ማርታም “በመጨረሻው ቀን በትንሣኤ እንደሚነሣ አውቃለሁ፤” አለችው። ኢየሱስም “ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ፤ በእኔ የሚያምን ቢሞት እንኳ ሕያው ይሆናል፤ ሕያው የሆነና በእኔ የሚያምን ሁሉ ለዘለዓለም አይሞትም፤ ይህን ታምኚያለሽኝ?” አላት። እርሷም “አዎን ጌታ ሆይ፤ አንተ ወደ ዓለም የሚመጣው ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆንህ እኔ አምናለሁ” አለችው። ይህንም ብላ ሄደች፤ እኅትዋንም ማርያምን በስውር ጠርታ “መምህር መጥቷል፤ እየጠራሽም ነው፤” አለቻት። እርሷም በሰማች ጊዜ ፈጥና ተነሣች፥ ወደ እርሱም መጣች፤ ኢየሱስም ማርታ እርሱን በተቀበለችበት ስፍራ ነበረ እንጂ ገና ወደ መንደሩ አልገባም ነበር። ከእርሷ ጋር በቤት ሲያጽናኑአት የነበሩ አይሁድም፥ ማርያም ፈጥና እንደ ተነሣችና እንደ ወጣች ባዩ ጊዜ፥ ወደ መቃብር ሄዳ በዚያ ልታለቅስ መስሎአቸው ተከተሉአት። ማርያምም ኢየሱስ ወዳለበት መጥታ ባየችው ጊዜ በእግሩ ላይ ወድቃ “ጌታ ሆይ! አንተ እዚህ ብትሆን ኖሮ ወንድሜ ባልሞተ ነበር፤” አለችው። ኢየሱስም እርሷ ስታለቅስ ከእርሷም ጋር የመጡት አይሁድ ሲያለቅሱ አይቶ በመንፈሱ አዘነ በራሱም ታወከ፤ “ወዴት አኖራችሁት?” ዓለም። እነርሱም “ጌታ ሆይ! መጥተህ እይ፤” አሉት። ኢየሱስም እንባውን አፈሰሰ። ስለዚህም አይሁድ “እንዴት ይወደው እንደ ነበረ እዩ፤” አሉ። ከእነርሱ ግን አንዳንዶቹ “የዐይነ ሥውሩን ዐይኖች እንደ ከፈተ ይህም ሰው እንዳይሞት ማድረግ አይችልም ነበርን?” አሉ። ኢየሱስም በድጋሚ በጥልቅ ኀዘን ተውጦ ወደ መቃብሩ መጣ፤ መቃብሩም ዋሻ ነበረ፤ ድንጋይም ተገጥሞበት ነበር። ኢየሱስ “ድንጋዩን አንሡ፤” አለ። የሞተውም ሰው እኅት ማርታ “ጌታ ሆይ! ከሞተ አራት ቀን ሆኖታልና አሁን ይሸታል፤” አለችው። ኢየሱስ “ካመንሽ የእግዚአብሔርን ክብር እንደምታዪ አልነገርሁሽምን?” አላት። ድንጋዩንም አነሡት። ኢየሱስም ዐይኖቹን ወደ ላይ አንሥቶ እንዲህ አለ፥ “አባት ሆይ! ስለ ሰማኸኝ አመሰግንሃለሁ። ሁልጊዜም እንደምትሰማኝ አወቅሁ፤ ነገር ግን አንተ እንደ ላክኸኝ ያምኑ ዘንድ በዚህ ዙሪያ ስለ ቆሙት ሕዝብ ተናገርሁ፤” ይህንም ብሎ በታላቅ ድምፅ “አልዓዛር ሆይ! ና፥ ወደ ውጭ ውጣ፤” ብሎ ጮኸ። ሞቶ የነበረውም ሰው እጆቹና እግሮቹ እንደ ተገነዙ ወጣ፤ ፈቱም በጨርቅ እንደ ተጠመጠመ ነበረ። ኢየሱስም “ፍቱትና ይሂድ፤ ተዉት፤” አላቸው። ስለዚህ ወደ ማርያም ከመጡት፥ ኢየሱስም ያደረገውን ካዩት ከአይሁድ ብዙዎች በእርሱ አመኑ፤
የዮሐንስ ወንጌል 11 ያንብቡ
ያዳምጡ የዮሐንስ ወንጌል 11
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የዮሐንስ ወንጌል 11:24-45
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች