ትንቢተ ሕዝቅኤል 27
27
ስለ ጢሮስ የወጣ ሙሾ
1የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ 2“አንተ የሰው ልጅ ሆይ! ስለ ጢሮስ ሙሾ አድርግ። 3በባሕር መግቢያ የምትኖር፥ በብዙም ደሴቶች ላይ ከሚኖሩ አሕዛብ ጋር ንግድን የምታደርግ ጢሮስን እንዲህ በላት፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ጢሮስ ሆይ! አንቺ፦ በውበት ፍጹም ነኝ ብለሻል። 4ዳርቻሽ በባሕር ውስጥ ነው፤ ልጆችሽም#ዕብ. “ሠራተኞችሽ” ይላል። ውበትሽን ፈጽመዋል። 5ሳንቃዎችሽን ሁሉ ከሳኔር ጥድ ሠርተዋል፤ ምሰሶዎችሽንም ይሠሩልሽ ዘንድ ከሊባኖስ ዝግባን ወስደዋል። 6ከባሳን ኮምቦል መቅዘፊያሽን ሠርተዋል፤ መቅደስሽንም በዝኆን ጥርስ ሠሩ፤ ከኪቲም ደሴቶች ዛፍም ቤቶችሽን ሠርተዋል። 7ዓላማ እንዲሆንልሽ ሸራሽ ከግብፅ በፍታና ከወርቀ ዘቦ ተሠርቶአል፤ መደረቢያሽም ከኤሊሳ ደሴቶች ሰማያዊና ቀይ ሐር ተሠርቶአል። 8አለቆችሽ በሲዶና ይኖሩ ነበር፤ የአራድ ሰዎችም ቀዛፊዎችሽ ነበሩ፤ ጢሮስ ሆይ! ጥበበኞችሽ በአንቺ ዘንድ ነበሩ፤ የመርከቦችሽም መሪዎች ነበሩ። 9#ግሪክ ሰባ. ሊ. “የቢብልያን ሽማግሌዎችና በአንች ዘንድ የነበሩ ጥበበኞች ጉባኤሽን ይረዱ ነበር ፤ የባሕር መርከቦች ሁሉና መርከበኞችም እስከ ሩቅ ምዕራብ ድረስ ለአንቺ ይነግዱ ነበር” ይላል።በአንቺ ውስጥ የነበሩ የጌባል ሽማግሌዎችና ጥበበኞችዋ ስብራትሽን ይጠግኑ ነበር፤ ከአንቺም ጋር ይነግዱ ዘንድ የባሕር መርከቦች ሁሉና መርከበኞቻቸው በመካከልሽ ነበሩ። 10ፋርስና ሉድ፥ ሊብያም#ዕብ. “ፉጥ” ይላል። በሠራዊትሽ ውስጥ ሰልፈኞችሽ ነበሩ፤ ጋሻና ራስ ቍርም በአንቺ ውስጥ ያንጠለጥሉ ነበር፤ እነርሱም ክብርሽን ሰጡ። 11የአራድ ልጆችና ሠራዊቶችሽ በቅጥሮችሽ ላይ በዙሪያ ነበሩ፤ ገማዳውያንም በግንቦችሽ ውስጥ ነበሩ፤ የጦር መሣሪያቸውንም በዙሪያ በቅጥርሽ ላይ አንጠለጠሉ፤ ውበትሽንም ፈጽመዋል።
12“ከኀይልሽ#ዕብ. “ከብልጥግናሽ” ይላል። ሁሉ ብዛት የተነሣ የተርሴስ#ግሪኩ “የካርቴጅ” ይላል። ሰዎች ነጋዴዎችሽ ነበሩ፤ ገበያሽን ብር፥ ወርቅና ብረት፥ ቆርቆሮና እርሳስም አደረጉ። 13ያዋንና ቶቤል፥ ሞሳሕም ነጋዴዎችሽ ነበሩ፤ ንግድሽንም በሰዎች ነፍሳትና በናስ ዕቃ አደረጉ። 14ከቴርጋማ ቤትም የነበሩት ሰዎች ፈረሶችንና ፈረሰኞችን፥ በቅሎዎችንም ወደ ገበያሽ አመጡልሽ። 15የሮድያን ልጆችም ነጋዴዎችሽ ነበሩ፥ ብዙ የሆኑ የደስያት ሰዎችም የዝኆን ጥርስ ይነግዱልሽ ነበር፤ ከዚያም የመጡ ሰዎች ዋጋሽን ይሰጡሽ ነበር። 16የሶርያም ሰዎች ከገንዘብሽ ብዛት የተነሣ ነጋዴዎችሽ ነበሩ፥ ከአንቺም ጋር አንድ ከሆኑ ከብዙ ሰዎች ጋር ትነግጂ ነበር፤ ነጭ ሐርንና ዕንቍን፥ ቀይ ሐርንና ወርቀ ዘቦን ከርከዴን የሚባል ዕንቍንና ልባንጃም የሚባል ሽቱን ከተርሴስ ያመጡልሽ ነበር፤ ገበያሽንም ረዓሙትና ቆርኮር መሉት። 17ይሁዳና እስራኤል ነጋዴዎችሽ ነበሩ፤ ስንዴንም ይሸምቱልሽ ነበር፤ ሰሊሆትንና በለሶንን፥ ዘይትንና የተወደደ ማርን፥ ርጢንንም ከአንቺ ጋር አንድ ይሆኑ ዘንድ ሰጡሽ። 18ከሥራሽ ብዛትና ከብልጽግናሽ ሁሉ ብዛት የተነሣ የደማስቆ ሰዎች ነጋዴዎችሽ ነበሩ፤ በኬልቦን የወይን ጠጅ፥ በነጭም የበግ ጠጕር ይነግዱ ነበር። 19ዳንና ያዋን፤ ከኦሴል የተሠራ ብረትንና ብርጕድን፥ ቀረፋንም ያመጡልሽ ነበር። 20ድዳን በተመረጡ እንስሳትና በሠረገላቸው፥ በክብር ልብስም ነጋዴሽ ነበረች። 21ዓረብና የቄዳር አለቆች ሁሉ የእጅሽ ነጋዴዎች ነበሩ፤ በግመሎችና በአውራ በጎች፥ በፍየሎችም በእነዚህ ከአንቺ ጋር ይነግዱ ነበር። 22የሳባና የራዕማ ነጋዴዎች እነዚህ ነጋዴዎችሽ ነበሩ፤ ንግድሽን በጥሩ ሽቱና በከበረ ድንጋይ ሁሉ፥ በወርቅም አደረጉ። 23የካራንና የካኔ፥ የኤደንም ሰዎች ነጋዴዎችሽ ነበሩ፤ አሦርና ኪልማድም ነጋዴዎችሽ ነበሩ። 24እነዚህ በአማረ ልብስ፥ በሰማያዊ ካባ፥ በወርቀ ዘቦም፥ በዝግባ በተሠራች፥ በገመድም በታሰረች፥ በግምጃም በተሞላች ሣጥን በገበያሽ ይነግዱ ነበር። 25የተርሴስ መርከቦች ሸቀጥሽን የሚሸከሙ ነበሩ፤ አንቺም ተሞልተሽ ነበር፤ በባሕርም ውስጥ እጅግ ከበርሽ።
26“ቀዛፊዎችሽ ወደ ትልቁ ውኃ አመጡሽ፤ የምሥራቅ ነፋስ በባሕር ውስጥ ሰበረሽ። 27ኀይልሽና ዋጋሽ፥ ንግድሽም፥ መርከበኞችሽም፥ መርከብ መሪዎችሽም፥ ሰባራሽን የሚጠግኑ ነጋዴዎችሽም፥ በአንቺም ዘንድ ያሉ ሰልፈኞችሽ ሁሉ በውስጥሽ ከአሉት ጉባኤ ሁሉ ጋር በወደቅሽበት ቀን በባሕር ውስጥ ይጠፋሉ። 28ከጩኸትሽ የተነሣ የመርከብሽ መሪዎች ፍርሀትን ፈሩ።#ዕብ. “ከመርከብ መሪዎች ጩኸት የተነሣ በዙሪያሽ ያሉ ሁሉ ይንቀጠቀጣሉ” ይላል። 29ቀዛፊዎችም ሁሉ፥ በመርከብ የተጫኑትም መርከብ መሪዎችም ሁሉ ከመርከቦቻቸው ይወርዳሉ፤ በየብስም ላይ ይቆማሉ፤ 30ድምፃቸውንም በአንቺ ላይ ያሰማሉ፤ ምርር ብለውም ይጮኻሉ፤ በራሳቸውም ላይ ትቢያ ይነሰንሳሉ፤ አመድም ያነጥፋሉ። 31ስለ አንቺም የራሳቸውን ጠጕር ይላጫሉ፤ ማቅም ያሸርጣሉ፤ በነፍስም ምሬት ስለ አንቺ መራራ ልቅሶን ያለቅሳሉ። 32ልጆቻቸውም ሙሾን ያሞሹልሻል፤ በባሕር መካከል እንደ ታወከች እንደ ጢሮስ ያለ ማን ነበር? ይላሉ። 33በባሕር ውስጥ ምን ያህል ዋጋ ታገኚ ነበር? በብልጥግናሽ ብዛት ብዙ አሕዛብን አጠገብሽ፤ ከአንቺም ጋር አንድ ከሆኑት ለይተሽ የምድርን ነገሥታት ሁሉ ባለጸጎች አደረግሻቸው። 34አሁን ግን በጥልቅ ውኃ ውስጥ በባሕር ተሰብረሻል፤ ከአንቺ ጋር አንድ የሆኑ ሁሉ በመካከልሽ ወድቀዋል። ቀዛፊዎችሽም ሁሉ ይወድቃሉ፤ 35በደሴቶች የሚኖሩ ሁሉ አለቀሱልሽ፤ ነገሥታቶቻቸውም እጅግ ፈርተዋል ፊታቸውንም ነጭተው አለቀሱ። 36የአሕዛብ ነጋዴዎችም አፍዋጩብሽ፤ አንቺም ፈጽመሽ ትጠፊያለሽ፤ ከእግዲህም ወዲያ እስከ ዘለዓለም አትኖሪም።”
Currently Selected:
ትንቢተ ሕዝቅኤል 27: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ