የሐዋርያት ሥራ 6
6
ስለ ሰብዐቱ ዲያቆናት መሾም
1በዚያም ወራት ደቀ መዛሙርት በበዙ ጊዜ ከግሪክ የመጡ ደቀ መዛሙርት በአይሁድ ምእመናን ላይ አንጐራጐሩባቸው፤ የዕለት የዕለቱን ምግብ ሲያካፍሉ ባልቴቶቻቸውን ቸል ይሉባቸው ነበርና። 2ዐሥራ ሁለቱም ሐዋርያት ሕዝቡን ሁሉ ጠርተው እንዲህ አሉአቸው፥ “የእግዚአብሔርን ቃል ትተን ማዕድን እናገለግል ዘንድ የሚገባ አይደለም። 3ወንድሞቻችን ሆይ፥ ከእናንተ ወገን በመልካም የተመሰከረላቸውን መንፈስ ቅዱስና ጥበብ የሞላባቸውን ሰባት ሰዎችን ምረጡ፤ ለዚህ ሥራም እንሾማቸዋለን። 4እኛ ግን ለጸሎትና ቃሉን ለማስተማር እንተጋለን።” 5#አንዳንድ የግእዝ ዘርዕ “ሕዝቡም ሁሉ ተስማሙ” የሚል ይጨምራል።ይህም ነገር በእነርሱ ዘንድ የተወደደ ሆነ፤ ሃይማኖቱ የቀናና መንፈስ ቅዱስ ያደረበትን ሰው እስጢፋኖስን፥ ፊልጶስን፥ ጵሮኮሮስን፥ ኒቃሮናን፥ ጢሞናን፥ ጰርሜናን፥ ወደ ይሁዲነት የተመለሰውን የአንጾኪያውን ኒቆላዎስንም መረጡ። 6በሐዋርያትም ፊት አቆሙአቸው፤ ጸልየውም እጃቸውን በራሳቸው ላይ ጫኑ።
7የእግዚአብሔርም ቃል ከፍ ከፍ አለ፤ በኢየሩሳሌምም ምእመናን እጅግ በዙ፤ ከካህናትም መካከል ያመኑ ብዙዎች ነበሩ።
አይሁድ እስጢፋኖስን እንደ ተቃወሙት
8እስጢፋኖስም የእግዚአብሔር ጸጋና ኀይል የመላበት ሰው ነበር፤ በሕዝቡም መካከል ታላላቅ ተአምራትንና ድንቅ ሥራን ይሠራ ነበር። 9የነጻ ወጭዎች ከምትባለው ምኵራብም ከቀሬናና ከእስክንድርያ፥ ከቂልቅያና ከእስያ የሆኑ ሰዎችም ተነሥተው እስጢፋኖስን ይከራከሩት ነበር። 10ነገር ግን ይቃወሙት ዘንድ አልቻሉም፤ በጥበብና በመንፈስ ቅዱስ ይከራከራቸው ነበርና። 11ከዚህም በኋላ “ይህን ሰው በሙሴና በእግዚአብሔር ላይ የስድብን ቃል ሲናገር ሰምተነዋል” የሚሉ የሐሰት ምስክሮችን አስነሡበት፤ 12ሕዝቡን፥ ሽማግሌዎችንና ጸሓፊዎችንም አነሳሡአቸው፤ ከበውም እየጐተቱ ወደ ሸንጎ አቀረቡት። 13የሐሰት ምስክሮችንም አቆሙበት፤ እነርሱም እንዲህ አሉ፥ “ይህ ሰው በዚህ ቤተ መቅደስ ላይና በኦሪት ላይ የስድብ ቃል እየተናገረ ዝም በል ቢሉት እንቢ አለ፤ 14የናዝሬቱ ኢየሱስ ይህን ቤተ መቅደስ ያፈርሰዋል፤ ሙሴም የሰጠንን ኦሪታችንን ይሽራል ሲል ሰምተነዋል።” 15በሸንጎም ተቀምጠው የነበሩት ሁሉ ትኩር ብለው ተመለከቱት፤ ፊቱንም እንደ እግዚአብሔር መልአክ ፊት ሆኖ አዩት።
Currently Selected:
የሐዋርያት ሥራ 6: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ