ትንቢተ ሕዝቅኤል 38
38
ጎግ የእግዚአብሔር መሣሪያ ሆኖ እንደሚነሣ
1የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ 2“የሰው ልጅ ሆይ! ፊትህን በጎግ ላይና በማጎግ ምድር ላይ፥ በሮስ#“በሮስ” የሚለው በዕብ. የለም። በሞሳሕና በቶቤል አለቃ ላይ አቅናበት፤ ትንቢትም ተናገርበት፤ 3እንዲህም በል፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ የሮስ፥ የሞሣሕና የቶቤል አለቃ ጎግ ሆይ! እነሆ! እኔ በአንተ ላይ ነኝ። 4እመልስህማለሁ፤ በመንጋጋህም ልጓም አገባብሃለሁ፤ አንተንና ሠራዊትህን ሁሉ፥ ፈረሶችንና ፈረሰኞችን፥ የጦር ልብስ የለበሱትን ሁሉ፥ ጋሻና ራስ ቍርን፥ ሰይፍንም የያዙትን ሁሉ አወጣለሁ። 5ፋርስንና ኢትዮጵያን፥ ሊብያንም፥#ዕብ. “ፉጥ” ይላል። ከእነርሱ ጋር ጋሻና የራስ ቍርን የለበሱትን ሁሉ፥ 6ጎሜርንና ከእርሱ ጋር ያሉትን ሁሉ፥ በሰሜን ዳርቻም ያለውን የቴርጋማን ቤትና ጭፍሮቹን ሁሉ፥ ብዙዎችንም ሕዝቦች ከአንተ ጋር አወጣለሁ።
7“አንተና ወደ አንተ የተሰበሰቡ ወገኖችህ ሁሉ ተዘጋጁ፤ አንተም ራስህን አዘጋጅተህ ጠባቂ ሁናቸው። 8ከብዙ ዘመንም በኋላ ትፈለጋለህ፤ በኋለኛውም ዘመን፥ የዘለዓለም ባድማ በነበሩ በእስራኤል ተራሮች ላይ ከብዙ ሕዝብ ውስጥ ወደ ተሰበሰበች፥ ከሰይፍ ወደ ተመለሰች ምድር ትገባለህ፤ እርስዋም ከሕዝብ ውስጥ ወጥታለች፤ ሁሉም በሰላም ይቀመጡበታል። 9እንደ ዝናም ትወጣለህ፤ እንደ ደመናም ምድርን ትሸፍን ዘንድ ትደርሳለህ፤ አንተም ከብዙ ሕዝብና ሠራዊት ጋር ትወድቃለህ።”
10ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ “በዚያ ቀን ነገር ወደ ልብህ ይገባል፥ ክፉ አሳብንም ታስባለህ፤ እንዲህም ትላለህ፦ 11ወደ ጠፋች ሀገር እወጣለሁ፤ ተዘልለው በሰላም ወደሚኖሩ፥ ሁላቸው ሳይፈሩ ያለ ቅጥርና ያለ መወርወሪያ፥ ያለ መዝጊያም ወደሚቀመጡባት ምድር እገባለሁ፤ 12ምርኮን ትማርክ ዘንድ፥ ብዝበዛንም ትበዘብዝ ዘንድ፥ ባድማም በነበሩ፥ አሁንም ሰዎች በሚኖሩባቸው ስፍራዎች ላይ፥ ከአሕዛብም በተሰበሰበ፥ ከብትና ዕቃንም በአገኘ፥ በምድርም መካከል በተቀመጠ ሕዝብ ላይ እጅህን ትመልሳለህ። 13ሳባና ድዳን፥ የተርሴስም#ግሪክ ሰባ. ሊ. “የካርታግና” ይላል። ነጋዴዎች፥ መንደሮችዋም ሁሉ፦ ምርኮን ትማርክ ዘንድ መጥተሃልን? ብዝበዛንስ ትበዘብዝ ዘንድ፥ ብርንና ወርቅንስ ትወስድ ዘንድ፥ ከብትንና ዕቃንስ ትወስድ ዘንድ፥ እጅግስ ብዙ ምርኮ ትማርክ ዘንድ ወገንህን ሰብስበሃልን? ይሉሃል።”
14አንተ የሰው ልጅ ሆይ! ስለዚህ ትንቢት ተናገር፤ ጎግንም እንዲህ በለው፥ “ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ በዚያ ቀን ሕዝቤ እስራኤል በሰላም በተቀመጠ ጊዜ አንተ የምትነሣ አይደለምን? 15አንተም፥ ከአንተም ጋር ብዙ ሕዝብ ሁላቸው በፈረሶች ላይ የተቀመጡ፥ ታላቅ ወገንና ብርቱ ሠራዊት፥ ከሰሜን ዳርቻ ከስፍራችሁ ትመጣላችሁ። 16ምድርንም ትሸፍን ዘንድ እንደ ደመና በሕዝቤ በእስራኤል ላይ ትወጣለህ። በኋለኛው ዘመን ይሆናል፤ ጎግ ሆይ!#“ጎግ ሆይ” የሚለው በዕብ. ብቻ። በፊታቸው በተቀደስሁብህ ጊዜ፥ አሕዛብ ያውቁኝ ዘንድ በምድሬ ላይ አወጣሃለሁ።
17“ጌታ እግዚአብሔር ለጎግ እንዲህ ይላል፦ በእነርሱ ላይ እንደማመጣህ፥ በዚያች ዘመን ብዙ ዓመት ትንቢት በተናገሩ በባሪያዎች በእስራኤል ነቢያት እጅ በቀደመው ዘመን ስለ እርሱ የተናገርሁ አንተ ነህን? 18በዚያም ቀን ጎግ በእስራኤል ምድር ላይ በመጣ ጊዜ መቅሠፍቴ በመዓቴ ይመጣል ይላል ጌታ እግዚአብሔር። 19በቅንአቴና በመዓቴ እሳት ተናግሬአለሁ፦ በእርግጥ በዚያ ቀን በእስራኤል ምድር ጽኑ መናወጥ ይሆናል፤ 20ከእግዚአብሔርም ፊት የተነሣ የባሕር ዓሣዎችና የሰማይ ወፎች፥ የምድረ በዳም አራዊት፥ በምድርም ላይ የሚንቀሳቀሱ ተንቀሳቃሾች ሁሉ፥ በምድርም ላይ የሚኖሩ ሰዎች ሁሉ ይንቀጠቀጣሉ፤ ተራሮችም ይገለባበጣሉ፤ ገዳላገደሎችም ይወድቃሉ፤ ቅጥርም ሁሉ ወደ ምድር ይወድቃል። 21በተራሮችም ሁሉ በእርሱ ላይ ፍርሀትን እጠራለሁ፤ የሰውም ሁሉ ሰይፍ በወንድሙ ላይ ይሆናል፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። 22በቸነፈርና በደም እፈርድበታለሁ፤ ዶፍም፥ የበረዶም ድንጋይ፥ እሳትና ድኝም በእርሱና በጭፍሮቹ፥ ከእርሱም ጋር በአሉ በብዙ ሕዝብ ላይ አዘንባለሁ። 23ታላቅ እሆናለሁ፤ እቀደስማለሁ፤ እመሰገናለሁም፤ በብዙ አሕዛብም ዐይን የታወቅሁ እሆናለሁ፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።
Currently Selected:
ትንቢተ ሕዝቅኤል 38: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ