ትንቢተ ሕዝቅኤል 28
28
በጢሮስ ንጉሥ ላይ የተነገረ ትንቢት
1የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ 2“አንተ የሰው ልጅ ሆይ! የጢሮስን አለቃ እንዲህ በለው፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ልብህ ኰርትዋል፥ አንተ እኔ እግዚአብሔር ነኝ፥ እግዚአብሔርም በባሕር መካከል እንዲቀመጥ እኔም ተቀምጫለሁ ብለሃልና፤ አንተ ሰው ስትሆን ልብህን እንደ እግዚአብሔር ልብ ብታደርግም አንተ እግዚአብሔር አይደለህም። 3ከዳንኤል ይልቅ አንተ ጥበበኛ ነህን? ብልሃተኞችም በጥበባቸው አላስተማሩህም። 4በጥበብህና በማስተዋልህ ብልጽግናን ለራስህ አግኝተሃልን? ወርቅንና ብርንም በግምጃ ቤትህ ውስጥ ሰብስበሃልን? 5በታላቅ ጥበብህና በንግድህ ብልጽግናህን አብዝተሃል፤ በብልጽግናህም ልብህ ኰርቶአል። 6ሰለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ልብህን እንደ እግዚአብሔር ልብ አድርገሃልና፤ 7ስለዚህ እነሆ የሌላ ሀገር ሰዎችን፥ የአሕዛብ ጨካኞችን አመጣብሃለሁ፤ ሰይፋቸውንም በጥበብህ ውበት ላይ ይመዝዛሉ፤ ክብርህንም ያረክሳሉ። 8ወደ ጕድጓድ ያወርዱሃል፤ በሰይፍም ትሞታለህ፤ ሬሳህንም ወደ ባሕር ይጥሉታል። 9አንተ ሰው ስትሆን ለሚገድሉህ ሰዎች፦ እግዚአብሔር ነኝ ትላቸዋለህን? ሰው ነህ እንጂ እግዚአብሔር አይደለህም። 10የሚወጉህም ሰዎች ብዙዎች ናቸው፤ ያልተገረዙትን ሰዎች ሞት ትሞታለህ፤ የሚገድሉህም ሰዎች ያልተገረዙት ናቸው፤ በእጃቸውም ትሞታለህ። እኔ ተናግሬአለሁና ይላል እግዚአብሔር።”
11የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ 12“የሰው ልጅ ሆይ! በጢሮስ ንጉሥ ላይ ሙሾ አሙሽበት፤ እንዲህም በለው፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ጥበብን የተሞላህ፥ ውበትህም የተፈጸመ መደምደሚያ አንተ ነህ። 13በእግዚአብሔር ገነት በዔድን ነበርህ፤ የከበረ ዕንቍስ ሁሉ፥ ሰርድዮን፥ ቶጳዝዮን፥ አልማዝ፥ ቢረሌ፥ መረግድ፥ ኢያሰጲድ፥ ሰንፔር፥ በሉር፥ የሚያብረቀርቅ ዕንቍ፥ ወርቅም ልብስህ ነበረ፤ የከበሮህና የእንቢልታህ ሥራ በአንተ ዘንድ ነበረ፤ በተፈጠርህበትም ቀን ተዘጋጅተው ነበር። 14አንተ ልትጋርድ የተቀባህ ኪሩብ ነበርህ፤ በተቀደሰው በእግዚአብሔር ተራራ ላይ አኖርሁህ፤ በእሳት ድንጋዮች መካከል ተመላለስህ። 15ከተፈጠርህበት ቀን ጀምረህ በደል እስከሚገኝብህ ድረስ በመንገድህ ፍጹም ነበርህ። 16በንግድህም ብዛት ግፍ በውስጥህ ተሞላ፤ ኀጢአትንም ሠራህ፤ ስለዚህ እንደ ርኩስ ነገር ከእግዚአብሔር ተራራ ጣልሁህ፤ የምትጋርድ ኪሩብ ሆይ! ከእሳት ድንጋዮች መካከል አጠፋሁህ። 17በውበትህ ምክንያት ልብህ ኰርቶአል፤ ከክብርህ የተነሣ ጥበብህን አረከስህ፤ በምድር ላይ ጣልሁህ፤ ያዩህም፥ ይዘብቱብህም ዘንድ በነገሥታት ፊት አሳልፌ ሰጠሁህ። 18በበደልህ ብዛት፥ በንግድህም ኀጢአት መቅደስህን አረከስህ፤ ስለዚህ እሳትን ከውስጥህ አውጥቻለሁ፤ እርስዋም በልታሃለች፤ በሚያዩህም ሁሉ ፊት በምድር ላይ አመድ አድርጌሃለሁ። 19በአሕዛብም ውስጥ የሚያውቁህ ሁሉ ያለቅሱልሃል፤ አንተም ለድንጋጤ ሆነሃል፤ እስከ ዘለዓለምም አትኖርም።”
20የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ 21የሰው ልጅ ሆይ! ፊትህን ወደ ሲዶና አቅንተህ ትንቢት ተናገርባት፤ እንዲህም በል፦ 22ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ሲዶና ሆይ! እነሆ በአንቺ ላይ ነኝ፤ በውስጥሽም እከብራለሁ፤ ፍርድንም በአደረግሁብሽ ጊዜ፥ በተቀደስሁብሽም ጊዜ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቂያለሽ። 23ቸነፈርንም በአንቺ ላይ፥ ደምንም በጎዳናሽ ላይ እሰድዳለሁ፤ ከዙሪያሽም በላይሽ ባለ ሰይፍ የተወጉ በመካከልሽ ይወድቃሉ፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ። 24ከእንግዲህም ወዲያ ለእስራኤል ቤት የሚወጋ እሾህ፥ በዙሪያቸውም ከአሉ ከናቋቸው ሁሉ የሚያቈስል ኩርንችት አይሆንም፤ እኔም ጌታ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ። 25ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ የእስራኤልን ቤት ከተበተኑባቸው አሕዛብ ዘንድ እሰበስባቸዋለሁ፤ በአሕዛብና በሕዝብ ፊትም እቀደስባቸዋለሁ፤ ለባሪያዬ ለያዕቆብም በሰጠኋት ምድራቸው ይቀመጣሉ። 26ተዘልለውም ይቀመጡባታል፤ ቤቶችንም ይሠራሉ፤ ወይኑንም ይተክላሉ፤ በዙሪያቸውም በአሉ በሚንቋቸው ሁሉ ላይ ፍርድን በአደረግሁ ጊዜ ተዘልለው ይቀመጣሉ፤ እኔም እግዚአብሔር አምላካቸው፥ የአባቶቻቸውም አምላክ እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።
Currently Selected:
ትንቢተ ሕዝቅኤል 28: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ