልክታቸው የሚያቀርቡትን ምግብ ለመብላት ስለምትፈተኑ፤ በአገሩ ከሚኖሩ ሕዝቦች ጋር ቃል ኪዳን አትግቡ። 16ሴቶች ልጆቻቸውን ለወንዶች ልጆቻችሁ ሚስቶች ብታደርጉ የእነዚያ ሴቶች ልጆች ጣዖት ማምለክን ስለሚከተሉ የእናንተንም ወንዶች ልጆች ጣዖት አምልኮን እንዲከተሉ ያደርጓቸዋል።
17“ብረት አቅልጣችሁ አማልክት አትሥሩ፤ #ዘፀ. 20፥4፤ ዘሌ. 19፥4፤ ዘዳ. 5፥8፤ 27፥15።
18“ከግብጽ የወጣችሁት በአቢብ ወር ስለ ሆነ የቂጣን በዓል በመጠበቅ በየዓመቱ አክብሩ፤ እንዳዘዝኳችሁ በአቢብ ወር እስከ ሰባት ቀን ቂጣ ብሉ። #ዘፀ. 12፥14-20፤ ዘሌ. 23፥6-8፤ ዘኍ. 28፥16-25።
19“በኲር ሆኖ የሚወለድ ወንድ ልጅ ሁሉ የእኔ ነው፤ የማንኛውም እንስሳ ተባዕት ሁሉ በሬም ሆነ በግ የእኔ ነው፤ #ዘፀ. 13፥2። 20ነገር ግን የበግ ጠቦት በመተካት የአህያን በኲር ለመዋጀት ትችላላችሁ፤ የማትዋጁት ከሆነ ግን አንገቱን ቈልምሙት፤ በኲር ሆኖ የተወለደውንም ወንድ ልጅ ሁሉ ትዋጃላችሁ። #ዘፀ. 13፥13።
“መባ ሳይዝ ማንም ሰው ባዶ እጁን በፊቴ አይታይ።
21“ሥራችሁን ሁሉ የምታከናውኑባቸው ስድስት ቀኖች አሉላችሁ፤ በእርሻም ሆነ በመከር ወራት በሰባተኛው ቀን ምንም ሥራ አትሥሩ። #ዘፀ. 20፥9-10፤ 23፥12፤ 31፥15፤ 35፥2፤ ዘሌ. 23፥3፤ ዘዳ. 5፥13-14።
22“የስንዴአችሁን በኲራት በምትሰበስቡበት ጊዜ የመከርን በዓል አክብሩ፤ የዓመቱ መጨረሻ በሆነው በፍሬ መከር ጊዜ የዳስን በዓል አክብሩ። #ዘሌ. 23፥15-21፤ ዘኍ. 28፥26-31።
23“በዓመት ሦስት ጊዜ ወንዶች ሁሉ ለእኔ ለእስራኤል አምላክ ለእግዚአብሔር ይሰግዱ ዘንድ ይምጡ። 24አሕዛብን ሁሉ አስወግጄ ግዛታችሁን አሰፋለሁ፤ ስለዚህ በእነዚህ በሦስት በዓላት ወቅት ወደ እኔ ስትቀርቡ አገራችሁን ለመውረር የሚመኝ ማንም አይመጣም።
25“ለእኔ የእንስሶች መሥዋዕት በምትሠዉበት ጊዜ ደሙን እርሾ ካለበት ኅብስት ጋር አታቅርቡልኝ ለፋሲካ በዓል ከታረደው እንስሳ ምንም ሥጋ እስከ ማግስቱ ጠዋት ድረስ አታቈዩ። #ዘፀ. 12፥10።
26“በየዓመቱ የመከራችሁን በኲራት ወደ እግዚአብሔር ቤት አምጡ። #ዘዳ. 24፥21፤ 26፥2።
“የበግም ሆነ የፍየል ግልገል በእናቱ ወተት አትቀቅሉ።”
27እግዚአብሔር ሙሴን፦ “ከአንተም ሆነ ከእስራኤል ሕዝብ ጋር ቃል ኪዳን የምገባው በዚህ ቃል መሠረት ስለ ሆነ ይህን ቃል በመጽሐፍ ጻፈው” አለው። 28ሙሴም ምንም ሳይበላና ሳይጠጣ ከእግዚአብሔር ጋር አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ቈየ፤ ጌታም በጽላቶቹ ላይ የቃል ኪዳን ቃላት የሆኑትን ዐሥሩን ትእዛዞች ጻፈ።
ሙሴ ከሲና ተራራ መውረዱ
29ሙሴ ከእግዚአብሔር ጋር ሲነጋገር ቈይቶ ስለ ነበር፥ ዐሥሩ ትእዛዞች የተጻፉባቸውን ሁለቱን የምስክር ጽላቶች ይዞ ከሲና ተራራ በወረደ ጊዜ ፊቱ አበራ፤ ለእርሱ ግን ይህ ሁሉ አይታወቀውም ነበር። #2ቆሮ. 3፥7-16። 30አሮንና ሕዝቡ ሁሉ ሙሴን ባዩ ጊዜ ፊቱ እንደሚያበራ ተመልክተው ወደ እርሱ ለመቅረብ ፈሩ። 31ሙሴ ግን ጠራቸው፤ አሮንና የሕዝቡ አለቆች ወደ እርሱ ቀርበው አነጋገራቸው። 32ከዚያም በኋላ የእስራኤል ሕዝብ በሙሉ ወደ እርሱ መጡ፤ ሙሴም በሲና ተራራ እግዚአብሔር የገለጠለትን ሕግ ሁሉ ሰጣቸው። 33ሙሴ ከእነርሱ ጋር መነጋገሩን ካበቃ በኋላ ፊቱን በሻሽ ሸፈነ፤ 34ሙሴ ከእግዚአብሔር ጋር ለመነጋገር ወደ እግዚአብሔር መገኛ ድንኳን በገባ ቊጥር ሻሹን ከፊቱ ላይ ያነሣ ነበር፤ ከዚያም በሚወጣበት ጊዜ የታዘዘውን ሁሉ ለእስራኤላውያን ይነግራቸው ነበር። 35እነርሱም ፊቱ ሲያበራ ያዩት ነበር፤ ስለዚህም ከእግዚአብሔር ጋር ለመነጋገር ወደዚያ እስከሚሄድበት ጊዜ ድረስ ፊቱን በሻሽ ይሸፍን ነበር።
Currently Selected:
ኦሪት ዘጸአት 34: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997